አቡጊዳ – ነገ ከሃላፊነቴ ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ አሉ ኢንጂነር ግዛቸው
የአንድነት ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ በአንድነት ራዲዮ ቀርበው፣ በሚሰጡት አመራር ዙሪያ እየተነሱ ያሉ በርካታ ቅሬታዎችን በተመለከተ፣ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። 
ኢንጂነሩ የሚሊዮኖች ንቅናቄ ለጊዜው የተቋረጠው፣ ከመኢአድ ጋር የዉህደት እንቅስቃሴ ስለነበረና ክረምት በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የተቋረጠው እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል አሳስበዋል። ለሚሊዮኖች ንቅናቄ የመሬት ባለቤትነት ዘመቻ የተሰበሰበው ገንዘብም ለተሰበሰበበት አላማ እንደሚዉል፣ ሰላማዊ ሰልፎች ባልተደረጉ ቦታዎች እንደሚደረጉም አረጋግጠዋል።
ከሰባት ወራት በፊት ኢንጂነር ግዛቸው በአንድነት ራዲዮ ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ «እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ አቅማችሁን አጎልብቱና እኔን አሳርፉኝ። ተረከቡኝ» ሲሉ ለወጣት አመራር አባላት ጥሪ ማቅረባቸው ያታወሳል። በዚሁ ቃለ ምልልስም፣ ኢንጂነር ግዛቸው ፣ የስልጣን ጥመኛ እንዳልሆኑ ለማሳየት ሞክረዋል። ወደሃላፊነቱ የመጡት ተለምነው እንደሆነና ነገ ከሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ፍቃደኛ እንደሆኑም አረጋግጠዋል።
የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደትን በተመለከተ፣ ከምርጫዉ በፊት ከመኢአድ ጋር የመዋሃዱ ነገር እንደማይሆን የገለጹት ኢንጂነር ግዛቸው ፣ «የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደት ኮሚቴ ለምን ፈረሰ?» ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ፣ «እኔ የለሁበትም። ያፈረሰው ምክር ቤቱ ነው» በሚል ጣታቸውን ወደ አንድነት ብሄራዊ ምክር ቤቱ አዙረዋል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የአንድነት የምክር ቤት አባላት፣ « የዉህደት አመቻች ኮሚቴዉን እንዲፈርስ አጀንዳዉን ያቀረቡት ፣ በጉዳዩም ላይ ይከራከሩ የነበሩት፣ ኢንጂነር ግዛቸው ራሳቸው ናቸው። አሁን ከሕዝቡ ቅሬታ ሲሰማና በሜዲያ ሲጠየቁ፣ በምክር ቤቱ ማላከካቸው አሳዛኝ ነው» ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
የብሄራዊ ምርጫ ስምንት ወር ቀርቶት፣ በቃለ መጠይቁ እንደታየው፣ በደጋፊዎችና በአባላት ዘንድ ትልቅ ጥያቄ የሚነሳባቸውና ተቃዉሞ እየገጠማቸው ያሉ ፣ እንደ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ያሉ የአመራር አባላት፣ እንዴት አድርገው ደጋፊዉን እና አባላቱን አስተባብረው ለዉጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚጠይቁት ያነጋገርናቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ለስልጣን ጥመኛ እንዳልሆኑ የተናገሩትን ቃል በማክበር፣ ለትግሉና ለፓርቲዉ ሲሉ ሃላፊነታቸው ቢያስረክቡ ጥሩ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።