‹‹ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት መላ ዘመናቸውን አሳልፈዋል›› – የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዜና ሕይወት እና ዕረፍት
- ከትምህርት ቤትና ከመጻሕፍት ያገኙት ዕውቀት አራት ዓይና ያደረጋቸው ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በተጠያቂነት ደረጃ የሚገኙና አገልግሎታቸውም ሙሉ ነበር፡- ቀዳሽና መዘምር፤ ጋዜጠኛና ሰባኬ ወንጌል፤ ጸሐፊና ተርጓሚ፤ አስተዳዳሪና መምህር፤ የአውራጃ አብያተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ ኤርትራን ጨምሮ የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስምንት መምሪያዎች ምክትልና ዋና ሓላፊ፡፡
- ሊቁ በሓላፊነት በተመደቡባቸው ቦታዎች ኹሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተማር፤ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፤ ሰበካ ጉባኤያትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር፤ አገልጋዮች ካህናትን በትምህርትና ሥልጠና በማብቃት አስተዳደርን ለማሻሻልና ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ድርጅት በንዋያተ ቅድሳትና በጽ/ቤት መገልገያዎች ለማሟላት እንደነበር ዜና ሕይወታቸው በስፋት አትቷል፡፡
- የአብነት ት/ቤቶችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎችንና ኮሌጆችን በበላይነት በሚያስተባብረው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ለሦስት ጊዜያት በዋና ሓላፊነት ተመድበው የላቁ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከእኒኽም በመንግሥት የተወረሱ 27 መንፈሳውያንና ዘመናውያን ት/ቤቶችን በተለይም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲመለስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐሳብ በማቅረብና በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነም በኋላ የበኩላቸውን ክትትል በማድረግ መንፈሳዊ ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያናችን ተመልሷል፡፡
- በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾነው ከተመደቡበት ጥቅምት ወር ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው መዳረሻ ከሌሎች ሊቃውንት ጋራ በመኾን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል÷ ቤተ ክርስቲያናችን የራስዋ የተጣራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት 81 ቅዱሳት መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ መሠረትነት አርመውና አስተካክለው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ለካህናትና ምእመናን በሴሚናር ሲያሰለጥኑበት የቆዩት የቃለ ዐዋዲ ደንብ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሻሻል የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት›› መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በአንድነት አዘጋጅተው ለምእመናን እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡ በርካታ የቅዱሳን ገድላትና የመላእክት ድርሳናት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡
- የቤተ ክህነት ሥነ ጽሕፈት ኮሚቴ አባል በመኾን በዐበይት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚወጡ ኅትመቶችና በሚሠራጩ የሬዲዮ መግለጫዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና በምርምር የተደገፉ፤ አንባቢንና አድማጭን የሚያረኩ በርካታ ጽሑፎችን በማቅረብ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡ በግል አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን››፤ ‹‹ሳታዩት የምትወዱት›› በሚል ለትምህርትና ለተግሣጽ ባሰራጯቸው ሥራዎቻቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለነገረ ሃይማኖት መጠበቅ ተከራክረዋል፤ ተሟግተዋል፡፡ በተለይም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ክፍል ኾኖ እንዲሰጥ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ መጽሐፉም በኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ለመምህራንና ለተማሪዎች መመሪያና ማጣቀሻ ኾኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
- የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊም ነበር፡፡ ከግንቦት ፲፬ – ፴ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. የያሬዳዊ ማሕሌትን ዐውደ ትርኢት በምዕራብ ጀርመን ለማሳየት ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ በመኾን የማሕሌታችንን ሥርዐት አሳይተው ተመልሰዋል፡፡ እ.አ.አ ከሐምሌ ፱ – ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ‹‹ክርስቶስን ዛሬ መስበክ›› በሚል ርእስ በእስክንድርያ በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክተኛ በመኾን ጥንታዊ እምነቷንና ሥርዐቷን በቃልም በጽሑፍም በመግለጥ ተሳትፈዋል፡፡ በየመንና በጅቡቲ ለሚኖሩ ምእመናን ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡፡
* * *
- ከደግ ቤተሰብ ተገኝተው በመልካም አስተዳደግ የወጡት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በትዳራቸውም የጋብቻ ጽናት ምሳሌነታቸውን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በተክሊልና በሥርዐተ ቁርባን ካገቧቸው የሕግ ባለቤታቸው ወ/ሮ ድጋፍ ወርቅ ፈቄ ጋራ የ፶ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን ከኹለት ዓመት በፊት አክብረው ነበር፡፡ ስምንት ልጆችንና ዐሥር የልጅ ልጆችን አፍርተውም ለወግ ለማዕርግ አብቅተዋል፡፡
- ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በሢመተ ክህነት÷ በ፲፱፻፵፩ ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕርገ ዲቁና፤ ሰኔ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሢመተ ቅስና ተቀብለዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው በዜማ፣ በአቋቋም፣ በቅኔና በነገረ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ኾኖ ትርጓሜ መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ከተለያዩ ሊቃውንት በመማር ምስጢር አደላድለዋል፡፡ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ የነገረ መለኰት ትምህርት የቴዎለጂ ዲፕሎማ ተቀብለዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት እና በዳግማዊ ምኒልክ የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
- ‹‹በዕለተ ሰንበትና በዐበይት በዓላት እየቀደሱና እያወደሱ፣ በሥራ ቀናት በቢሮ እየሠሩ፣ ለምእመናን ወንጌል እየሰበኩ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እያስተማሩና እያሠለጠኑ ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሙሉ አገልግሎት ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡
- በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋት አውራጃ በማፉድ ወረዳ በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም አጥቢያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ስማቸው ክንፈ ገብርኤል፤ ያረፉትም የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዋናው በዓል በሚከበርበት በታኅሣሥ ገብርኤል፤ ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ለነፍሳቸው ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፤ በእርሳቸው እግር ምሁራንን እንዲተካልን ፈጣሪን በጸሎት እንለምነዋለን፡፡››
የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን ዜና ሕይወት ወዕረፍት ከዚኽ በታች ይመልከቱ፡፡

