ለአቶ ግርማ ሰይፉ አክብሮቴን እገልጻለሁ – ግርማ ካሳ

አቶ ግርማ ሰይፉ በኢትዮጵያ ፓርላማ ብቸኛ የተቃዋሚዎች ተወካይ ናቸው። በፓርላማ ዉስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ትረታ የሳቡ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎች በመጠየቅ፣ በተስጣቸው ጥቂት ደቂቃዎች የአገዛዙ ባለስልጣናትን ደም ግፊት በየጊዜው እንዲጨመር የሚያደርጉ አንጋፋ ሰው ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ለተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን፣ በፓርላማ የሕዝብ ብቸኛ ድምጽ በመሆን ለሚያበረክቱት አስተዋጾ ያለኝን ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ። ለእኝህ ወዳጄ ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ እገልጻለሁ።

የሕሊና እስረኞችን በተመለከተ ይፋ በሆንው የሚሊዮኖች ድምጽ ለሕሊና እስረኞች የበየነ መረድ ዘመቻን በተመለከተ፣ በአንድነት ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ጊዜ አቶ ግርማ ሰይፉ አንድ ጥያቄ ይጠየቃሉ። የአንድነት ፓርቲ አባል የነበሩና ከነጀነራል መላኩ ተፈራ ጋር፣ ከአምስት አመታት በፊት ስለታሰሩ፣ አቶ መላኩ ስለሚባሉ እሰረኛ የተመለከተ ነው። “አቶ መላኩ የአንድነት አባል ነበሩ። የሕሊና እስረኛ ተደርግው ነው ወይ የሚታዩት ?” የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው። አቶ መላኩ እነ አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ፣ ናትናኤል መኮንን ከመታሰራቸው ሁለት አመታት በፊት የታሰሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ተገደው ይሁን አምነዉበት፣ በኢቲቪ ቀርበው፣ ከግንቦት ሰባት ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ስንት እስረኛ እያለ፣ የእኝህ ሰው ስም በተናጥል ተጠቅሶ ጥያቄ መቅረቡ በራሱ አጠያያቂ ነው። ሆን ተብሎ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በሚሰጡት መልስ ችግር ዉስጥ እንዲገቡ፣ ታስቦ እንደሆነ መገመት አያቅትም።

አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የታሰረ ሁሉ የሕሊና እስረኛ እንዳልሆነ ገልጸው፣ አንድ ሰው ጥፋት አጥፍቻለሁ ብሎ ካመነ (ወዶም ሆኖ ተገዶ) ፣ አላጠፋም ብለው መከራከር እንደማይችሉ ገልጸዋል። ሰላምን በማስጠበቅ አንጻር፣ አንድነት ከኢሕአዴግ የበለጠ እንጂ ያላነሰ የጸረ-ሽብርተኝነት አቋም እንዳለውም አቶ ግርማ ሰይፉ አስረድተዋል።

ሆኖም የአቶ ግርማ ሰይፉ መልስ በመለጠጥና በማጦዝ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻ አቶ ግርማ ሰይፉ ላይ እና ፓርቲያቸው አንድነት ላይ ተከፍቷል። የዚህ ዘመቻ አዝማች ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው ደግሞ “የሕዝብ አይን እና ጆሮ ነኝ” የሚለው በሻእቢያ የሚደገፈው ኢሳት ነው።
አቶ ግርማ ሰይፉ አንድነት በሽብርተኝነት ላይ ከኢሕአዴግ የበለጠ እንጂ ያነሰ አቋም እንደሌለው በግልጽ አስቅምጠዋል። ጸረ-ሽብርተኝነት እና ሽብርተኛ የሆነው የጸረ-ሽብርተኘንት ሕጉ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የአንድነት ፓርቲ በጸረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ላይ ያለው አቋም ግልጽ ነው። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መርህ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎ እንቅስቃሴዎችን ባደረገ ጊዜ ዋና አጀንዳ አድርጎ አንግቦት የነበረው የጸረ-ሽብርተኝኘት ሕጉ እንዲሰረዝ በማድረጉ ላይ ነበር። በወቅቱ የአንድነት ፓርቲን ወክለው፣ ከነሽመለስ ከማል ጋር በጸረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ዙሪያ ክርክር ያደረጉት፣ አቶ ሃብታሙ አያሌውም፣ በይፋ ሕጉ እንደማያስፈልግም መግለጻቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ ግርማ ሰይፉ ራሳቸው፣ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር በጸረ- ሽብርተኝነት ሕግ ስም መንግስት ህዝቡን እያሸበረ እንደሆነም አስረድተዋል። እንደዉም “ሽብርተኞች” እየተባለ ዜጎችን የማሰሩ ጎጂ ተግባራትን “መንግስታዊ ዉንብድና” ብለው ነው ያቀረቡት። እንደዉም ያለማገናን እንደ አንድነት ፓርቲ ይሄ ዜጎችን እያሸበረ ያለውን የጸረ-ሽብርተኝነት ሕግ የታገለ ድርጅት የለም።

ታዲያ ሁኔታው ይሄ ሆኖ እያለ፣ ቅንጣቢ በመያዝ፣ ብዙ ዋጋ በአገር ቤት እየተከፈሉ ያሉ ወገኖች ላይ፣ አሁን ኢሳት እንዳደረገው፣ አክብሮት በጎድለው መልኩ ጠጠር መወርወር የሚያስተዛዝብ ነው። በተለይም ኢሳት አላማው ምን እንደሆነ እንድንገነዘብ እያደረገን ነው። ትግላቸው ጸረ-ወያኔ ነው ቢሉንም ሌሎች ላይም ሳያነጣጥሩ እንዳልቀረም እያየን ነው።

ኢሳቶች በአቶ ግርማ ሰይፉ ላይ ያቀረቡት ከዚህ በፊትም አቶ ሃብታሙ አያሌውም ላይ አቅርበዉት ነበር። “ከአድማጮች የመጡልን ነው” በማለት አቶ ሃብታሙን ወያኔ ነው እስከማለት የተደረሰበትም ሁኔታ እንደነበረም ሁላችንም የምናስታወሰው ነው።

እንደኔ አስተያየት፣ አቶ ግርማ ሰይፉ የተናገሩት ነገር ምንም ስህተት አለው ብዬ አላስብም። ስህትት ሰሩ ቢባልም ደግሞ ብዙ ልንደነቅም አይገባም። ከፖለቲካ መሪዎቻችን ስህተቶች ሲሰሩ፣ ስህተቶችን አርመው፣ ከወደቁበት ተነስተው ጉዞ እንዲጀመሩ መደግፍና ማንሳት እንጂ ማብጠልጠል ነውር ነው። እንዲህ ስል አቶ ግርማም ሆነ ሌላ የፖለቲካ መሪ ተጠያቂ መሆን የለባቸዉም ማለቴ አይደለም። (በቅርቡ የአንድነት መሪ በነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ላይ እና የሰማያዊ መሪ አቶ ይላቃል ላይ ትችቶች እኔም አቅርቤ ነበር) ሆኖም ስንተችና ስንቃወም መረጃ ይዘን መሆን አለበት። ዉይይቶች ከተደረጉ፣ እዉነትን ይዞ፣ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶ፣ በአክብሮት መሆን አለበት። ኢሳት ለነ ዶር ብርሃኑ ነጋ ሰዓታት በየጊዜው ዓድማጮች እስኪሰለቻቸው ድረስ እንደሚሰጥ፣ ለአንድነቶች ወይም ለአንድነት ድጋፍ ድርጅት መሪዎች በቂ ጊዜ ቢሰጥ፣ ምናልባት ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ በሚገባ ሊኖረው ይችል ነበር። ኢሳቶች ግን ያንን አላደረጉም።

ሌላው የአንድነት ፓርቲ የአንድ ግለሰብ ፓርቲ እንዳልሆነም መታወቅ አለበት። አቶ ግርማ ሰይፉ አንድ የፓርቲው አንጋፋ ጠንካራ አመራር ናቸው። ሆኖም አንድነት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ብዙ አባላትና ደጋፊዎች ያሉት ድርጅት ነው። በቅርቡ በመቀሌ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በአዋሳ ጽ/ቤቶቹን በአዲስ መልክ ከፍቶ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ እየሰራ ነው። በመጪው ምርጫ እሳተፋለሁ ብሎ በይፋ አዉጆ የምርጫ ዘመቻውን ጀምሯል። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋዜጣውን አላትምም በማለቱ፣ የራሱ ማተሚያ ማሽን ገዝቶ፣ በር ሲዘጋ ሌላ በር አስከፍቶ፣ መልእክቶቹን ለሕዝብ እያቀረበ ነው።

ታዲያ ኢሳቶች የአንድነት ፓርቲ እንደ ፓርቲ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ያልዘገቡ፣ አንድ የአንድነት አባል ተሳሳተ ብለው በብዙ ሺህ ዶላር የሚያወጣ የአየር ጊዜ ማጥፋት ምን ይባላል ?

ኢሳቶች አቶ ግርማ ሰይፉ ተናገሩት ካሉት በዘለለም አንድነት ለምርጫ እሳተፋለህ ማለቱን እየተቸ በይፋ እየተናገሩ ነው። ኢሳቶችም ሆነ ሌሎች አንድነት ለምርጫ እሳተፋለሁ ማለቱ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው ላይ ችግር የለኝም። የተሻለ አማራጭ ኖሯቸው፣ በአንድነት ፓርቲ ላይ ተቃዉሞ ቢያሰሙ ለምን ሊባሉ አይገባም። ለምን ሲቃወሙ ሌላ አማራጭ በማቅረባቸው። ነገር ግን ምንም አማራጭ ሳይኖራቸው፣ እነርሱም በባዶ ዉስጥ ሆነው፣ በፈታኝ ሁኔታ ዉስጥ ደፋ ቀና የሚሉት፣ እኔ አቶ ግርማ ሰይፉና አንድነቶች ላይ ጠጠር መወርወር ትንሽ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ረገድ ቆም ብለው እንዲያስቡ እመክራለሁ።

በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እምነት ያላችሁ፣ ህዝቡ ከተደራጀና ከተባበረ ለዉጥ ያመጣል የምትሉ፣ የጥላቻና የስሜት፣ የግትርነት ፖለቲካን ሳይሆን የበሰለ፣ የስለጠነ ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያቀፈን ፖለቲካን የምትደገፉ፣ በሁሉም አካባቢዎች ህዝቡ ለፍትህና ለነጻነት ለማንቀሳቀስ ደፋ ቀና እያለ ያለውን ፣ ከሕዝቡ ጋር ያለውን አንድነትን ተቀላቀሉ፣ ደግፉ።

የአንድነት ፓርቲ አንጻራዊ ጥንካሬ ቢኖረውም ብዙ ድክመቶች አሉት። ድክመትን፣ አክብሮት ባለበት መልኩ እየጠቆምን፣ የአመራር አባላቱም ሲሳሳቱ እየገሰጽን፣ ካልሰሙም ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ግፊት እያደረግን፣ ፓርቲው አቅሙን እንዲያጎለበት ማድረግ ነው የሚጠበቅብን። እነ ከበደ ካሳና ኢቲቪ ትንሽ ነገር ባገኙ ቁጥር በአንድነት ልስይ ይጮሃሉ። እነ ሲሳይ አጌናና ኢሳቶች ደግሞ ኢዚያ ትንሽ ነገር ይዘው ብዙ የአየር ሰዓት ፈጅተው፣ አንድነትን በማጥላላት ይፈርጃሉ።

የአንድነት አመራር አባላት ከየአቅጣጫው ቀሥት እንደተመዘዘባቸውም ተርድተው ለነዚህ ቡድኖች ብዙ ቀዳዳ ላለመስጠት እንዲጠነቀቁ አጥብቄ እየመከርኩ፣ “ሥራችሁ ላይ በርቱ” እላቸዋልለሁ: የሚያወራው ፣ የሚተቸው መተቸቱን ዕና ማወራቱን አያቆምምና ለወሬ ቦታ አትስጡ እላለሁ።

በአገር ዉስጥና ከአገር ውጭ ያለን፣ በሚሊዮኖች የምንቆጠር ለዉጥ ፈላጊ ወገኖች፣ በግላችን የድርሻችንን ለመወጣት እንሞክር። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሆን። እኔ አምነት አለኝ እያንዳንዳችን ከተነሳን ለዉጥ ማምጣት እንችላለን። አንርሳ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደ ዜጋ የድርሻቸዉን በአገር ቤት እየከፈሉ ነው። እኛም የድርሻችንን ለመከፈል እንዘጋጅ።

አቶ ግርማ አገዛዙ አፍንጫ ሥር ሆነው በፓርላማ እያደረጉት ያለው ለማወቅ ይችን ያዳምጡ፡

https://www.youtube.com/watch?v=9HffknkPwYw