“አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” መስፍን በዙ በስቴት ዲፓርትመንት

ከይማም አባተ

በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ በተለያዩ ኢትዮጵያዊያንን የተመለከቱ ጉባዔዎች፣ ስብሰባዎች፣ ሰልፎችና ሌሎችም ዝግጅቶች ላይ እንደ እርጎ ዝምብ ጥልቅ ማለት ልምድ ያደረገው እራን እንደ ጋዜጠኛና የመገናኛብዙሃን ባለቤት በማቅረብ ለወያኔ አሳፋሪና ወራዳ ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኘው መስፍን በዙ የተባለው ግለሰብ ስቴት ዲፓርትመንት በመገኘት ወያኔን የጠቀመ መስሎት በአንጻሩ ግን የሚጎዳና የሚያጋልጥ ድርጊት ፈጽሟል። ይህንን መሠረት በማድረግ ነው “አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” የሚል ርዕስ  ለዚህ መጣጥፍ የሰጠሁት።

ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ መስፍን በዙ የስቴት ዲፓርትመንት ዕለታዊ ገለጻ ለጋዜጠኞች በሚሰጥበት ቦታ በመገኘት ሴፕቴምበር 29 ቀን 2014 ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የወያኔ ኢምባሲ ውስጥ የደረሰውን ሁኔታ (ማለትም ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በኢምባሲው የድህንነት አባል የደረሰውን የግድያ ሙክራ) አስታውሶ ለወደፊቱ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይደገም የአሜሪካ መንግሥት ኢምባሲዎችን ለመጠበቅ ያሰባቸውን እርምጃዎችና ለደረሰውም ችግር ተጠያቂዎች ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ላይ ለስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ለሚስ ጃን ሳኪ ጥያቄ አቅርቧል።

መስፍን በዙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ደካማ በመሆኑ ለማስተላለፍ የፈለገውን ሃሳብ አስተካክሎ ለማቅረብ ካለመቻሉ በተጨማሪ ከመጠን ያለፈ በመደናገጡና በመርበርበቱ ምክንያት ለመናገር ያሰበውን ሳይናገር ተቃራኒውን ወያኔን የሚጎዳውንና የሚያጋልጠውን ነው የተናገረው። በዚህም መሠረት በአሳፋሪ ሁኔታ “…..ፕሬዝዳንት ኬሪና ሴክረተሪ ኦባማ በማለት፣ፕሬዝዳንት አባማን ከፕሬዝዳንትነት አውርዶ የውጭ ጉዳይ ሴክሬተሪ አድርጎ በመናገሩ በገለጻው ላይ የነበሩትን በሙሉ በሳቅ አስፈንድቆ ቅሌቱንና ውርደቱን ቅሟል።

እኔ እንደሚመስለኝ መስፍን በዚህ ድክመቱና ወራዳነቱ ምክንያት፣ተወግዞ ሥልጣነ ክህነቱ የተሰረዘበት የቨርጂኒያው ታደሰ ሲሳይ እንኳ ንቆት ያባረረውና ለሬዲዮ ማካሄጃ ይከፍልለት የነበረውን ገንዘብ ያቋረጠበት። መስፍን ስራና መተዳደሪያ ስለሌው ከታደሰ ሲሳይ ላይ አጭበርብሮ ብዙ ገንዘብ  ለሴኩሪቲ፣ለአጥር፣ ለሬዲዮና ለተለያዩ ጉዳዮች እንደወሰደበትና የተጣሉበትም ምክንያት የገንዘብ ጉዳይ እንደሆነ ውስጥ አወቆች ይናገራሉ። እኔ ታዲያ የሚገርመኝ እንዴት ነው ታደሰ ሲሳይ እንኳ ንቆ ያባረረውንና አሽቀንጥሮ የጣለውን መጋዣ እንዴት ወያኔዎች ቢቸገሩና ሰው ቢያጡ ነው እነሱ የሚጠቀሙበት? ወይንስ መስፍን ምናልባት ለወደፊቱ ጉርሻ ለማገኘት ይሆናል አለችሎታውና አለሙያው እየተፍጨረጨር ያለው። ሆኖም የታደሰ ሲሳይ ድጎማ ስለቀረበትና የዘኬ ምግብ ስለተቋረጠበት ሰሞኑን ክብደቱ ትንሽ ቀንሶ የታየውና በረባው ባልረባውም ቁጣ ቁጣ የሚለውና የሚርበተበተው።

መስፍን በወያኔ የጸጥታ ሰራተኛ (ዲፕሎማት) ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ ወሬው እንዳይሰራጭና ወያኔ ላይ ትችት  እንዳይቀርበት ማድረግ ሲገባው ጭራሹን እራሱ የግድያ መኩራውን ላልሰሙት ሲያስተጋባ ነበር። በዚህም ጊዜ ነው በገለጻው ላይ የተገኙት ከተለያ የዜና ማሰራጫ የመጡ ጋዜጠኞች በወያኔ ኢምባሲ የደረሰውን የግድያ ሙኩራ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት። አንድ ጋዜጠኛ እንዳሉት “ …ጥይት የተኮሰው ዲፕሎማት ላለመታሰር የዲፕሎማቲክ ከለላ (diplomatic immunity) ተጠቅሟል ወይ? …” በማለት የወያኔን በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ መከፈቱን በጠራና በተስተካከለ እንግሊዝኛ በገለጻው ላይ ለተገኙትና ገለጻውን በቴሌቭዥን፣ በሬዲዮና በድረገጽ ለሚከታተሉ አወጁት። ይህ ሁናቴ ወያኔን የሚያበሳጭና የሚያበግን እንጂ የሚያስደስት ሊሆን አይችልም። ጉዳዩን በዛ ዝግጅት ላይ መስፍን ባያነሳው ኖሮ ማንም ትኩረት የሰጠው ጉዳይ አልነበረም። ስለሆነም መስፍን በዙ ለሰራው ጥፋት ጉርሻ ሳይሆን የቁጣ አለንጋ ከወያኔ ሳይደርስበት አይቀርም።

መስፍን በቋንቋ እጥረት ምክንያት መናገር ፈልጎ ሳይናገረው የቀረው ጉዳይ ከኢትዮጵያ የሚመጡ የልዑካን ቡድን አባላትና በአሜሪካ የሚገኙ  የወያኔ ዲፕሎማቶች ደህንነት አሳስቦኛል ምን መደረግ አለበት በማለት ወያኔን ለመጥቀም ነበር። በጣም የሚያሳዝነው የግድያ ሙኩራ የተደረገባቸው ሰላማዊና ያልታጠቁ ሰልፈኞች ቢሆኑም መስፍን ይከራከር የነበረው የግድያ ሙኩራ ላደረገው ወንጀለኛ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የግድያ ሙከራ ያደረገው ሰለሞን ታደሰ ገብረሥላሴ (ወዲ ወይኒ) በአሜሪካ የፌዴራል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በማግስቱ ተባሯል። መስፍን በዙ ግን በገለጻው ላይ  “… ተኩሱን አስመልክቶ ማንም የታሰረ ሰው የለም፣ ፖሊሶች ነግረውኛል…” በማለት የወያኔን ገበና ለመሸፈን እንደ ጣቃ ሲቀደድ በገሃድ ታይቷል።

ወዲ ወይኒ በሰራው ወንጀል ከአሁን በኋላ አሜሪካን መግባት ያከተመለት ከመሆኑም በላይ ሊገባ እንኳ ቢፈልግ በግድያው ሙከራ ክስ እንደሚመሰረትበት ታውቋል። ወዲ ወይኒ ከሞቀው ወንበሩና ከተደላደለበት የአሜሪካ ኑሮው ተፈንቅሎ ወደመጣበት ወደ ደደቢት ዋሻ መመለሱ ሌሎችም ወያኔዎች የሚያጋጥማቸው ከዚህ የተለየ እንደማሆን አመልካች ነው።

መስፍን  በዙ የተናገረውን እራሱ አስረጅ የሆነውን ቪዲዮ ለማየት እዚህ ላይ ይጫኑ።

http://www.youtube.com/watch?v=wW_FVnzYD4U