መጋኛን ለማስለቀቅ የተጀመረ ፉከራ የሰው ህይወት አጠፋ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መጋኛን ለማስለቀቅ የተጀመረ ፉከራ የሰው ህይወት አጠፋ።
አርሶ አደር ግርማ ዳኜ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡
ከሰሞኑ ግን በሆድ ህመም ምክንያት ወደ እርሻ ስፍራው ሄዶ የእለት ስራውን መከወን ባለመቻሉ ቤቱ ይተኛል፡፡
በዚያ አካባቢ በቆየ ልማድ ተመሳሳይ የሆድ ህመም በሽታ መጋኛ በሚል በቆየ ልማድ ነው የሚጠራው፡፡
እናም የአቶ ግርማ ዳኜ ባለቤት ከቤቷ ወጣ በማለት ባህላዊ መድሀኒት ማፈላለግ ትጀምራለች፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ለዚህ ህመም መፍትሄ ይሰጣል በማለት በሰፊው የሚተገብሩት ልማድ አለ፡፡
ህመምተኛውን በጀርባው በማስተኛት እምብርቱ አካባቢ ጠብመንጃ በመደቀን ይፎክራል፣ ይሸልላል፡፡
በዚህ መንገድ መጋኛው ፈርቶ ህመምተኛውን ጥሎት ይሄዳል በሚል እምነት መነሻ ወይዘሮዋ ወደ ጎረቤት በመሄድ ለዚሁ ህክምና የአከባቢው ታጣቂ የሆነውን ጎረቤቷን አቶ ለማ ከልሌን ትጠራለች፡፡
አቶ ለማ ግዜ አላጠፉም ወደ ህመምተኛው ቤት በመሄድ ጤንነቱ ጥሩ እንዲሆን ተመኝቶና የህመሙን ስሜት ጠይቀው ህክምናውን ይጀምራል፡፡
የያዘውን መሳሪያ በአቶ ግርማ ሆድ ላይ በመደገን መፎከርና መሸለል ይጀምራል፡፡
የአካባቢው ሰዎች ይህንን ሲያደርጉ ቀድመው መሳሪያው ጥይት እንዳልጎረሰ ያረጋግጣሉ፡፡
አቶ ለማም መሳሪያውን ወደ ላይ በማድረግ ደጋግመው ምላጭ በመሳብ ይህንኑ አድርገዋል፡፡
ነገር ግን ህክምናው አንደተጀመረ አፍታም ሳይቆይ ጥይቱ ይጮህና የአቶ ግርማን ሆድ በመምታት ለዘላለሙ ያሸልባሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አቶ ለማ በሰው መግደል ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነ ነው የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኢንስፔክተር ፍቅሩ ውቤ የተናገሩት፡፡
With our e-mail alerts, you will get everything from breaking news about Ethiopia to the days most popular videos, drama, health tips and stories sent straight to your inbox. Sign up for Email alerts