አዲሱ የአዋሽ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ Awash Bridge Opens to Traffic

አዲስ አበባ ህዳር 26/2007 አዲሱ የአዋሽ ወንዝ ድልድይ ግንባታ በመጠናቀቁ ዛሬ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮ-ጅቡቲ መስመር 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚስተናገድበት መንገድ ሲሆን በቀን ከ20 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችንም ያስተናግዳል።

የዚህ መስመር አካል የሆነው አሮጌው የአዋሽ ድልድይ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ከመስጠቱ ባለፈ በአንድ ጊዜ ከአንድ ተሽከርካሪ በላይ ማሳለፍ ባለመቻሉ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን እና የአዲሱ ድልድይ መጠናቀቅም ይህንን ችግር እንደሚፈታው በመስመሩ የሚገለገሉ አሽከርካሪዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንዳሉትም መስመሩ ለአገሪቱ ንግድ ወሳኝ በመሆኑና የትራፊክ ፍሰቱም እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አዲስ ድልድይ መስራት አሰፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም የመንገድ ኮሪደሩን የትራፊክ ፍሰት አስተማማኝ የሚያደርግ፣ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ ድልድይ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ ለአገልግሎት በቅቷል።

የድልድዩ ግንባታ ሥራ 240 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ገንዘቡም ከጃፓን መንግስት በተገኘ እርዳታ የተሸፈነ ነው።

ግንባታው የተጠናቀቀው ይህ ድልድይ 143 ሜትር ርዝመትና 9 ነጥብ 3 ሜትር ስፋት ሲኖረው በመግቢያና መውጫ በኩል በጥቅሉ 935 ሜትር መዳረሻ መንገድም ተሰርቶለታል።

ከ40 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠው የቀድሞው ድልድይ በአንድ ጊዜ 36 ነጥብ 6 ቶን የመሸከም አቅም ሲኖረው የማስተላለፍ ችሎታው ደግሞ በአንድ ጊዜ አንድ ተሽከርካሪ ብቻ ነው።

በአንጻሩ አዲሱ ደልድይ በአንድ ጊዜ 40 ነጥብ 8 ቶን የመሸከምና ሁለት ተሽከርካሪዎችን የማስተላለፍ አቅም ያለው ነው።

ድልድዩ ከመሃል አገር ወደ ጂቡቲና ሶማሊያ በሚያመራው ዋና መንገድ ላይ የተገነባ በመሆኑ በአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ በኩል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከተጠቀመችበትና በመጠቀም ላይ ካለችበት የጂቡቲ ወደብ ጋር በማገናኘት ሰፊ ሚና እንደሚጫወት ነው አቶ ሳምሶን የተናገሩት።

የድልድዩን ግንባታ ሥራ ያከናወነው ሳቶ ካጂዮ የተባለ የጃፓን የሥራ ተቋራጭ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ሴንትራል ኮንስትራክሽን የተባለው ጃፓናዊ አማካሪ ድርጅት ነው።

ሦስት ዓመታትን በፈጀው በዚህ ድልድይ ግንባታ ሂደት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጥሯል። ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም ዘመናዊ አሰራርንና ቴክኖሎጂን ከጃፓናውያን መቅሰም እንደቻሉ ነው የተናገሩት።

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።