ሰንደቅ – አንድነት ሠላማዊ ሰልፍ ጠራ

“ምንም አይነት ደብዳቤ አልደረሰንም”
አቶ ማርቆስ ብዙነህ የአ.አ.ከተማ አስተዳደር
የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ

አንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የህሊና እስረኞችን ለማሰብ በመስከረም 3 እና መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለማድረግ ያሰብኩት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ሊሳካልኝ ባይችልም፣ በመጪው መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም ግን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅጃለሁ ሲል አስታወቀ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ በበኩሉ ከፓቲው የደረሰኝ ደብዳቤ የለም ብሏል።

የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ህዝብ ግንኙነት ባልደረባ የሆኑት አቶ ነዋይ ገበየሁ፤ አንድነት መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም ሊያካሂድ ያሰበውን ሰልፍ በተመለከተ ለሚመለከተው ቢሮ ደብዳቤ ማስገባታቸውን፤ ነገር ግን አሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። «የሚመለከተው ቢሮ ፈቃዱን ሰጠም፣ አልሰጠም የመስከረም 25 ሰልፍ የማይቀር ነው» ያሉት የህዝብ ግንኙነቱ፤ «ለዚህም ቢሮው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቀናል» ብለዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ ምንም አይነት ደብዳቤ ቢሯቸው ፈርሞ እንዳልተቀበለ የሚናገሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ናቸው። አቶ ማርቆስ ሰለጉዳዩ ከሰንደቅ ተጠይቀው «ምንም አይነት ደብዳቤ አልደረሰንም» የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተውናል። ፓርቲው በበኩሉ ከሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ በተጨማሪ ለፍትህ ቢሮ፤ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስና ለሚመለከተው ሁሉ በደብዳቤያችንን በግልባጭ ልከናል ብሏል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም ሰልፉን ለማካሄድ ያቀደው «የአንድነት ንቅናቄ ለህግ የበላይነትና የህሊና እስረኞችን ለማሰብ» በሚል መሪ ቃል በመያዝ ሲሆን፤ በዚህም ስር የፕሬስ ነፃነት መታፈን ጭምር እንደሚነሳ አቶ ነዋይ ገበየሁ ጨምረው ይናገራሉ።

ቀደም ሲል መስከረም 3 ቀን 2007 ዓ.ም በአራት ኪሎ የህሊና እስረኞችን የሚያስብ የሻማ ማብራት ፕሮግራም ለማካሄድ አስበው እንደነበር ያስታወሱት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በመቀጠልም መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም በቀበና አደባባይ ወይም በኤረር ሜዳ የሻማ ማብራት ፕሮግራሙ ሳይሳካ መቅረቱን ይናገራሉ። በመጪው መስከረም 25 ግን ከአንድነት ጽ/ቤት ተነስቶ አቧሬ አደባባይ ላይ በሚጠናቀቀው ሰላማዊ ሰልፍ 100 ሺህ የሚደርሱ አባላት እና ደጋፊዎች ይገኛሉም ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

አንድነት ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ በቀጣይ ቀናት በብሮሸርና በመኪና የታገዘ የቅስቀሳ ጥሪ አደርጋለሁ ቢልም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ በበኩሉ ፈርሜ የተቀበልኩት ደብዳቤ የለም በማለት ሰልፉን እንደማያውቀው አረጋግጧል።