ሰበር ዜና – የቅ/ሲኖዶሱን ልዕልናና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መፃረራቸውን የቀጠሉት አቡነ ማትያስ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› አሉት – ‹‹አባ ማትያስ አላበደም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ›› ሲሉም በማኅበሩ ላይ የጥፋት መመሪያ ዐዋጁበት!
- ጥቂት አማሳኞች በማንጨብጨብ ሲከተሏቸው፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጨምሮ ብዙኃን ጉባኤተኞች በድንጋጤና በተደምሞ አዳምጠዋቸዋል፡፡ ፓትርያርኩ በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንዳሉም አመላካች ኾኗል፡፡
- ማኅበረ ቅዱሳን÷ በጉባኤያት፣ በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ የስብከተ ወንጌል ስርጭት፣ በቅዱሳት መካናት ልማት፣ በአብነት ት/ቤቶችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ድጎማና ሞያዊ እገዛዎች ያከናወናቸው ተግባራት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በስፋት ተዳስሰዋል፤ ጉባኤተኞች ማኅበሩ ላስመዘገባቸው የሥራ ፍሬዎች ደማቅ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ፣ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብሰባ አዳራሽ በተጀመረው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ በረከት እንዲሰጡ የተጋበዙት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› በማለት ‹‹በቁጥጥር ሥር እንዲውል›› ቅስቀሳ እንዳካሔዱበት ተሰማ፡፡
