ሰው ለመግደል የሞከረው በ14 ዓመት ተቀጣ Man sentenced to 14 years for attempted murder

የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በቂም በቀል ተነሳስቶ፤ ሰውን ለመግደል በማሰብ የግል ተበዳይን በመስታወት ስባሪ ደጋግሞ ሆዱን በመውጋት የሆድ ዕቃ ጉዳት፣ የግራ ጆሮ ማቁሰል፣ የማጅራት ግዝገዛና በቀኝ እጅ ላይ ወግቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ሲል በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ባሳለፍነው አርብ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ወሰነ።

እንደ ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ከሆነ፤ ተከሳሽ አቶ እንዳለ ወልዴ አበጋዝ ሰውን ለመግደል አስቦ ሐምሌ 11 ቀን 2005 ዓም በግምት ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04/05 ክልል ውስጥ ልዩ ቦታው ሻውልደማ ትምህርት ቤት ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ የግል ተበዳይ አቶ ሽመርጋ ገዳን ጨካኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ደጋግሞ በመስታወት ስባሪ በመውጋት፤ አንደኛ ትንሹን አንጀት በመቆራረጥና የሆድ ዕቃ ጉዳት በማድረስ፤ ሁለተኛ በግራ ጆሮው ላይ በመውጋት እና በቀኝ እጅ ላይ በመወጋት ያቆሰለና ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ እንዲሁም የግል ተበዳይን ማጅራት በመገዝገዝ ያቆሰለ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው መግደል ሙከራ ወንጀል ተከሷል ይላል።

ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን፤ ተከሳሽ በበኩሉ የተመሰረተበትን ክስ በሚገባ ሊከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ተብሏል።

     የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ድርጊቱ በሙከራ የቀረ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሞት ቅጣት ጥያቄ ወደጎን በመተው በ14 ዓመት ፅኑ እስራትና ለ5 ዓመት በሚደርስ ከማህበራዊ መብቶቹ እንዲታገድ ሲል የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።