የገዢው ፓርቲ አባላት በታዛቢነት ተመረጡ – ፍኖተ ነጻነት
የህዝብ ታዛቢ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰዎችን ለመምረጥ በየቀበሌው በተደረገው ታዛቢዎችን የማስመረጥ ሂደት ላይ የገዢው ፓርቲ አባላት በታዛቢነት መመረጣቸውን በምርጫው ሂደት ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች ለፍኖተ-ነፃነት ገለፁ፡፡
በዛሬው እለት ታዛቢዎችን በማስመረጥ ሂደት ላይ “የገዢው ፓርቲ አባላት ህዝቡን በማግለል እርስ በእርስ በመመራረጥና የምርጫ ሂደቱን በድብቅ እያካሄዱ” መሆኑን የገለፁት የፍኖተ-ነፃነት ምንጮች “ይህ አካሄድ ህገ-ወጥ እና የምርጫውን ደንብ የጣሰ” መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በደንቡ መሠረት የየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል የሆነ ሰው ታዛቢ መሆን እንደማይችል የተገለፀ ቢሆንም ይህ ደንብ ተጥሶ የገዢው ፓርቲ አባላት በታዛቢነት እየተመረጡ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተያያዘ ዜና የህዝብ ታዛቢ ምርጫውን ለመታዘብ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ወረዳ የተገኙ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት በተመረጡት የህዝብ ታዛቢዎች ላይ ባነሱት ቅሬታ የተነሳ ለእስር መዳረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከታሰሩት የአንድነት ፓርቲ አባላት ውስጥ የወረዳ 12/13 ሰብሳቢ የሆነው አቶ ብሩክ አየለ ይገኝበታል፡፡