ለውጪ ሀገር የሕክምና ጉዞ የሚያማክር ተቋም ሥራ ጀመረ Medical center consults patients who wish to travel abroad seeking medical care
ኢትዮጵያውያን ዓለም በደረሰበት የሕክምና ደረጃ ተጠቃሚ እንደሆኑ የማድረግ አላማን አንግቦ የተነሳው ጌትዌል የጤና ማማከር አገልግሎት ተቋም ስራውን መጀመሩን አስታወቀ። የጌትዌል የጤና ማማከር አገልግሎቶች መስራችና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በጋሻው ባይለየኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ተቋሙ በሀገራችን ለሚገኙ ህሙማን የተሻለ ህክምናን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያገኙ ለማስቻል የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም የምክር፤ የውጪ ሀገር ህክምና ማመቻቸት፣ የጉዞ ወቅት አጋዥ የህክምና ባለሙያዎችን ማቅረብና የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ ታካሚዎች የተሟላ ህክምና እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል።
ጌትዌል የጤና ማማከር አገልግሎት ሰጪ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ ዕውቅና ካላቸው በታይላንድ፣ በህንድ፣ በሲንጋፖርና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ውስጥ ከሚገኙ ስምንት ሆስፒታሎች ጋር በጥምረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በእነዚህ ሆስፒታሎችም ውስጥ ዜጎች በሀገራችን ውስጥ የማይገኙ ወይም አቅርቦታቸው ዝቅተኛ በሆኑ የህክምና ዘርፎች እንዲታከሙ የማማከርና የማገናኘት ስራዎችን ይሰራል ተብሏል።
በዚህም በሀገራችን አቅርቦታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ የህክምና ዘርፎች መካከል ተቋሙ የሚያተኩርባቸው እንደካንሰር፣ የልብና የሳንባ ህክምናና ቀዶ ጥገና፣ የነርቭ ህክምናና ቀዶ ጥገና፣ የአጥንት መገጣጠሚያ ህክምና፣ የመሀንነት ችግር፣ እንደኩላሊት፣ ጉበትና መቅኔ ያሉትን የውስጥ አካል ማስቀየርን ጨምሮ ለህሙማን አገልግሎቱን የት ከማንና እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ያማክራል ብለዋል።
ከጌትዌል ተቋም ጋር ለመስራት ከአራቱ አገራት የተመረጡት ስምንት ሆስፒታሎች ያላቸው የሰው ሃይልና ብቃት፣ የሚጠቀሙት የህክምና ቴክኖሎጂ ደረጃ፣ ከውጪ ሀገር ለሚመጡ ታካሚዎች ያላቸው ልዩ አገልግሎትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተቀባይነት ከግምት ውስጥ ገብቶ የተመረጡ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር ሆስፒታሎቹ በዝቅተኛ ዋጋ የተሻለ ህክምናን መስጠት መቻላቸው ተመራጭ እንዳደረጋቸው የተቋሙ መስራችና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር በጋሻው ባይለየኝ አስረድተዋል።
በተቋሙ በኩል ወደተጠቀሱት ሀገሮች እና ሆስፒታሎች ሄዶ መታከም የሚፈልግ ደንበኛ ሲመጣ የህሙማኑን ሁኔታ ማጣራትና የውጪ ሀገር ህክምና አስፈላጊነትን፤ ቀደም ብሎ የተከታተላቸውን የህክምና ማስረጃዎች በመመርመር፤ በሽተኛው ከሚታከምበት ሆስፒታል ዶክተሮች ጋር መረጃን መለዋወጥ፤ የጉዞውን ሁኔታ ማሰናዳት ጨምሮ ታካሚው ከውጪ ሀገር ህክምናውን ጨርሶ ሲመለስ የህክምና ክትትል እንዲያገኝ ማመቻቸትን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል። እንደዶክተር በጋሻው ባይለየኝ ገለፃ ከሆነ በቀጣይ በውጪ ሀገር በሚሰጡ ክሊኒካል ፌሎ ሺፕ ፕሮግራሞች ላይ የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ ልምድ ይዘው እንዲመጡ ከማስቻል ባሻገር፤ የውጪ ዶክተሮች በሀገራችን ተገኝተው ህክምናዎችን የሚሰጡበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ጠቁመዋል።
With our e-mail alerts, you will get everything from breaking news about Ethiopia to the days most popular videos, drama, health tips and stories sent straight to your inbox. Sign up for Email alerts