የማያለቅስ ልጅ…

  • አባቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ግለሰባዊ ዓምባገነንነትን አልፈቀዱም የቤተ ክርስቲያን አሠራርና አመራር ማኅበራዊና ጉባኤያዊ ነው፡፡
  • ግለሰባዊ አመራር÷ ክሕደትንና ኑፋቄን ለማስገባት፣ ለሌሎች አካላት ቁጥጥር እና ዘመን የፈቀደለት ኹሉ ልቡ የወደደውን በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲጭን ያመቻል፡፡
  • ቤተ ክርስቲያን እንደ መኪና መሪውን የያዘ መኪናውን ወደ ፈለገው ሊወስደው የሚችልባት ቦታ ብትኾን ኖሮ ዘመነ ሱስንዮስን መሻገር ባልቻለች ነበር፡፡

*             *             *

  • የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት÷ በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይና በሊቃነ ጳጳሳት መብት ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ በተነሡ ማኅበራትና ወጣቶች ላይ፣ በየገጠሩ በተሠማሩና የመከራ ገፈት በሚቀምሱ ካህናትና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን በደልና ጫና እየሰሙና እያዩ ዝም ቢሉ በእናታቸው ጀርባ ላይ ኾነው መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ለማስከበር ደግሞ አስቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣንና መብት መከበር አለበት፡፡
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ግለሰባዊ ዐምባገነንነት የሚወስደውን መንገድ በማረም የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ክርስቶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱም የበላይ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መኾኑን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አጽንቶታል፡፡
  • የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በምልአተ ጉባኤያቸው አንድ ኹነው የቅዱስ ሲኖዶሱን ሉዓላዊ ሥልጣን እንዳስጠበቁትና ቤተ ክርስቲያንንም ከግለሰብ አገዛዝ እንደታደጓት ኹሉ ለዘለቄታውም፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረቡትንና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክረው የወሰኑበትን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን አንድ ኹነው ለመፍታት መነሣት አለባቸው፡፡

*             *             *

(የዳንኤል ክብረት እይታዎች፤ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

eotc holy synod fathers

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ በተመለከተ አሰረ ሐዋርያትን የተከተለ ኾኖ እንዲጸድቅ አድርጓል፡፡ አባቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ግለሰባዊ ዓምባገነንነትን አልፈቀዱም፡፡ ጸሎተ ሃይማኖቱም ‹‹ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› በማለት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ዘሐዋርያት መኾንዋን ያመለክታል፡፡ በ፶/፶፩ ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የተሰበሰበችው ሲኖዶስም ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ›› አለች እንጂ ‹እኔ› የሚል ግለሰባዊ ድምፅ አልተሰማባትም፡፡

ኢትዮጵያውያን አበው የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዐት ብቻ ሳይኾን ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን የአመራር ሥርዐቶች ከግለሰብ ዐምባገነንነት ለማውጣት መልካም የኾነ ሥርዐት ሠርተዋል፡፡ ቅዳሴው በአምስት ልኡካን እንዲኾን፣ አጥቢያው በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዲመራ፣ ገዳማት በምርፋቅ(ጉባኤ አበው) ወይም በማኅበር እንዲመሩ፣ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስን አንድ ጳጳስ (ፓትርያርክ እንኳ ቢኾን) ብቻውን እንዳይሰጥ፣ ቢያንስ ሦስት አበው ሊኖሩ እንደሚገባ፤ አንድ አባት ብቻውን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን እንዳይለውጥ፤ አድርገው የሠሩበት አንዱ ምክንያት ግለሰባዊ ዐምባገነንነትን ለመቋቋም እንዲቻል ነው፡፡

ይህን ማኅበራዊና ጉባኤያዊ የኾነ የቤተ ክርስቲያን አሠራርና አመራር ለማስወገድ በየዘመናቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ የዚኽም ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ግለሰባዊ አመራር ለሦስት ነገሮች የተጋለጠ ነው፡፡ የመጀመሪያው፡- ክሕደትንና ኑፋቄን ለማስገባት ይመቻል፡፡ አንዱ ወሳኝ ሌላው ‹ኦሆ በሃሊ› ስለሚኾን እርሱ ትክክል ነው ያለው ትክክል፤ ስሕተት ነው ያለው ደግሞ ስሕተት ይኾናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤያዊት በመኾንዋ አንዳንድ ግለሰቦች በየዘመናቱ ያመጡትን ክሕደት በጉባኤ ተመልክታ በጉባኤ ለማውገዝ ጠቅሟታል፡፡ ደገኛ ትምህርትና ድርሰት ሲገኝ ደግሞ እንዲሁ በጉባኤ ተመልክታ ለመቀበል ረድቷታል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምስጢርን ጽፎ በጨረሰ ጊዜ ጉባኤ ሊቃውንቱ ተመልክተው ‹‹አማንኬ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ወቄርሎስ አፈ በረከት ተንሥኡ በመዋዕሊነ፤ ኢትዮጵያ ተመሰለት በቁስጥንጥንያ፤ ወተአረየታ ላዕለ እስክንድርያ – በእውነት ዮሐንስ አፈ ወርቅና አፈ በረከት የኾነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፤ ከእስክንድርያም ልቃ ከፍ ከፍ ብላለች፤›› ብለው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

ለተኛው፡- ለሌሎች አካላት ቁጥጥር ስለሚመች ነው፡፡ ጌታችን አስቀድሞ ኃይለኛውን ማሰር እንዳለው መሪውን የያዘ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ልቡ ለመዘወር እንደሚመቸው ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይኼ ነገር በዘመነ ሱስንዮስ ጊዜ ታይቷል፡፡ ሮማውያን ግብጻዊውን ጳጳስ በሮማዊ ጳጳስ በመተካት ቤተ ክርስቲያኒቱን በሮማዊ ጳጳስ ለማስመራትና ለመቆጣጠር ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠባይ ማኅበራዊና ጉባኤያዊ በመኾኑ ጉባኤ ሊቃውንቱ ከግብጹ ጳጳስ ጋራ ኾኖ ተቃወማቸው፤ ጳጳሱና ሊቃውንቱም እስከ ደም ማፍሰስ ድረስ መሥዋዕት ኾኑ፡፡

ጥቅምት ፲፱ ቀን ፲፮፻፳፩ ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም በምትገኘው ደብረ መዊዕ የተሰበሰቡት የቤተ ክርስቲያን ማኅበርተኞች ለዚህ ማስረጃ ናቸው፡፡ በዚኽ የደብረ መዊዕ ጉባኤ እስከ 7000 የሚደርሱ ምእመናን፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ሊቃውንት ተሰባስበው ነበር፡፡ የጉባኤው መሪዎችም እነ አባ ተስፋ ኢየሱስ፣ አባ ዘጊዮርጊስ ዘዋሸራ፣ አባ እንጦንዮስ፣ አባ ግርማ ሥሉስ ዘውይት ነበሩ፡፡ የጉባኤው አፈ ጉባኤ ደግሞ አባ ግርማ ሥሉስ ነበሩ፡፡ በዚህ ጉባኤ የተገኙት ኹሉ ንጉሡንና አዲሶቹን ሮማውያን የሃይማኖት መሪዎች ተቃውመው እንደ አንድ ልብ መክረው እንደ አንድ ቃል ተናግረው በተዋሕዶ ጸኑ፤ የንጉሥ ሱስንዮስም ጦር ጥቅምት ፲፱ ቀን ከብቦ ፈጃቸው፡፡

እነዚህ ጽኑአን ጉባኤተኞች ነበሩ በኋላ ዐፄ ሱስንዮስ ሐሳባቸውን እንዲቀይሩና ‹‹ፋሲል ይንገሥ፣ ሃይማኖት ይመለስ›› እንዲሉ ያደረጋቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ መኪና መሪውን የያዘ መኪናውን ወደ ፈለገው ሊወስደው የሚችልባት ቦታ ብትኾን ኖሮ ዘመነ ሱስንዮስን መሻገር ባልቻለች ነበር፡፡

ሦስተኛው ምክንያት፡- ዘመን የፈቀደለት ኹሉ ልቡ የወደደውን በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳይጭን ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ መንግሥታት ለራሳቸው የሚመቻቸው መሪ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማስቀመጥ ሞክረው ነበር፡፡ የቤተ ከርስቲያን አሠራር፣ ሕግና ሥርዐት ግን በአንድ ሰው የሚዘወር ባለመኾኑ ገመዱን ከመበጣጠስ ያለፈ ጀነሬተሩን ማቋረጥ አልተቻላቸውም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎችም በጉባኤ እንጂ በአንድ ሰው ኅሊና ብቻ የሚወሰኑ ባለመኾናቸው አስተዳደራዊ ጥቅም ከማግኘትና በደል ከማድረስ ባለፈ አጥንቷን ለመስበር ዐቅም አላገኙም፡፡

His Holiness Abune Mathias with thier Graces the Archbishops

ይህን ታሪካዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ሐሳብ ጠንቅቆ በመረዳት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ግለሰባዊ ዐምባገነንነት የሚወስደውን መንገድ በማረም የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ክርስቶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱም የበላይ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መኾኑን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አጽንቶታል፡፡


የአገራችን ሰው ሲተርት ‹‹የማያለቅስ ልጅ በእናቱ ጀርባ ይሞታል›› ይላል፤ ይራበው አይራበው፣ ይታፈን አይታፈን፣ ይመመው አይመመው፣ ይመቸው አይመቸው አይታወቅምና፡፡ ምናልባትም ዝምታው እንደ ጨዋነት ታስቦለት ዘወር ብሎ የሚያየው ላይኖርም ይችላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይና በሊቃነ ጳጳሳት መብት ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ በተነሡ ማኅበራትና ወጣቶች ላይ፣ በየገጠሩ በተሠማሩና የመከራ ገፈት በሚቀምሱ ካህናትና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን በደልና ጫና እየሰሙና እያዩ ዝም ቢሉ በእናታቸው ጀርባ ላይ ኾነው መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ለማስከበር ደግሞ አስቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣንና መብት መከበር አለበት፡፡ ያልቆመ አንገት ራስን አይሸከምም እንዲሉ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በምልአተ ጉባኤያቸው አንድ ኹነው የቅዱስ ሲኖዶሱን ሉዓላዊ ሥልጣን እንዳስጠበቁትና ቤተ ክርስቲያንንም ከግለሰብ አገዛዝ እንደታደጓት ኹሉ ለዘለቄታውም፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረቡትንና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክረው የወሰኑበትን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን አንድ ኹነው ለመፍታት መነሣት አለባቸው፡፡