የዕርዳታ/ስጦታ አሉታዊ ተጽዕኖ – በወርቁ ለገሠ

ዕርዳታ ወይም ስጦታ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜና ቦታ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ነፍስ ሊያተርፍ፣ የወደቀውን መልሶ ሊያቋቁም እንደሚችል ጨርሶ መካድ ጨለምተኛ አመለካከት ይሆናል፡፡ ስጦታ የሚለው ስያሜ የተቀባዩን ልብ ያማልላል። የቅርብ ወዳጃችሁ አዲስ ሀይብሪድ ቶዮታ መኪና ገዝቶ ቁልፉን ቢያስረክባችሁ ወይ ደግሞ እዚህ አሜሪካ ስትመጡ አንድ ጓደኛችሁ ቤት ተከራይቶ፣ የኪስ ሰጥቶ ቢያስቀምጣችሁ ለጊዜው ደሥ አይላችሁም? ውሎ አድሮ ግን በቀረብኝ፣ አሜሪካ ስመጣ እግሬን በሰበረው የሚያሰኝ ክስተት ሊገጥማችሁ ይችላል። ገድሉን በማስመልከት መለኮታዊ ሃይል አላብሰው በሰላ ብዕር የሚጽፉ ብዙ ካድሬዎች አሉት። በርግጥ ስሙና ግብሩ ከተጣጣሙ መለኮታዊ ሃይል የማያገኝበት ምክንያት አልነበረም። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጊዜው ማተኮር የፈለኩት አሉታዊ ጎኑ ላይ ነውና ትዕግስታችሁን ጀባ በሉኝ።

ዕርዳታ/ስጦታ ከጥንት ጊዜ ጀመሮ አሁን እሳካለንበት ክፍለ ዘመን ቅርጹ ይለያይ እንጅ የሰው ልጆች እንደ ባህልና ወጋቸው ሲጠቀሙበት ይታያል። የዓላማውን ውስብስብነትና ረቂቅነት ተገን በማድረግ ለጋሽ ተቀባይን በቀላሉ የሚያጠቃበት መሣሪያም ሆኖ እንዳገለገለ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ በጥንት ጊዜ ህንዶች ባላንጣ ዘመዶቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ለማጥፋት ጦር ሰብቆ ከመዋጋት ይልቅ ስጦታ ፍቱን የብቀላ መሣሪያ መሆኑን ፈትሸውታል። ነገሩ እንድህ ነው። በጣም የጠሉትን ባልንጀራ፣ ጎረቤት ወይም ቤተዘመድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ላሞች በስጦታ ያበረክቱለታል። ይህ የፈረደበት ተቀባይ ብዙ ጊዜ በኢኮኖሚ ከለጋሹ የኮሰሰ ነው። ይህ ሰው ስጦታውን ስልቅጥ አድርጎ ቁጭ እንድል በወቅቱ የሚኖረው ባህልና ወግ አፈቅድለትም። በስጦታ መልክ መመለስ ይኖርበታል። 1000 ጥገቶች ተሰጥቶት 1000 መመለስ ደግሞ አንገት ማጣት ነው። ከፍ አድርጎ መስጠት በህብረተሰቡ ባህልና ወግ አንቱ የተሰኘ ከበሬታን ያጎናጽፋል። ስለዚህ የሚያርስበት በሬ ሳይቀር ሙጥጥ አድርጎ ይከፍልና ድህነቱ ሲጠናበት መኖር አለበትና በጣት በሚቆጠሩ ዓመታት የጎረቤቱ ወይም የቅርብ ዘመዶቹ ግብረበላ ይሆናል። ጠላቱ በስጦታ መልክ  ተበቀለው ማለት ነው። ሌላው ሊወስደው የሚችለው አማራጭ ዓይኑ በጨው እጥብ አድርጎ ስጦታውን ሳይመልስ መቅረት ነው። ይህም በጎ አማራጭ ሆኖ አይገኝም። ህብረተሰቡ የፈሳች ዝንጀሮ ያደርገዋል። በተጨማሪ ስጦታውን ባለመመለሱ የለጋሹን ፊት ቀና ብሎ ለማዬት ያፍራል። ይህ በሚያስከትለው የስነ ልቦና ቀውስና በሚፈጠረው የበታችነት ስሜት ባላንጣው አድርግ የሚለውን ሁሉ ሳያጉረመርም ይፈጽማል፤ አወዳደቁም አያምርም።

አሁን ካደጉ አገሮች የሚሰጥ ዕርዳታ ይዘት ጥንት ህንዶች ከሚጠቀሙበት በይዘቱ ይለያል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው። አይለይም። ለምሳሌ አገራችንን። በዓለም ከፍተኛውን ዕርዳታ ከሚቀበሉ አገሮች አንዷ ስትሆን ጥርስ ያወጣ ድህነት የሰፈነባቸውን አገሮች ሃይሌ ገ/ሥላሴ ሯጮችን እንደሚያስከትለው እየመራቻቸው ትገኛለች።  ይህ በተነሳ ቁጥር ከመሪዎቿ በስተቀር የህዝቦቿ ሞራል ስብር፣ መንፈሳቸው ሽምቅቅ ይላል። ለዚህ ነው አብዛኛው ሰው አጋጣሚ ቢያገኝ አገሩን ለቆ መሰደድ ዝግጁነቱን የገለጸው። በሀ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሆነ ከዚያ በፊት ይህ ለኢትዮጵያውያን የሚዘገንን ዕርምጃ ነበር። አሜሪካና አውሮፓ የሚሰጡን ከፍተኛ ዕርዳታ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ እንድንሄድ፣ እንደካሮት ቁልቁል እንድናድግ አድርጎናል። በገንዘብ ሊተመን የማይችል ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበታል። ሌሎች ጥቃቅን ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በ ኤርትራና ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ዕልቂት፣ የሶማሊያ ጦርነት፣ በአገሪቱ የተንሰራፋው አምባገነን ሥርዓት ከዕርዳታ ጋር ባለን ንክኪ ምክንያት የከፈልናቸው ውድ ዋጋዎች ናቸው።

ታዋቂው እንግሊዛዊ ባዮሎጅስት ሪቻርድ ዳውኪንስ ሰልፊሽ ጅን በተሰኘው መጽሃፋቸው የሌሎችን ደህንነት ለመጠበቅ የራስን ህይወት እስከ መሰዋት የሚደርሱ  ሰዎች አሉ የሚለውን ፍልስፍና የጎሪጥ ይመለከቱታል። ለምሳሌ ይላሉ፡ ወፎችን የሚያጠቃው ጭልፊት በሰማይ ሲያንዣብብ የተመለከተች ወፍ መጣላችሁ የሚል ድምጽ በማሰማት ሌሎችን የመታደግ ብሎም የራሷን ህይወት አደጋ ላይ የመጣል ዕርምጃ ትወስዳለኝ የሚለው ርዕዮት ለሳቸው የዋህ አስተሳሰብ ነው። እንዲያውም ይላሉ የሞት አደጋ ሊያስከትል የሚችለው ጭልፊት ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ ያልተነገራቸው ወፎች በመደናገጥ ግማሾቹ በአጋጣሚ ወደሱ በመብረር ሳያስቡት መስዋዕትነት የሚከፍሉት እነሱ ናቸው። አቅጣጫው ከዬት እንደሆነ መጀመሪያ የለየችው ወፍ ግን ትክክለኛ በረራ በማድረግ ለመትረፍ ያላትን ዕድል ታሰፋለች ይላሉ።

ከፖለቲካ ነጻ ናቸው ብለን የምንገምታቸው የምግባረ ሠናይ ድርጅት ሰዎችም ሆኑ ሳይንቲስቶች ራሱ የሚያደርጉልን ስጦታ ከራሳቸው ወይም ከሃገራቸው ጥቅም አኳያ እንጅ  በዋናነት ከኛ ደህንነት አኳያ የሚመነጭ አይደለም፡፡ የዓለም ከበርቴው ቢል ጌት ሲረዳን የዜና አውታሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሩ አሃዝ ከነሳንቲሙ ተጠቅሶ፣ የሱና የውድ ባለቤቱ ሥም በክብር መዝገብ ላይ እንድሰፍር ተደርጎ ነው። ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ ካደረገ ተመራማሪዎቹ ከሚያገኙት የኪስ ገንዘብ በተጨማሪ የሚታተመው የምርምር ውጤት ለተመራማሪዎቹ የደረጃ እድገት፣ ለዩኒቨርሲቲው ደግሞ የገቢ ምንጭ እንድሆን ታስቦ ነው። አንድ ፕሮፌሰር ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን የውሃ ማቆርና የደን ልማት ዕንቅስቃሴ ሪፖርት አስመልክቶ ለመሆኑ የትግራይ መሬት እንደገና የሚለመልም ይመስልሃል? ብሎ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ የሚገርምም የሚያስደንቅም ነበር። ትግራይ አትለመልምም ነው ያለው። ታዲያ ይህ ሁሉ ንብረትና ውድ ጊዜ ለምን እንድባክን ወሰናችሁ? ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ከፍተኛ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥልጣን የተያዘው በትግሬ ነው። አንድ የዕርዳታ ፕሮጀችት  ትግራይን ማዕከል አድርጎ ከተቀረጸ ለመጽደቅ ያለው ዕድል መቶ በመቶ ነው ሲል ምሬቱን ገልጿል።  እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ቁም ነገር አንድ ፕሮፈሠር የማይምንበትን ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባር ላይ እንዲያውል ያስገደደው ምስጢር ምንድነው? የሚለው ሲሆን ከዕርዳታው በስተጀርባ ሌላ ተልዕኮ መኖሩን ነው።

 ቻይናና ህንድን ብንመለከት በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ በወቅቱ አንቱ የተሰኙ የኢኮኖሚ ጠበብቶች ከህዝባቸው ብዛትና ከድህነታቸው መጠነ ሰፊነት የተነሳ ለነዚህ አገሮች ዕርዳታ መስጠት ጣዕራቸውን ማራዘም ስለሚሆን መርዳት አያስፈልግም የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ ዕርዳታ እንድቀንስ ሞክረዋል። እነዚህ አገሮች በአደጉ አገሮች ብያኔ ሳይደናገጡ ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራት በተለይ ቻይና ወሳኝ የዓለም ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ያረቀቅኩበት ብዕር፣ ያደረኩት ዓይነ ርግብ፣ የለበስኩት ፒጃማና ቁርስ የበላሁበት ሹካ የተፈበረከው በቻይና አገር ነው። ዕርዳታ በገፍ የሚጎርፍላቸው የአፍሪካ አገሮች ግን አሁንም የልመና እጆቻቸውን እንደዘረጉ ናቸው።

ላሳጥረው። ዕርዳታ/ስጦታ ከበጎ ጎኑ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ይጎላል የሚለውን አስተሳሰብ አራምዳለሁ። የዕድል ነገር ሆኖ እኔም ሆንኩ እናንተ በስጦታ አዟሪት ውስጥ ወድቀናል። ውጭ አገር አፈር ግጠን ካገኘናት ዶላር/ዩሮ ላይ ቆንጥረን ወደአገር ቤት የምንልከው ዕርዳታ/ስጦታ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ተግታችሁ ጸልዩ።

ቸር ይግጠመን።

 ወርቁ ለገሠ 10/23/10