በበዓል ቀን የርሃብ አድማ ! ርዕዮት ምን ልትነግረን ነው? ዳዊት ሰለሞን

በብሄራዊ በዓላት ቀን በአብዛኛው ከወደ እስር ቤት የሚሰማው ዜና አስደሳች ነበር፡፡ይህንን አጼዎቹ ፣ሰው በላው የደርግ ስርዓትና ብሶት ወለደኝ ያለን ኢህአዴግ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡በዘንድሮው አዲስ አመትም የመንግስትን ይቅርታ በማግኘት ከወዳጅ ዘመዶቻቸው የተቀላቀሉ ስለመኖራቸው ተሰምቷል፡፡በአዲሱ ዓመት ይቅርታ ከተቸራቸው እስረኞች መካከል ታዋቂ ፖለቲከኞች፣አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች አለመኖራቸው ተፈቺዎቹ በደረቅ ወንጀል ታስረው የነበሩ መሆናቸውን ለመናገር ብዙ መድከም አይጠይቅም፡፡

መንገስት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ሂሩት ክፍሌና ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር አቅርበውት ለነበረ የይቅርታ አቤቱታ የእምቢታ ምላሽ መስጠቱም ይቅርታ የሚገባውና የማይገባው በመንግስት ማውጫ ውስጥ ስለ መኖሩ ማሳያ ነው፡፡የይቅርታው ጉዳይ ለጊዜው ይዘግይልንና በጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ላይ በበዓል ቀን ስለ ተፈጸመ ግፍ ላካፍላችሁ፡፡

ጋዜጠኛዋን በበዓሉ ዋዜማ ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ አምርተን ነበር፡፡በመጠየቂያ ሰዓት መድረስ የቻልን ቢሆንም ጥበቃዎቹ ‹‹ርዕዮት የምትጠየቀው በዋናው በር ሆኗል፡፡ስለዚህ ወደ ዋናው በር ሂዱ›› አሉን፡፡ዋናው በር ፈጣን ተራማጅ በ10 ደቂቃ የሚደርስበት በመሆኑ ሰዓቱ እንዳይረፍድና እንዳንከለከል በማለት መሮጥ ጀመርን፡፡

ዋናው በር ግብረ ገብነት አልያም ፖሊሳዊ ስነ ምግባር በዞረበት ለሰላምታ እንኳ አግኝቷቸው የማያውቁ የሚመስሉ ጠባቂዎች ‹‹በዚህ በኩል እስረኛ አይጠየቅም ሂዱ ››አሉን፡፡ግትር ብለን በዚህ በኩል ግቡ ተብለናል አልን፡፡ሰዓቱ እየሄደ ፖሊሶቹም በአቋማችን የበለጠ በመበሳጨት እየዛቱ ነው ፡፡በመካከሉ የርዕዮት ታናሽ እህት እስከዳር አለሙና እጮኛዋ ስለሺ ሀጎስ ከግቢው ውስጥ እየተጣደፉ ወጡ፡፡

ስለሺ አንገቱን አቀርቅሮ እጆቹን እያወናጨፈ ብቻውን ያወራል፣እስከዳርን በሙሉ አይን ማየት ያስፈራል፡፡ ፊቷ በርበሬ መስሎ በእንባ ጎርፍ እየታጠበች ነው፡፡አብሮኝ የነበረው ሰውና እኔ ለመግባት እናደርግ የነበረውን ትንቅንቅ በመተው ሁለቱን ለማጽናናት እና ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ መወትወቱን ተያያዝነው፡፡

ርዕዮት ቤተሰቦቿን እንዳገኘች‹‹ያለሁበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፣ችግር ውስጥ ነኝ››ትላቸዋለች፡፡በዚህ ወቅት በዙሪያዋ የነበሩ ሴት ፖሊሶች ጋዜጠኛዋ ላይ በመጮህ ‹‹ስለ ራስሽ ብቻ አውሪ››ይሏታል፡፡