Registration for condominium homes for Ethiopian diaspora will start next week በውጪ ሃገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የማህበራት ቤቶች ምዝገባ በቀጣዩ ሳምንት ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 26፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውጪ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመስራት በተቀረፀው ፕሮግራም መሰረት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በያሉበት ሃገር ምዝገባ እንደሚጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከክልሎች ከከተማ መስተዳደሮች ጋር በተደረገው ቅድመ ዝግጅት ላይ የተወያየ ሲሆን፥ የመመሪያ ማውጣት ስራዎችና የመሬት ዝግጅቶች በአብዛኛው አካባቢዎች ላይም በመተግበር ላይ ነው ተብሏል።
ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ የአለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 3 ነጥብ 2 ሚሊየን እንደሚደርስ ይገመታል።
ከእነዚህ ውስጥ ከ3 ሺህ ባለ የሚሆኑት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች በኢትዮጵያ ተሰማርተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማህበር ተደራጅተው የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ዕድል መንግስት ማመቻቸቱም ይታወቃል።
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ እና በክልሎች የ10/90፣ የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ምዝገባ መካሄዱም የሚታወስ ነው።
የማህበራት የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ለማከናወን አሁን ላይ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የመሬት ዝግጅት እና መሰል ስራዎች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው፥ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሃገር ምዝገባ እንደሚጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በማህበር ቤቶች መመሪያ መሰረት ከ12 እስከ 24 በመሆን መደራጀት እንደሚችሉና በመረጡት ዲዛይን መሰረትም ቤቶቻቸውን ማስገንባት እንደሚችሉም ነው የተገለፀው።
የአጠቃላይ ቤቱን ሂሳብ ሀምሳ በመቶ አስቀድመው መቆጠብ ሲኖርባቸው፥ ቀሪውንም ቤቶቹ ሲጠናቀቁ መፈፀም ይኖርባቸዋል።
በሞላልኝ ከሳቴብርሀን
With our e-mail alerts, you will get everything from breaking news about Ethiopia to the days most popular videos, drama, health tips and stories sent straight to your inbox.
Sign up for Email alerts