ከደም እጦት ጋር በተያያዘ 40 በመቶ እናቶች በየዓመቱ ይሞታሉ Among patients who died of lack of blood, 40% are mothers

በአሸናፊ ደምሴ
በአገራችን ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ህይወታቸው እንደሚያልፍና ለዚህም ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ከደም ለጋሾች ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት “የሚዲያ ተቋማት አስተዋፅኦ በበጐ ፈቃድ የደም ልገሳ መበራከት ዙሪያ” በሚል ለመገናኛ ብዙሃንና ለኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የውይይት ሃሳቦችን ያቀረቡት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ገ/ሚካኤል እንደተናገሩት፤ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በአንድ ሀገር ውስጥ ከአጠቃላዩ የህዝብ ቁጥር አንፃር አንድ በመቶ የሚሆነው ደም መለገስ አለበት ቢልም፤ ሀገራችን አላት ከሚባለው 90 ሚሊዮን ህዝብ አንፃር በዓመት 900 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ ነበረበት ያሉ ሲሆን፤ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን በደም ባንኮች ያለው ስብስብ 88 ሺህ ዩኒት ወይም 10 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በመሆኑ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች እናቶች ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ መሞታቸው ተጠባቂ ነው፤ ይህንም ለመቀነስ በእጅጉ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በብሔራዊ ደረጃ 25 የሚደርሱ የደም ባንኮች መኖራቸውን የተናገሩት ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል፣ እነዚህ የደም ባንኮች እስከ 400 ሺህ ዩኒት ደም በዓመት የመሰብሰብ አቅም አላቸው ብለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ200 ሺህ እስከ 250 ሺህ ዩኒት የደም ፍላጐት መኖሩን ገልፀው፤ ባለፈው ዓመት 88 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡንና በያዝነውም ዓመት እስከ 160 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ግንዛቤን ከማስረጽ አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝባችን ደም የመለገስ ባህሉ ደካማ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዳንኤል፤ ከ2ሺህ 500 እስከ 3ሺህ የሚደርሱ ቋሚ ደም ለጋሾች ቢኖሩም በቂ አይደሉም ብለዋል።
ይህንንም ቁጥር ለማሻሻልና የደም ለጋሾችን ለመጨመር እንደ እንቅፋት ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዳንዶች ደም ከለገሱ የሚጐዱ ስለሚመስላቸው፣ መርፌን ፍራቻ፣ የግንዛቤና የተሳሳተ አመለካከት መኖሩ ለደም ለጋሾች እጥረት እንደዋነኛ መንስኤዎች ናቸው ተብለው ተጠቅሰዋል። 

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።