ነውጠኛ ሄሊኮፕተር ያደመቀው በዐል (+video)

ዕለቱ 9ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እና የሕገ-መንግስታችን 20ኛ የልደት በዓል የሚከበርበት ህዳር 29፤ ቦታው ደግሞ ለዚሁ በዓል ተብሎ በፍጥነት እንዲደርስ የተደረገው የአሶሳ ከተማ ስቴድየም ነው፡፡ የኢ.ፌ.ድሪ ጠቅላላ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ የፌደሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣የጎረቤት ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስቴሮች፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የባህል ቡድኖች…ብቻ ምን አለፋችሁ ኢትዮጵያ በስቴድየሙ ከትማለች፡፡ በዓሉ ሰፊ፣ ደማቅና ብዙ ሊባልለት የሚገባ ነበር፡ ስለዚህ ሌላው በይደር ይቆየንና ለዛሬ አንድን ለየት ያለ ክስተት መርጨ ላውጋችሁ።   ለበዓሉ ከታቀዱት ትርኢቶች አንዱ፣ ለ26 ቀናት ሀገሪቱን በመዞር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 204 ሚልዮን ብር የሰበሰበው እና ከታላቁ መሪ ለኢትዮጲያ ብሔር ብሔረሰቦች የተበረከተው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ግድቡንም በአሉንም ወደምታስተናግደው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ መግባት ነበር፡፡ ዋንጫው ወደ አሶሳ ስቴድየም እንዲገባ የታሰበውም ለየት ባለ መንገድ ነበር፤ በሄሊኮፕተር ከሰማይ። በእርግጥ ይህ ለየት ያለ አቀራረብ የታሰበለትን በአሉን የማድመቅ ግብ መትቷል ፡፡ ግቡን የመታው ግን አዘጋጆቹ ባሰቡት መንገድ አልነበረም። ታሪኩ እንዲህ ነዉ። አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፡ የሚመራውን ቡድን በመያዝ የስቴድየሙን መሀል ከተቆጣጠረ የቡድኑን 26 ቀን ሀገር አቀፍ ጉዞ በሰፊው መተረክ ከመጀመሩ ነበር ዋንጫውን ያዘው የመከላከያ ሄልኮፕተር በድንገት ከተፍ ያለው፡፡ ሄልኮፕተሩ ወደ ሜዳው መሀል ጉዞውን ቀጥሏል፤ ሰራዊት ፍቅሬም ትረካዉን። ሄሊኮፕተሩ ወደ መሀል እስኪደርስ የተነቃነቀ ሰው አልነበረም፣ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የገመተ የነበረም አይመስል። ልክ ሄልኮፕተሩ ሜዳው መሀል ደርሶ ከፍታ […]