አይ አማርኛ…
የታሪክ ጎማ ሲሽከረከር አልባሌ ውድቂያን ወድቀው ያው ታሪክ በድድ (ጥርስ አልባ) የሳቀባቸው አእላፍ ናቸው። የታሪክ አተላ የሆኑት እንዚህ ቀጣፊዎች የቆየና በቅርብ የፈጠሩትን የታሪክ ቡትቶ ተላብሰው የቅጥፈት ስራቸውን ተያይዘውታል። ሰው መግባባት እንዳይችል ሃገርን በክልል ፈርጀውታል። አማርኛ ቋንቋም የዝግታ ሞት እንዲሞት መቃብሩን መሰውለታል። ይሁን እንጂ አማርኛው አዳዲስ ቃላቶችን እያከለ፤ አሮጌውን እያደሰ፤ በጣም ያፈጅና ያረጅ ቃላቶችን ጭራሽኑ እያስወገደ ጎሳን፤ ዘርንና ሃይማኖትን ሳይተግን ያሻ ሁሉ ይገለገልበታል።
ያለፉና ያሉ መድበለ ጽሑፍ አቅራቢዎችም በድንቅ ሁኔታ ተጠቅመውበታል፤ ይጠቀሙበታልም። እውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ – ኦሮማይ በተሰኘው መጽሐፉ እንዲህ ብሎን ነብር።
ህንጻው ምን ቢረዝም ምን ቢጸዳ ቤት
መንገድ ቢሰፋ፤ ቢንጣለል አስፋልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድን ነው ውበቱ።
ይህ ጌዜ የማይሽረው አባባል ነው። የተሰመረበት ቃልም ድርብ ትርጉምን ይዝዋል። አማርኛ በስላቅ መሸንቆጥን፤ በሰምና ወርቅ ቁም ነገር ማስተላለፍን፤ በተምሳሌና በቅኔ በሌሎችም ዘይቤዎች እንደልብ ሃሳብን ለመግለጥ የመገልገያ መሳሪያ ነው።
ተመኘ ቢጨንቀው የሚያዘንበው እንባ
ጎርፍ ሆኖ ቢያደርሰው ካለመኖር አምባ። (የብርሃን ፍቅር – ደበበ ሰይፉ)
ጸጋዬ ደግሞ እንዲህ ይለናል።
ያየር ያድማሳት ገምራው ያ እንደ ጋሬጣ የሾረ
ርቱዕ-ጥፍሩ የነፈረ (እሳት – ጸጋዬ ገብረመድኅን)
አማርኛን እናጠፋለን ብሎ መገመት ነቀዝ እንደበላው እህል መቅለል ነው። ይልቅስ ከራስና ከሃገር ጋር እርቅን በማውረድ አብረን እንገልገልበት። ለምንፈራው ተረግጠን፤ የምንደፍረውን ረግጠን የምንበላው እንጀራ ይቅርብን። አማርኛ ቋንቋም በሃገርና በውጭው አለም እያደገ ነውና መገታት አይቻልም። ቋንቋ መግባቢያ ነው። ለዛም ይመስለኛል ትላንት በአማርኛ ስናናግራቸው በቁጣ ይነድ የነበሩ ዛሬ በፍቅር የሚያናግሩን። እንደሚያልፍ የሃገራችን ጎርፍ ፓለቲካ የሚሽከመው ዝባዝንኬ ነገር በዙ ነው። እውን የሆነውንና ለሁሉ ብርሃን ሊሰጥ የሚችለውን “የነፃነት ጧፍ” በመጨበጥ ወደፊት እንራመድ።
ዘመን አመጣሽ አሻጥር
ባንድ ክልል ማመን፤ ባንድ ነገድ
በኢትዮጵያ መነገድ ለማትረፍ
እኔ ለኔ ሌላው ይርገፍ። (የተጉዋጎጠ ልብ – ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው)
ባጭሩ ዛሬ በዛት ያላቸው መጽሃፍትና የሙዚቃ ውጤቶች በየጊዜው ገብያ ላይ ይቀርቡልናል። እንግዛቸው፤ እናንብ፤ እንናዳምጥ፤ እናበራታቸው የሰራቸውን ፍሬ ቀምሰን ገምቢ ምክርን እንለገሳቸው። ዝልፊያና ስድብ ይቅር። የአማርኛ ቋንቋም ሂደት ይምዘገዘጋል። እኛው በእኛው ለእድገቱ አስተዋጾ እናርግ።
“ከእንግዲህ ወዲህ ወደ ነበርንበት ባርነት የምንመለስ ከሆነ ግን አሁንም በልወለድ ሌላው ኢትዮጵያዊም ባይወለድ በተሻለ ነበር”። ”ግን ተስፋ አንቁረጥ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ሁነን ተወልደናልና” (አልወለድም – አቤ ጉበኛ)
የአማርኛ እድገት ይቀጥላል። አይ አማርኛ እንዳበጅሽ ተበጃለሽ ነውና ሚስጥሩ የሚወድ ይገለገልባታል። ለዛሬው ይብቃኝ።
ሰንበተን እንይ!!
አደፍርስ ተሰማ
ከሚኒሶታ