የመለስ “ትሩፋቶች” – መጽሃፍ ቅኝት
በክንፉ አሰፋ
ደራሲ – ኤርምያስ ለገሰ
ብዛት – 406 ገጾች
አሳታሚ – ነጻነት አሳታሚ ድርጅት
እንደ መንደርደርያ
በስፋት ሲወራለት የነበረውን ይህን መጽሃፍ ሙኒክ-ጀርመን ላይ ገዝቼ ለማንበብ እያፈላለግኩ ሳለሁ፤ አንድ ወዳጄ ይዞት አየሁ። የደበዘዘ የመለስ ፎቶ ያለበትን ይህንን መጽሃፍ የኦስሎው አበበ እጅ ላይ ነበር። ገና ሰላምታ ሳንለዋወጥ ነበር መጽሃፉን ከእጁ ላይ የነጠቅኩት። ታማኝ በየነም እዚያው አብሮን ስለነበር አስተያየቱን ጣል አደረገ። “መነበብ ያለበት መጽሃፍ” እንደሆነ አበክሮ ነገረኝ። ታማኝ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መጻህፍት በሙሉ እንደማያመልጡት አውቃለሁ። በዚህ አዲስ መጽሃፍ ላይ አንዳች አዲስ ነገር እንደሚኖር ከንግግሩ ለመረዳት አያዳግትም።