በፈራረሰችው ጋዛ የጨለመው ተስፋ ! * በደም ምድሯ የሚንሰራፋው ጥላቻ! ነቢዩ ሲራክ
ወር በተጠጋው የእስራኤል ጋዛን የማጥቃት ዘመቻ በአሳር በመከራ የተደረሰው የ 72 ሰዓቱ የጦርነት ማቆም ሊያልቅ የቀሩት ጥቂት ሰአታት ብቻ ናቸው። በእስራኤል የአየር የየብስና የባህር ድብደባ ከ1800 በላይ አብዛኛው የጋዛ ንጹሃን ፍልስጥኤማውያንን ተገድለዋል። ከ 9000 የማያንሱትን ቆሰለዋል። በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በሃገራቸው ተሰደው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ጋዛ እንዳልነበረች ሆናለች
ይህ ሁሉ ሆኖ ጦርነቱ እንዲያቆም በተደረሰው የ 72 ሰአታቱ የሶስት ቀን የጦርነት ማቆም ስምምነት በቀጣይ ጦርነቱን ለማስቆም በግብጽ ካይሮ በዋናነት ሃማስና ፋታህን በተሳተፉበት የፍልስጥኤም እና በእስራኤል የጦርነት ማቆም ድርድር የተሳካ አይመስልም። ለአልህ አስጨራሹ ድርድር የመክሸፍ ምክንያቶች ፍልስጥኤማውያን “ጋዛ ከእገታ ትውጣ !” የሚለው ጥያቄ ሲያነሱ እስራኤል በበኩሏ “ሃማስ ትጥቁን ይፍታ !” በሚል የማይሞከር ቅድመ ሁኔታ ተስፋውን አጨልሞታል !
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው የፍልስጥኤምና የእስራኤል ግጭት በተቀሰቀሰ ቁጥር በአቅመ ደካማና በንጹሃን ታዳጊ ህጻናት ላይ የሚያርፈው በትር ልብን በሃዘን እንደሰበረ መሆኑ ውስጥን ያደማል ። በደል ግፉ ባላባራባት የፍልስጥኤም የደም ምድር በጋዛ በሞት የሚቀጠፈው የንጹሃን ነፍስ ፣ አካለ ስንኩል የሚሆነው ግፉዕ ፣ ከተወለደበት ቀየ የሚፈናቀለውን ዜጋ አበሳ ሁኔታ መመልከት ሰላም ይነሳል !
በፍልስጥኤማውያን የውስጥ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ ፖለቲከኞቸ ለሁለት ሲከፈሉ እስራኤሎች ስራውን ሰርተውታልና ያገኙትን እድል ተጠቀሙ ጋዛንና “ነውጠኛ አሸባሪ ” የሚሉትን ሃማስን ከቀረው ቀረው ፍልስጥኤም ጋር ለያዩት ። ወላጅ ከልጅ ፣ ቤተሰብ ከቤተሰብና ፣ ዘመደ ከአዝማዱ በገዛ ሃገሩ ተለያየ ። ፍልስጥኤም በገዛ ሃገራቸው በሰማይ ምድሩ የማያዙ ከመሆን አልፈው በቀያቸው ስደተኛ ሆነው መኖር ግድ አላቸው። መከራቸው በዚህ ቢያከትም መልካም ነበር … ግን አልሆነም ! እውነቱ ይህ ሆነና ትናንትም ዛሬም የሚታየው ሰቆቃ በጨቋኝና በተጨቋኝ “ዝሆኖች ” መካከል የሚደረገው ፍትጊያ ውጤት እልቂት ለመሆኑ ምስክሮች ሆንን ። ምክንያት እየተፈለገ የሚያልቁት የሚፈላለጉት ባላንጣዎች አለመሆናቸው ዛሬም ያሳዝናል …
” ዝሆኖች” በተራገጡ ቁጥር እንደ ሳሩ የሚደቁ ፣ የሚደቆሱ ንጹሃኑ ናቸው:( ይህም የሁለት ኩታ ገጠም እህታማች ሃገራት ንጹሃንን ውሎ አዳር አክፍቶታል። ከራማላህ እስከ ከቴልአቢብ ፣ ከእየሩሳሌም ጋዛና ራማላህ ያልታጠቁ ንጹሃን በስጋት ሽብር ሰለባ ሆነዋል። የአንባጓሮው ውጤት የሰው ልጅ መከራ እንዲገፍት ከማድረግ ባለፈ መገዳደሉ ባተረፈው ጥላቻ እና ቂም ጎረቤቶች በጉርብትና ሊያኖራቸው የሚችለውን ሰላማዊ ቀጣይ ህይወት እየበጠበጠው ይገኛል …
የጋዛ ፍልስጥኤናውያንን አስለቅሶ እያደማቸው ያለውን የእስራኤል ጦር እየተፈታተኑ ያሉት የሃማስ የጦር ክንፍ አባላት በእስራኤል ሰማይና ምደር እያሳዩት ያለው የመከላከል የማይጨበጥ ስልት እና ቆራጥነት እና ብርታት ለደጋፊዎቻቸው የባለድልነት ስሜት ማጫሩ ባይከፋም እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት ንጹሃን በዚህ ደረጃ ያልተገበረበት ቢሆን መልካም ነበር ! ለአንድ ወር እስራኤሎች በከፈቱት መጠነ ሰፊ ጥቃት ግፍ ፈጻሚው ወታደር አፈሙዙን ድረስ ግንባራቸውን እየሰጡ “ግደሉን አንፈራም !” የሚሉ ፍልሰጥኤማውያንን ታዳጊዎች ፍርሃት ሳያበራግራቸው እያሳዩት ያለ ወኔ ግፍ ያመጣው ቢሆንም ቅሉ በዚህ ደረጃ ከታዳጊዎች የሚጠበቅ አልነበረም! … ወደድንም ጠላንም ታዳጊዎች ልበ ሙሉ ሆነው ከአንጋች ጋር የመጋፈጣቸው ሚስጥሩ ፣ ግፍ በዝቶ በውስጣቸው የቋጠሩት ጥላቻ እና በቀል ለመሆኑ ጥርጣሬ የለኝም ። ምስኪን ምንዱባኑ ታዳጊዎች ሰቆቃውን አይተውት ፣ ተነግሯቸው ብሎም አስተናግደውት ሰቆቃው እልኸኛ አድርጓቸዋል ! በደሉ ሲገነፍል ደግሞ እሳት የጎረሰውን መሳሪያ የሚሸሽ ሰብዕና ያጣሉ ፣ ያመራሉ! ወንድም እህታቸውን ፣ ዘመድ አዝማድ ወገናቸውን ከጨረሰው እሳት ጎራሽ ጠመንጃ ከያዘው ወታደር ጋር ጉርቦ ለጉሩቦ ሲተናነቁ አይተናል ! በቃ ህይወት በዚያ ምድር እንዲህ ሆናለች 🙁
እውነቱ ይህ ሆነና ታዳጊው ተምሮ እንዳያድግ አእምሮው በሁለት ወገን ተገድቧል። በእገታ የተገደበው ዜጋ ፣ የመከራ ኑሮን በሚገፋበት ቀየ በነጻነት ታጋዮቹ በውስጥ ለውስጥ የጥላቻ አስተምሮት ተጨምሮበት ጥላቻው ጣራ ነክቷል። በዚህና በዚያ በጥላቻ አድጓልና የፍቅር ፣ የሰላምንና የአብሮነትን ተስፋው ጨልሟል ። ታዳጊው በጥላቻ ውርስ ቅብብል አድጓልና ቀጣዩ መከራ በዚህ ብቻ አያባራም። ፍልስጥኤማውያን ታዳጊዎች ከምሬት ብሶት እንባ ጋር መከራ በደሉን ሲሰሙ ያድራሉ። ከቤቱ ጥላቻ ውርስ አረፍ ሲሉ መገናኛ ብዙሃኑ ይቀበሏቸዋል።
እንደሰማን እንዳየነው መገናኛ ብዙንም ወገንተኛነት ተጠናውቷቸው በየአቅጣጫው ከእሳት ላይ የሚጨምሩት ቤንዚል ለጥላቻው መንሰራፋት ትልቁን ድርሻ መያዛቸውን መታዘብ ለቻለ አሁንም ቀጣዩን መከራ ያሳይ እንደሁ እንጃ … ለታዳጊዎች አስተማሪ ቁም ነገር የተቀላቀለበት ሳቅ ፣ ቀልድ ፣ ጫወታ ፣ ምክር አዘል ምስልና ካርቶን ያቀርቡ የነበሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዛሬ እያቀረቡት የምናየው መረጃ ደስ አይልም። በቅርቡ ” ጥዩር አል ጀና ” በሚል የሚታወቀው ለታዳጊዎች በአረብኛ የሚተላለፍ ዝነኛ የሆነ የልጆች ቴሌቪዥን ፕሮግራም አንድ ያልወደድኩትን ዝግጅት ተመልክቻለሁ። በዚሁ ጣቢያ ተወዳጅ የህጻናት ዘፋኝ ታዳጊ ጃንን የወታደር ልብስ ለብሳ ስለጋዛ ስትዘምር ሲታዩ የነበሩ ምስሎች ተቀነባብሮ በታዳጊዋ መቅረቡን መመልከት ህሊናን ይጎዳል ። በፕሮግራሙ መካከል ለመዝናኛ በሚመስል መንገድ የቀረበው “አብዮታዊ ” መዝሙር የጋዛን ግፍ ለህጻናት ታዳጊዎች በማይመጥን መልኩ ማሳየት ሊፈጥረው የሚችለውን ስለ ልቦናዊ ቀውስና ጥላቻ አውጥቸ አውርጀ አዝኛለሁ 🙁 በዚህም በሉት በዚያ ግፍ እንደ ሰደድ እሳት እየለበለባቸው ያሉ ዜጎቸ መከራ ሳያንስ ለቀጣዩ ትውልድ ጥላቻና በቀል የማወራረስ ይትበሃል በመገናኛ ብዙሃነ በሰፊው ሲሰበከ መስማትና መየት ለህሊና አይመችም…
ላለፉት አስርት አመታት ብቻ ፍጥጫውን ተከትሎ በተደረጉት ሁሉ ጥቃቶች ፍልስጥኤማውያን በእጅጉ ተጎድተዋል ። ከፍልስጥኤሙ የከፋ ሰቆቃ ጋር ባይወዳደርም በእስራኤላውያን ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይም አልፎ አልፎ ከሚደርሰው ጥቃት በባሰ መልኩ በሰላም ወጥቶ መግባት በስጋት ፣ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ልኮ መመለሳቸውን መጠበቅ አሁንም በስጋት ፣ በእረፍት በመዝናኛ ቦታወችና በትራንስፖርት ያለ ስጋት መንቀሳቀስ ዘበት ሆኗል። እርግጥ ነው መደቆሳቸውን ተከትሎ በፍልስጥኤማውያን ልብ ስር እየሰደደ የመጣው የጥላቻና የበቀል አጸፋ በእስራኤል ከተሞች የአጥፍቶ መጥፋቱ ፍንዳታ አሁን እንደ ቀድሞው አይደጋገምም። ያ በር ሲዘጋ ሌላ አደገኛ በር ተከፍቷል። በዚህ ሰአት ጥቃቱ በተወንጫፊ ሚሳኤል የታጨቀው አረር መተካቱን የእስራኤላውያንን እንቅስቃሴ በሽብር ሲያወላክፈው ፣ ጥቃት ድብደባው ዜጎችን ከስጋት ሊያወጣቸው አልቻለም። ይህ ገፊ ምክንያት ሆኖ ዛሬም የእስራኤላውያን ደም እንደ ፍልስጥኤማውያን ባይረክስም በስጋት ተከበው መኖራቸው ግን እርግጥ ነው። ይህ ስጋት በፈጠረው ክፍተት አብረው በሰላም መኖር ያለባቸው የወንድማማች ልጆች መካከል በለየለት ጥላቻ ውስጥ ተዘፍቀዋል። የአንድ ዜጋቸውን የደም ዋጋ በመቶዎች ሳይሆን ሽዎችን የፍለልስጥኤም ዜጎች እያስገበረ ያለው የእስራኤል መንግስትም የሃማስ ታጣቂዎችን የሚሳኤል ጥቃት ለመመከት ጸረ ሚሳየል መከላከያወችን በመደገን ለመከላከል ቢሞክርም እንደ ዝናብ የሚወርደውን የሃማስ ታጣቂዎች የሮኬት ሚሳኤል ጥቃት ሊያስቆመው አልቻለም !
በፍጥጫው የሌሉበት ንጹሃን፣ ህጻናትና ታዳጊዎችን እንደ ገና ድፎ ዳቦ ከላይና ከታች የሚያነዷቸው ” ዝሆኖች ” ትንኮሳ አልቀው የተረፉት ለጥላቻ ዘመቻ ሰለባ ኢላማ መሆናቸው ማየት ያማል። የነገ ሃገር ተረካቢዎች አድገው ሃገራቸውን በሰላም እና በፍቅር ጎዳና እንዳይታደጉ በጥላቻ እየተሰበኩ ፣ በዚህ መልኩ በአለማችን የሁለት ጎረቤት ሃገራት ዜጎች በበቀል እየተጠመቁ የሚገኙበት ከባቢ ቢኖር የእስራኤልና የፍልስጥኤም ምድር ነው ማለት ይቻላል ! በአጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ንጹሃን በእርግጥም ያሳዝናሉ ! እውነቱ ይህ ሆነና ገላጋይ ባጣው በዚህ ቀጠና በቀል ነግሶ ስር እየሰደደ መጥቷል። ይህንን እውነታ በንጹህ ሰብአዊ እዝነ ልቦናውን ለታዘበ መካከለኛው ምስራቅ ከርሰ ምድር ያረገዘው ረመጥ ምጥ መዳረስ ለቀጣዩ አደጋ ምልክት ነው! ” ብሎ ቢናገር ” አናምንም !” እንዳትሉት …የፈራረሰችው ጋዛ የጨለመው ተስፋ እና በደም ምድሯ የሚንሰራፋው ጥላቻ ያሰጋል !
ሰሞነኛውን የሚዘገንን የጋዛን ንጹሃን ደም መፍሰስ ያየ ሰላም ናፋቂ ቀጣዩ ምን ይሆን ? ብሎ መጨነቁ አይቀርም ! ቀጣዩ አስፈሪ ነው!
ብቻ ለጋዛ ንጹሃን ጸልዩ !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ