አቡጊዳ – መኢአድ፣ የአንድነት እና መኢአድ ዉህድ ፓርቲን ለመምረጥ እጩዎች ስማቸውን እንዲያቀርቡ ጠየቀ

በቅርቡ ከአንድነት ጋር ዉህደት ይመሰርታል ተብሎ የሚጠበቀዉ መኢአድ ፣ የዉህዱን ፓርቲ ለመምራት እጩ መሆን የሚፈልጉ የድርጅቱ አባላት፣ ስማቸዉን እንዲያቀርቡ፣ የመኢአድ የዉህደቱ አመቻች ጉባኤ አሳወቀ።

ከቀረቡ እጩዎች መካከል መኢአድ በድርጅቱ ልማዳዊ በሆነው አሰራር መሰረት፣ የመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ፣ መኢአድን ወክሎ ለዉህዱ ፓርቲ ተወዳዳሪ የሚሆነውን አንድ እጩ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥም እጩዎች መቅረባቸው ይታወቃል።

የመኢአድን የዉህድት አመቻች ጉባኤ መግለጫን እንደሚከተለው አቅርበናል፡
==============================================

ለመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)

ለላዕላይ ምክር ቤት አባላት በሙሉ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ውህደት ለመፈጸም አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመመሥረት በሂደት ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት በአዘጋጁት የውህደት ሰነድ ላይ ከመኢአድ አንድ እንዲሁም ከአንድነት አንድ ኘሬዝዳንታዊ እጩ ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት የተመረጠው ግለሰብ የውህዱ ፓርቲ ኘሬዝዳንት ይሆናል፡፡
ስለሆነም በመኢአድ በኩል ለዚህ ውድድር መቅረብ የሚፈልግና በስምምነቱ ሰነድ ላይ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟላ የመኢአድ የላዕላይ ምክር ቤት አባል የሆነ ማመልከቻውን በአምስት ቀናት ውስጥ ለፓርቲው የውህደት የአመቻችና ጉባዔ ጠሪ ኮሚቴ ማስገባት የሚችል መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
የውህደት አመቻችና ጉባዔ ጠሪ ኮሚቴ