“በእያሱ ዳቦ ነው ትራሱ”
የልጅ እያሱ ዘመነ-መንግስት በቂ የሆነ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ በመጣሉ የአገሬው ገበሬ ከባድ ምርት ያመረተበት የጥጋብ ዘመን ስለነበር “በእያሱ ዳቦ ነው ትራሱ” የሚለውም አባባል ይህን ጊዜ ለማመስገን የተነገረ መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ዘገባዎች ላይ አንብቤአለሁ። “በዘውዲቱ ፀጉር ይጎትቱ”…”በተፈሪ የለም ፍርፋሪ”… የሚሉትን አባባሎች አመጣጥ ደግሞ በሌላ ጊዜ እነግራችኋለሁ።
ልጅ እያሱ እና ራስ ተፈሪ በመሀከላቸው በነበረው የከረረ ቅራኔ አማካኝነት ሆድ እና ጀርባ ሆነው ጦር ለይተው ብረት መዘው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከአደዋ ጦርነት ቀጥሎ የሚጠቀሰውን ታልቁን የሰገሌ ጦርነትን አንስተው ቢተላለቁም በመሀከላቸው ግን የማይካድ ጥብቅ የሆነ የስጋ ዝምድና ነበራቸው።
የራስ ተፈሪ አባት ራስ መኮንን ከአጤ ምንሊክ ጋር በጋብቻ የሚዛመዱ የቅርብ ዘመድ እና ከልጅነት እስከዕልፈት እንደወንድማማች ሆነው ስለኖሩ ታዲያ አጤ ምንሊክ የልጅ እያሱ አያት የራስ ተፈሪ አጎት ነበሩ ማለት ነው። ይህ ትልቁ ዝምድናቸው ሲሆን የራስ ተፈሪ ባለቤት እትጌ መነን የንጉስ ሚካኤል የልጅ ልጅ ስለነበሩ ልጅ እያሱ ሚካኤል አጎታቸው ነበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ ራስ ተፈሪን እና ልጅ እያሱን አማች ያደረገ ሌላ ዝምድና ነው።
የንግስና ዙፍን ላይ ለመቀመጥ ሲሉ ዝምድናቸውን ጥለው የታጠቀ የጦር ሠራዊት አደራጅተው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚታወሱትን ሁለቱን ታላቅ ጦርነቶች የተዋጉት ሹማምንት በሙሉ ልጅ እያሱ፤ አባ ሹምዬ፤ ራስ ጉግሳ ወሌ እና ራስ ተፈሪ በስጋ የተሳሰሩ ዘመዳሞች ነበሩ።
Lij Iyasu
