፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል

03

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የሚካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ ይጀመራል፡፡

ዘንድሮ ለ፴፫ኛ ጊዜ የሚካሔደው ይኸው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ከጥቅምት ፭ – ፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የሚቆይ ሲኾን ከ50 አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ከ800 ያላነሱ ልኡካን ይገኙበታል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ መቀመጫ ከኾነው ከአዲስ አበባ፣ የሀገረ ስብከቱን ተወካዮች ጨምሮ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ምክትል የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት የሚገኙ ሲኾን ከእያንዳንዳንዱ አህጉረ ስብከት ደግሞ የሰበካ ጉባኤ፣ የስብከተ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት፣ የካህናት እና የምእመናን ተወካዮች የኾኑ ስድስት፣ ስድስት ልኡካን እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡