ሞት ራስዋ ትደፋ እንጂ ኃይሉ አይሞትም

ከዶ/ር በቀለ ገሠሠ

እጁ ወርቅ ሆኖ አፉ ወለላ
አንደበቱ ርቱዕ እጅጉን የሰላ
አ ቋሙ ጥብቅ አንዴ እማይላላ
አግዜር እያለለት የዘለዓለም ከለላ
የኃይሉ ሞት ወሬ የለዉም አንዳች መላ።

ሞት ራሷ እልም ብላ ትሙት
ኃይሉ አይሞትም ዝም ብላችሁ አትሙት።

በረከተ መርገምን እያድበለበለልኝ
ባለጌን ሊያዋርድ እናትክን በሉልኝ
ወገን ሊያከብር በናቴ እኮ ሴት ነኝ
ተንኮልን ለማጥፋት ቆርጠሃት ጣልልኝ
የቅዱሳንን አጽመ ርስት ርኩሳን አይወስዱብኝ
እያለ ሁሉን ሲጠይቀኝ
የርሱ ሞት ወሬ ፍጹምም አይገባኘ።

አገር ሻጭ እያለ ርካሹ ደላላ
ወገን ገዳይ እያለ ጨካኙ ነፍሰ በላ
ስግብግቡ ሁሉ በቁሙ እየተላ
ኃይሉ ከቶ አይሞት፤ ዘለዓለም ይኖራል ፍቅር እየበላ።

የሞቱትስ አገር ሻጮች
ያለቁትስ የሀህብረ ጠላቶች
ብኩኖቹ የግል ጥቅም አሳዳጆች
በልተዉ አማይጠረቁ አሲዳም ሆዳሞች
ታሪክ የሌላቸዉ ዝቃጭ አረመኔዎች
ናቸው የሞቱት እስከቁመናቸዉ።

በረከተ መርገም ይረግማል እንጂ አይንበረከክም
ገሞራዉ እሳት ነዉ ያጋያል እንጂ እሱ አይሞትም
ነበልባሉ ጠራርጎ አንድም ባንዳ አያስቀርም።

በኢትዮጵያ ምድር ሃቁን መሰከረ
በቻይና መሬት ገዢ አሳፈረ
በኖርዌይ ሳለ እዉነት ተናገረ
በስዊድን ላይ እጅግ አመረረ።

የኔ ጀግና የኔ ከርታታ
ሙሉ ባለታሪክ ሁሉንም የረታ
ዘለዓለም ይኖራል ሁላችን እንበርታ።

የኢትዮጵያ ምድር ምንኛ ጨካኝ ነዉ
እንከፍ እንከፉን ትቶ ሸጋዉን እሚመርጠዉ?

ተናገር አንት ምድር ኃይሉ ምን እንዳለ
መስክሪ ኢትዮጵያ ፀጋዬና ጀግናዉ ሁሉ ከወዴት እንዳለ።

ምን ነካሽ ኢትዮጵያ መርሳቱን አበዛሽ
ገዳዮችሽ እያሉ የሞቱልሽን ረሳሽ
ለም መሬት እያለሽ ተራቡ ሕዝቦችሽ
ያ ሁሉ ወንዝ እያለሽ ተጠሙ ልጆችሽ
ብርቱ ሕዝብ እያለሽ ተደፈረ አገርሽ
ተከላካይ ጠፍቶ ተዋረደ ሕዝብሽ።

ደግ አምላክ እያለሽ እርኩሳን ሲፈሩ
ይሄ ሁሉ ቁጣ ምንድን ነዉ ምስጢሩ?

ምስጢሩስ ቀላል ነዉ ቀድመን አምናቀዉ
ህብረቱ ላልቶ ስግብስግ መብዛቱ
ላገር ጥቅም ሳይሆን ለሆድ መገዛቱ
ይሄ ይመስለኛል ግልጽ ነዉ ትዝብቱ።

እስመ አንተ ኃይሉ ወወልደ ዮሐንስ ካዕላይ
አክበረከ፤ አፍቅረከ ወአኩተከ ብፃይ
ይክበር ወይሰባ ስምከ ዘበምድር ወዘበሰማይ።