ሁለት ሰዎችን አብነት አካባቢ የገደለው ወጣት በ20 ዓመት እስራት ተቀጣ Man who killed two people around Abinet hotel sentenced to 20 years in pirson

በቂም በቀል ተነሳስቶና ስለት ታግዞ በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል የፈፀመው የ19 ዓመቱ ተከሳሽ ዳዊት ወርቅነህ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ20 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ሲል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት አርብ ታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈበት።

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ እንዳስረዳው፤ ተከሳሹ በሁለት ክሶች ይጠየቃል ይላል። በመጀመሪያው ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ቂም በመያዝ ሰውን ለመግደል አስቦ ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 6፡30 ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 05/08 ልዩ ቦታው አብነት ላይት ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ሟች ሚኪያስ ፋንታሁንን በጩቤ በግራ በኩል ደረቱ አካባቢ አንድ ጊዜ ወግቶ ለመግደሉ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል ሲል ያትታል።

በሁለተኛ ክሱ ዐቃቤ ሕግ እንደሚያመለክተው ደግሞ ተከሳሹ ከላይ በተጠቀሰው ጊዜና ልዩ ቦታው አብነት አደባባይ አስፓልት ላይ ሟች ውብሸት ኑርሰፋን በጩቤ በግራ በኩል ደረቱ አካባቢ አንድ ጊዜ ወግቶ በመግደሉ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው መግደል ወንጀል ተከሷል ይላል።

     የ19 ዓመቱ ወጣት የተመሰረተበትን ክስ በሚገባ ሊከላከል ባለመቻሉና ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ክሱን ለችሎቱ ሊያስረዳ በመቻሉ ተከሳሽ ጥፋተኛ ተብሏል። በዚህም መሠረት በፈፀመው የግድያ ወንጀል በ20 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።