ቋሚ ሲኖዶስ: ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘመናዊው የኹለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት እንዲተከል ወሰነ፤ ለተቋማዊ ለውጥ ባለተስፋዎች የምሥራች፣ ለአማሳኝ ተቃዋሚዎች ኀፍረትና መርዶ ነው!!

Head of EOTC Patriarchate

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

  • ትክክለኛ የቋሚና አላቂ ንብረት ምዝገባና አስተዳደር፣ ተቀባይነት ያለውና እምነት የሚጣልበት የገንዘብ ገቢና ወጪ እንቅስቃሴ፣ ግልጽና ወጥነት ያለው የግዥ አፈጻጸም፣ ብቁ የቁጥጥር ሥርዐት ባለመዘርጋቱ የቤተ ክርስቲያናችን ጥቅል ሀብት አይታወቅም፡፡
  • በማንኛውም ሕጋዊናመናዊ የሒሳብ ምርመራ አሠራር እጅግ ኋላ ቀር በኾነው በነጠላ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ እና በሞዴላሞዴሎች አሠራር የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ እና ንብረት ከብኩንነት፣ ከመዘረፍ እና ከመጭበርበር ለማዳን አልተቻለም፡፡
  • በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ሦስት የበጀት ዓመታት ላይ የተካሔደው የውጭ ኦዲት÷ አጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴያችንና የንብረት አስተዳደራችን በዘመናዊው የሒሳብ ምርመራ ስልት ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለውና ሞያዊ አስተያየት ለመስጠት የማያስችል (Disclaimer of Opinion report) እንደኾነ አረጋግጧል፡፡

double_entry_accounting00

  • የቤተ ክርስቲያናችንን የገንዘብ ዝውውሮች ወጥነትና ተቀባይነት ባላቸው የፋይናንስ ደንቦችና መመሪያዎች ለመመዝገብ እንዲኹም ተአማኒ የኾኑና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ ፋይናንስ ነክ መረጃዎችንና ሪፖርቶችን በወቅቱ ለማቅረብ ያስችላል የተባለው የኹለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት፣ ሀብታችንን በአግባቡ በማስተዳደር ዋናውን ሐዋርያዊ ተልእኳችንን የምናጠናክርበት አቅም እንደሚፈጥርልን ታምኖበታል፡፡
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የቋሚ ሲኖዶሱን የፋይናንስ ፖሊሲ ውሳኔ ለመተግበር በሚያከናውነው ቅድመ ዝግጅት የተመረጡ ሠራተኞች የአጭር ጊዜ የፒችትሪ ሥልጠና እንዲጀምሩ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
  • ለአ/አበባ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተጠንቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ይኹንታና የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበትና የብዙኃን ካህናትንና ምእመናንን ተቀባይነት ያረጋገጠው የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ÷ በኹለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት ላይ ተመሥርቶ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንደሚዘረጋ ለሚጠበቀው ዘመናዊና ወቅቱን የዋጀ የፋይናንስ አስተዳደር ቃለ ዐዋዲ ዝግጅት ደልዳላ መሠረት እንደሚጥል ተመልክቷል፡፡

የዜናውን ተጨማሪ መረጃዎች ይከታተሉ፡፡