አመካከት ከዝንጀሮ ተመልከት (ወርቁ ለገሠ)
ይህ የአገራችን ምሳሊያዊ አነጋገር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተለይ ቆላማው ክፍል የሚኖረው ህዝብ ኑሮውንና አካባቢውን ተንተርሶ የቀመረው ብሂል ነው። ዝንጀሮ ድንጋይ ሲወረወርበት ተሸብሮ የሚደናበር ፍጡር አይደለም። መጀመሪያ የድንጋዩን ፍጥነትና አቅጣጫ፣ የወረወረው ሰው አድራሻና ያነጣጠር ችሎታውን በጥንቃቄ ይገመግማል። ድንጋዩ እላዩ ላይ ሊያርፍበት ጥቂት ሴኮንዶች እስኪቀሩ የነበረበትን ቦታ በፍጹም አይቀይርም። መቼም ድንጋይ ድንጋይ ነውና ከሰው ጡንቻና ከመሬት የስበት ሃይል ባገኘው ጥምር ጉልበት ተኩራርቶ በማያገባው የዝንጀሮን ጭንቅላት ሊበረግድ ሲውዘገዘግ ዝንጀሮ በቅጽበት ወዴት ማፈግፈግ እንዳለበት ወስኖ ፎቀቅ ይላል። ይህን ተፈጥሯዊ የሂሳብ ስሌት ስለሚጠቀም የሰው ዕጅ በከንቱ ይዝላል እንጅ ዝንጀሮ በፍጹም በድንጋይ አይመታም። አመካከት ከዝንጀሮ ተመልከት የሚባለው ለዚህ ነው።
ሰሞኑን ደግሞ የአውስትራሊያው ተመራማሪ ዶ/ር ጉተር አመካከት ከዓሣ ዝርያ ተመልከት ይሉናል። በእንግሊዝኛው አጠራር ፓሮትፊሽ የተሰኘው ዓሣ ዕንቅልፍ ሊጥለው ከመቃረቡ በፊት ከስንጥቡ ሥር የሚገኘውን ትልቅ ዕጢ በመጠቀም አንድ ሰዓት የሚፈጅ መረብ እንደ ሸረሪት ድር አድርቶ መኝታውን ያዘጋጃል። ከዚህ ድካም በኋላ ልክ በቀለ ሞላ ሆቴል ስንተኛ የወባ አጎበር ውስጥ እንደምንገባ ሁሉ እሱም እዚህ መረብ ውስጥ ገብቶ ሰላማዊ ዕንቅልፉን ይለጥጣል። እስካሁን ሳይፈታ የቆዬው እንቆቅልሽ ዓሣው በየቀኑ መረብ የመሥራቱን አታካች ሥራ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል የሚፈጽምበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ነበር። መቼም ውቅያኖስ ውስጥ ስለሚኖር ከቢምቢ ለመከላከል አስቦ እንዳልሆነ ለመገመት የሳይንስ ሊቅ መሆን ብሎም መመራመር አያስፈልግም። በተጨማሪ የወባ ትንኝ በፍቅር የወደቀችው ከሰው ደም ጋር እንጅ ለዓሣ ብዙም ሃጃ የላትም። ይሄን ዕንቆቅልሽ ለመፍታት ዾ/ር ጉተር ዕንቅልፋቸውን ሰውተው በውድቅት ሌሊት የሚከተለውን ሙከራ አደረጉ።
ግናቲድ የተባሉ ጥገኛ ፍጡራን መረብ ውስጥና ከመረብ ውጭ የተኙ ዓሳዎችን በውድቅት ሌሊት ጥቃት እንዲሰነዝሩባቸው በሣይንሳዊ ዘዴ አሰማሯቸው። አብዛኞቹ ራሳቸው በፈበረኩት መረብ ውስጥ የተኙት ዓሦች የሠላም ዕንቅልፍ ሲያሳልፉ ከመረብ ውጭ የተኙት ዓሦች ግን እንደተኙ በተሰነዘረ ጥቃት ክፉኛ መጎዳታቸውን ተመለከቱ። በዕንቅልፍ ላይ እያለ ለጥገኛ ፍጡራን የጥቃት ሰለባ እንዳይሆን እንዲህ የዘየደ እንስሳ እስካሁን በዓለም ላይ መኖሩን አልሰማሁም፣ ክስተቱም እጅግ አስገርሞኛል የሚል አስተያዬት ሰንዝረዋል።
ዶ/ር ጉተር ከዚህ ጥናታቸው በመነሳት የሚከተለው መላ ምት ላይ ደርሰዋል። እነዚህ የዓሣ ዝርዮች ይህን መሠል የመከላከያ ብቃት ሊካኑ የቻሉት ምናልባት ለብዙ ዘመናት ሳያሰልስ የተካሄደው የከረረ የአጥፊና ጠፊ ትግል የወለደው ተፈጥሯዊ የመከላከል ሥልት ነው ይላሉ። ይህ አገላለጽ በአዝጋሚ ለውጥ የሚያምኑ ሰዎች ጎራ የሚካተት ነው። የዕምነት ሰዎች ደግሞ “አቤት የሱ ሥራ!” ብለው መደመማቸው አይቀርም። ከሁለቱ ጎራዎች ባንደኛው ላይ መካተት፣ አለዚያም የራስን መላ ምት መተለም ይቻላል። ዋናው ነጥብ ከዚህ ጥናት የምንጨብጠው ቁም ነገር ምንድነው? የሚለው ነው። መልሳችን እንደመልካችንና አመላችን ሊለያይ ይችላል። ሆኖም ግን ጥቃትን የመከላከል ዕርምጃ ግዕዛነ አዕምሮ ባለው ፍጡር አይወሰንም፣ በደመ ነፍስ የሚኖሩ እንስሳትም ይካተቱበታል የሚለው አስተሳሰብ ያስማማናል ብዬ እገምታለሁ።
ቸር ይግጠመን
ወርቁ ለገሠ (11/17/10)
ምንጭ፡ BBC