መነበብ ያለበት ስለ ሃብታሙ የተጻፈ (ዘሪሁን ሙሉጌታ) ክፍል 2

ከክፍል አንድ የቀጠለ

እሁድ (ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም) በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጽ/ቤት ውስጥ የ“አዲሱ ትውልድ ተልዕኮ” በሚል ርዕስ ወጣት ሀብታሙ አያሌውን ገብዘዉት ነበር፡፡ ሀብታሙን በአካል ያየሁት ያኔ ነበር፡፡ ከሀብታሙ ጋር በደንብ የተዋወቅነው ከዚህ ዘገባ በኀላ ነበር፡፡ ሀብታሙን ስሞኑን ሳስታውስው፣ ያኔ በስንደቅ ጋዜጣ ላይ የዘገብኩትን መለስ ብየ አየሁ። እስቲ በጋራ እናነብው ፡፡

ክፍል 2 – “እኔም ብሆን የቃሊቲ እስር ቤት ዕጩ እስረኛ ነኝ”

የፖለቲካ ፍዘቱ ለምን ተፈጠረ?

ወጣት ሀብታሙ ሕዝቡ መብቱን እንዳይጠይቅ፣ እንዲፈራ፣ እንዲሸማቀቅ፣ ኀሳቡን በነፃነት እንዳይገልፅ የሚያደርጉት ገዢዎች በሚፈጥሩት የፖለቲካ ፍዘት ነው ብሏል። ይህ ደግሞ ለአገዛዝ እንዲመቻቸውና የስልጣን ዕድሜአቸውን ለማራዘም እንደሆነም ገልጿል። የፖለቲካ ፍዘት ስትራቴጂአቸውን በተመለከተ ወጣት ሀብታሙ ሲገልፅ፣ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን ባልፈለገበት መንገድ በተለያዩ ሕጎች ቀይዶ ይዞ እያነከሰ እንዲኖር በማድረግ እንደሆነም አስረድቷል።

የመጀመሪያውና ዋነኛው የኢኮኖሚ ተፅዕኖ የተፈጠረው በፖለቲካ ፍዘት መሆኑንም አብራርቷል። የአገርን ኢኮኖሚ ባልተገባ አካሄድ ለራስ ፍላጎት ማዋል ተገቢ አለመሆኑና ለፖለቲካ ፍዘቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው ወጣት ሀብታሙ ያወሳው።

“የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ታላቅነት የሚለካው ሀገርን እንደ ሕዝብ ፍላጎት በመምራት፣ ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ በመሆን የሕዝብን መሠረታዊ ችግሮች በመቅረፍ የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት ቢሆንም፤ በሀገራችን ግን ከዚህ የተለየ ነው። የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ልዕልና በማረጋገጥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕፃን አብዮታዊ ዴሞክራሲ እስኪዘምር የፓርቲውንና የገዢዎቹን ዕድሜ በማስረዘም ላይ ያለመ ነው። አብዮታዊነተን በዘመቻ ለማስፋፋት ኢኮኖሚው እንደመጠቀሚያ ውሏል። በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚውም ጤናማ ባለመሆኑና የሀብት ክፍፍሉም ፍትሐዊ ባለመሆኑ ሁለት ማኅበረሰብ በመፍጠር አንደኛው አብዮታዊ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተብሎ ተከፍሏል” ሲል አስረድቷል።

በፖለቲካ ፍዘቱ ሳቢያ አብዮታውያኑ ለብቻቸው በከበቡዋትና በእነሱ የአጥር ክልል ውስጥ ገብቶ መኖር አስገዳጅ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ሀብታሙ ከአብዮታውያኑ ውጪ ያለ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ ማግኘት ይገባው ከነበሩ ጥቅሞች ሁሉ የተገለለና ከጓሮ ሆኖ የሚቆዝም ነው ብሎታል። “በአብዮታዊነትና በኢትዮጵያዊነት መካከል የተገነባው ግንብ አንዱን በፖለቲካ ፍዘት አጥሮ ሌላውን በአብዮታዊነት እና በገዢዎች ፍላጎት ልክ ያለ የአብዮታውያን ሀገር ሆናለች” በማለት በነፃነትም ሆነ በእድገት መኖር የሚቻለው ለገዢዎች በሚኖር ታማኝነት ልክ ነው ብሏል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዘርፍ ለስራ ዕድል ፈጠራ ለወጣቱ አንድ አማራጭ ቢሆንም፤ ብቸኛው አማራጭ ብቻ ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ያወሳው ወጣት ሀብታሙ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዘርፍ በሕዝቦች የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ብቻ ፋይዳው መመዘን እንዳለበት ገልጿል። ይህ ልምድ በጀርመን፣ በጣሊያንና በፈረንሣይ ኢኮኖሚ ውስጥ ግልፅ ለውጥ ማምጣቱን አውስቷል። ነገር ግን በእኛ ሀገር የእነጀርመን ልምድ ሳይሆን ሕዝቦችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት አብዮታዊነትን እንዲዘምሩና ኢህአዴግ “የልማት ሰራዊት” የሚለውን የስርዓቱ ደጋፊ አካል መፈልፈያ አድርጎታል ብሏል። አብዮታዊነት ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ባሻገር በነፃ ማኅበራትም ውስጥ አብዮታዊ መሆን አስገዳጅ መሆኑንም አውስቷል። በጥቃቅና አነስተኛ ተቋማት የተደራጁትን ወጣቶች በሌላ ነፃ የሲቪክ ማኅበር መደራጀት ፈፅሞ አዳጋች መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ሀብታሙ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ውስጥ እየሰሩ ያሉ ወጣቶች የግድ አብዮታዊ ካባቸውን ለማውለቅ ይገደዳሉ ብሏል፤ በአጠቃላይ የብቃትና የክህሎት መመዘኛ አብዮታዊነት ብቻ እንደሆነና በአብዮታዊነት ልክ የካድሬነት ስልጣንና ሹመት ይሰጣል ብሏል።

በጥቅሉ በዚህ ዘመን ያለው ወጣት ከፖለቲካ ፍዘት ለመውጣት ሦሰት አማራጮች ብቻ እንዳሉት የጠቀሰው ወጣት ሀብታሙ መጀመሪያው በማንኛውም የኢኮኖሚ መስክ ተወዳዳሪ የሆነ አቅም ለመፍጠር አብዮታዊ መሆን ግዴታ መሆኑን፤ ሁለተኛ እራስን ከፖለቲካ አግልሎ በደጋፊነት ስም መስሎ የመኖር አማራጭ ሲሆን ሦስተኛው ያመኑበትን የፖለቲካ አቋም በማራመድ ከውድድሩ መገለልና ለአደጋ መጋለጥ ነው ብሏል።

ከፖለቲካ ፍዘቱ ለመውጣት ግን የሦስተኛውን አማራጭ አደጋ በትከሻው ተሸክም ለመሄድ ማሰብ መጀመር ተገቢ መሆኑንና ኢትዮጵያም ውስጥ መስዋዕትነት የማያስከፍል አንድም ርምጃ የለም ብሏል።ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ተቃውሞ ዋጋ ያስከፍላል ያለው ወጣት ሀብታሙ ትውልዱ ከዚህ የፖለቲካ ፍዘት መውጣት እራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም መክሯል።

ወጣት ሀበተሙ ለፖለቲካ ፍዘት መፍጠር ከኢኮኖሚ ተፅዕኖ ባሻገር የፖለቲካ ምህዳር መጥበቡንም በሰፊው ዘርዝሯል። ሀቀኛ የመድበለ ፓርቲ ስርዓትና የነፃ ተቋማት እንዲያብቡ አለመደረጉን አውስቷል። በመንግሰት በጀት የሚተዳደሩ ነፃ ያልሆኑ የሲቪክ ማኅበራት መኖርን በምሳሌነት አንስቷል። የኢትዮጵያ ታሪክና ወጣቱ በወጣት ሀበተሙ ገለፃ፤ የኢህአዴግ የፖለቲካ አቅጣጫ የሀገሪቱን ታሪክ አዛብቷል። በመሆኑም የተዛባው ታሪክ መታረም አለበት። በዓለም ላይ በተሳሳተ የፖለቲካ አቅጣጫ ሁለት ሆና የነበረችው ጀርመን ታሪክን በሚያርም ትውልድ አንድ መሆኗን፤ ነገም ቢሆን ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪክን በሚያርም ትውልድ አንድ መሆናቸው እንደማይቀር ገልጿል። “ኢህአዴግ የታሪክ ቀበኛ ነው” ያለው ወጣት ሀብታሙ በራሱ በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የትግል መስዋዕትነት ከፍለው ለዘመናት የቆዩ ታጋዮች ከኢህአዴግ በለቀቁ ማግስት ታሪካቸው በሌላ ይተካለ ብሏል።

በመሆኑም ኢህአዴግ ለታሪክ ታማኝ አለመሆኑን አስረድቷል። ጀርመን የሂትለር ሐውልትን ሳታፈርስ ኢህአዴግ የፈጠራቸው ፖለቲከኞች ግን የምኒልክ ሐውልት ካልፈረሰ ብለው ነበር ሲል አስታውሷል። “ኢትዮጵያ የሚባል አስተሳሰብ ሲነሳ እራስ ምታታቸው የሚጨምሩ ገዢዎች አሉን” ያለው ወጣት ሀብታሙ እራሱን ያመመው ሰው ደግሞ የሚወስደው እርምጃ አይታወቅምና እንዘጋጅ ብሏል።

አብዮታውያኑን መቃወም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ደጋግሞ የገለፀው ወጣት ሐብታሙ “እኔም ብሆን የቃሊቲ እስር ቤት ዕጩ እስረኛ ነኝ” ብሏል። “ሕዝቡ የበለጠ አደጋን በመፍራት ዝም ያለ ነው” ሲል የሕዝቡን ዝምታ የገለፀው ወጣት ሀብታሙ “ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ከአብዮታውያኑ አደጋና ሰቆቃ የሚታደገው ሙሴን የሚጠብቅ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ቀድማችሁ ወደ ፖለቲካ የገባችሁ ለሕዝቡ ሙሴ ሆናችሁ ሰፊውን ሕዝብ ለመምራት የተሰጣችሁን ዕድል ተጠቀሙበት “ኮልታፋ ነኝ” ያለው ሙሴ አሮን ይተካሃል ተብሏል። አቅም ያነሳችሁ ካላችሁ አሮን የሚባል እየፈለጋችሁ አስከትሉ” ሲለ ምክሩን ለግሰሶ ነበር