ፍቅርን፣ ሰብአዊነትንና ተፈጥሮን ያከበረ፡- የጉዞ ማስታወሻ ክፍል -፩- በፍቅር ለይኩን
ዕለተ ሰንበት ቅዳሜን ‹‹ከአፍሪካ ፒስ ኤንድ ግሪን ኢንሼቲቭ›› አገር በቀል ድርጅት መሥራች፣ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ወደ ጥንታዊውና ታሪካዊው ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ ተጉዤ ነበር፡፡ የጉዞው ዓላማም ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ወንድማማችነትንና የአረንጓዴ ልማት/ተፈጥሮን የማፍቀርንና የመንከባበከብ ጽንሰ አሳብን በሰዎች አእምሮ ውስጥ የመዝራት ቅንና በጎ እሳቤ የወለደው ነው፡፡
ለሰብአዊ ፍጥረት ሁሉ ፍቅርና ሰላም እጅጉን አስፈላጊው እንደሆነ አንዳች ጥያቄ የለውም፡፡ እናም ጉዞአችን ሕይወት ላለው ፍጥረት ሁሉ የህልውና መሠረት የሆነችውን እናት ተፈጥሮን ማድነቅ፣ መጠበቅና መንከባበከብ የሁላችንም ኃላፊነትና ግዴታ እንደሆነ ማስተማርንና መሳወቅን ግቡ አድርጎ የተነሣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ሰብአዊነትንና ተፈጥሮን ያስቀደመና ያከበረ ጉዞ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይህ ጉዞ እግረ መንገዱንም የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች መንፈሳቸውን ዘና በማድረግ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ንጹሕ አየርና ልምላሜ ጋር በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ቆይታን እንዲያደርጉ ለማድረግም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ ጉዞ ነው፡፡ በእርግጥም ሰላም፣ ፀጥታና የመንፈስ መረጋጋት ለራቀው፣ ከጠዋት እስከ ማታ ሩጫና ድካም ከሚበዛበት የከተማ ሕይወት ለአፍታም ቢሆን ተገልሎ ከተፈጥሮ ጋር እየተጫወቱና ተፈጥሮን እያደነቁ መንፈስን ለማረጋጋት፣ ከራስ ጋር በፀጥታ ለመነጋገርና የጽሞና/የግል ጊዜ ለማግኘት እንዲህ ዓይነት ጉዞዎች ጠቃሚነታቸው አሌ የማይባል ነው፡፡
ሸገርንና ተወዳጇን ቅዳሜን ከአድናቂዎቿና ከወዳጆቿ ጋር በአንድነት ‹‹መልካም ቀን!›› በሚል የመልካም ምኞት ቃል ተሰናብተን በቦሌ ቀለበት መንገድ፣ በኬንያ ኤምባሲ፣ ሾላ አልፈን በስድስት ኪሎ ወደ አዲሱ ገበያ አድርገን ነበር የጉዞአችንን መዳረሻ ወደሆነው ወደ ደብረ ሊባኖስን ያመራነው፡፡ የእኛይቱ ሸገር አዲስ አበባም ገና በማለዳው በሰውና በመኪና ብዛት ትርምስ የተነሣ ሸክም የተጫናት፣ ቀንበር የከበዳትና ጭንቀት ያሰጠማት መስላለች፡፡
የእቴጌ ጣይቱዋ አዲስ አበባ፣ የእኛይቱ ሸገር ለአዲስ ሙሽርነት፣ ለአዲስ የውበት ዳግም ትንሣኤዋ የፍርስራሽ ክምር እስከ አንገቷ አጥልቋታል፡፡ የባቡሩ መንገድ፣ አዳዲስና የማስፋፋያ የመንገድ ሥራዎች፣ እዚህም እዛም በከተማይቱ እምብርት የሚታዩት የሕንጻ ግምባታዎች የሸገርን መፃኢ ብሩህ ዘመን የሚያበስሩ ይመስላሉ፡፡ በእርግጥም አዲስ አበባ ልማት ወይም ሞት ያለች ነው የምትመስለው!!
አዲሱ ገበያን አልፈን ጉለሌ ቦታኒካል ጋረደን ስንደርስ ከመካከላችን አንዱ ወዳጃችን ስለዚሁ ቦታኒካል ጋርደን ጥቂት ማብራሪያ ሊሰጠን ሞከረ፡፡ በቅርቡም አሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጂም ኬሪ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በዚሁ ጋረደን አሪፍ ቆይታ እንዳደረጉም ይኸው ወዳጃችን ጨምሮ ተረከልን፡፡ በቅርቡም ይህን ድንቅ የሆነ የተፈጥሮ ገነት ውብ ተምሳሌት እንደምንጎበኘው ለራሳችን ቃል ገብተን ከአፍታ የጉለሌ ቆይታችን በኋላም ጉዞአችንን ወደ ሰብረ ሊባኖስ አደረግን፡፡
በጉዞአችንም ለጥ ያለውን ሜዳና፣ የእርሻ ቦታዎችን፣ ባሻገር የሚታየንን የተፈጥሮን ውበት ባሻገር እየታዘብን በፍጥነት ከሚነጉደው የመኪናችን ፍጥነት ጋር ስለ ጉዞአችንና አልፎ አልፎም ደግሞ የየግል ጨዋታዎቻችን እያወጋን ሸገርን እየራቅናት ሄድን፡፡ ሱሉልታን፣ ሙከጡሪን፣ ሰላሌን፣ ደብረ ፅጌንና ሌሎች ትናናሽ ከተሞችን አልፈን ወደ ጉዞአችን መዳረሻ ወደ ደብረ ሊባኖስ ተቃረብን፡፡
እንደማስታውሰው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነበር ዳግመኛ ደብረ ሊባኖስን ለማየት ይህን መልካም የሆነ አጋጣሚ ያገኘሁት፡፡ ወደዚህ ጥንታዊ ገዳም ስንቃረብ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ያነበብኩት ፖርቹጋላዊው ቄስ አልቫሬዝ በጉዞ ማስታወሻው ስለ ደብረ ሊባኖስ የተረከው መሳጭ ትርክቱ ታወሰኝና ፭፻ ዓመታት ገደማ ወደኋላ በዓይነ ሕሊናዬ ተጉዤ ስለ ደብረ ሊባኖስ ማሰብ፣ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡
ፖርቹጋላዊው ተጓዥና፣ ሚሽነሪና መምህር ቄስ አልቫሬዝ በዛ ዘመን ደብረ ሊባኖስ በአገሪቱ ካሉ ገዳማት መካከል ታላቅና እጅግ የተከበረ፣ በደኖች የተከበበ፣ የታላላቅ መንፈሳዊ አባቶችና ሊቃውንት መናኸሪያ፣ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የቅኔ፣ የዜማ፣ የሥነ ምግባር፣ የሕግ፣ የፍልስፍና እና የሌሎችም እውቀቶችና ጥበቦች ማዕከል እንደሆነ ነበር በልዩ አድናቆት የገለጸው፡፡
ዛሬ ያ ጥቅጥቅ ያለ ደን የለም፣ ከተሜነትና ዘመናዊነት ደብረ ሊባኖስን ቀይሮታል፡፡ ግና እነዛ ዓመታትን ያስረጁ፣ ግርማ ሞገሳቸው እጅጉን የሚያስደምመው ገዳሙን የከበቡት ባሻገር የሚታዩት ተራራዎችና የተፈጥሮ ደን ውበት ዛሬም ሕያው ነው፡፡ ከእነዚህ ውብ ተራራዎችና ልዩ የተፈጥሮ ትንግርትና ተአምር ጋር በመፋጠጥ ሰውነት ሁሉ ዓይን ይሆናል፡፡ ከገዳሙ ተፈጥሮአዊ ውበትና ፀጥታ ጋር ለአፍታ በፍቅር ይወደቃል፡፡ ነፍስም በለሆሳስ ልዩ በሆነ ቋንቋ ከተፈጥሮ ጋር መነጋገር ትጀምራለች፡፡
ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት በዚህ ገዳም ውስጥ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮት፣ የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ለአፍታ ሳያጓጓቸው ሁለተናቸውን ለፈጣሪ አደራ ሰጥተው፣ ግርማ ሌሊቱን ጠብ አጋንቱን ታግሠው ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን፣ ጽዮንን ተስፋ አድርገው ታላቁን መንፈሳዊ ተጋድሎ በድል የፈጸሙ አባቶችና እናቶች በየተራ በአእምሮ ጓዳ ይከሰታሉ፡፡ እነዚህ ለፍቅር፣ ለእውነትና ለፍትሕ የተጋደሉ መንፈሳዊ አርበኞች ፍቅራቸው፣ ትሕትናቸው፣ ትዕግሥታቸው፣ ጽናታቸው፣ እስከ ሞት ድረስ ሣይቀር የታመኑለት ወንጌል ድል ነስቶ ታላቅ እምነታቸው በፍቅር ተውቦ፣ አሸብርቆና ደምቆ ይታያል፡፡
ደግሞም በዚህ ጥንታዊ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ ለእናት አገራቸው ክብርና ነፃነት ክቡር ሕይወታቸውን የከፈሉ፣ በፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮችና ባንዳዎች መትረየስ አረር ያለ ርኅራኄ የታጨዱ፣ እናት አገሬ፣ እምዬ ኢትዮጵያ ‹‹ብረሳኝ ቀኜ ትርሳኝ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ!›› በሚል ጽኑ ማሕላ ቃል ታስረው፣ የእናት ምድራቸውን፣ የሕዝባቸውን ፍቅር በልባቸው እንደተሸከሙ፣ በክህደትና በአድር ባይነት መንፈስ ሕሊናቸውን ሳያረክሱ የኢትዮጵያን ነፃነት በደማቸው ቀድሰውና አንጽተው ያለፉ እነዛ የነፃነት አርበኞች ገዳማውያን ሕያው ታሪካቸው ነፍስ ዘርቶና ድል ነሥቶ ይሰማል፣ ይታያል፡፡
እዚህች ላይ እስቲ በተለይ ፋሽስት ኢጣሊያ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ካደረሰው ዘግናኝ የጭፍጨፋ ታሪክ ጋር ለአፍታ ያህል ቆይታ እናድርግ፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንዲሚመሰክሩት የዓድዋውን ውርደትና አሳፋሪ ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን/ሐበሻን በቅኝት ግዛት ለመያዝ ለሁለተኛ ጊዜ ከሮማ ምድር ተሻግሮ ለዳግም ወረራ የመጣው የፋሽስቱ የኢጣሊያ መንግሥት በተለይ በዚህ ገዳም ላይ ወደር የሌለው ጭፍጨፋና እልቂት እንዳደረሰ ተመዝግቧል፡፡
በ1928 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳምና በዙሪያው በሚኖሩ መናኒያን መነኮሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት ላይ የፋሽስት ሠራዊት ያሳየውን ጭካኔና ያደረሰውን ዘግናኝ እልቂት ኢጣሊያዊው ምሁርና የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ ‹‹Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience›› በሚለው መጽሐፋቸው፡-
‹‹. . . የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገ/ማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጭምር ሣይቀሩ ተገደሉ፡፡ ግንቦት ፳፩ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ቀን ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ ከማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ በደረሰው ምስጢራዊና ጥብቅ ትእዛዝ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላም የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት ፳፮ ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ … ፡፡›› በማለት ዘግቦታል፡፡
በነገራችን ላይ ፋሽስቶች ይሄን ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ያካሄዱት በቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምሥራቅ ኢጣሊያው የፋሽስት ገዢ የሆነው ግራዚያኒ በጠራው ግብዣ ላይ ኤርትራውያኑ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ባደረጉበት የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በግራዚያኒ ላይ ይህን የግድያ ሙከራ ላደረጉ ለእነዚህ ሁለት ወጣቶችም ገዳሙ መሸሸጊያ ሆኗቸዋል፣ የገዳሙም አባቶች፣ መናኒያንና አገልጋዮችም ከዚህ ሴራ ጋር ተባባሪ ናቸው በሚል ነበር ይሄ ዘግናኝ እልቂትና መከራ በገዳማውያኑ ላይ የደረሰባቸው፡፡
እናም ይህ ገዳም ከጥንታዊነቱ፣ ግዙፍ ታሪኩና ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ድባቡ፣ ከአስደናቂና አስደማሚ ግርማው ባሻገርም በገዳሙ ዙሪያ ባሉ ጫካዎች፣ ወንዞች፣ ፏፏዋቴዎች፣ ሸንተረሮችና ተራራሮች ማዶ ልቆና ገኖ የሚሰማ አንድ ሕያው የሆነ የነፃነት ደወል ድምፅ፣ የነፃነት ልዩ ውበት አለ፡፡ በደም የተቀደሰ፣ በደም የነጻ፣ በደም የተዋበ፣ በደም ለዘመናት የጸና፣ የፋሽስቶችንና የአውሮፓውያኑን ቅኝ ገዢዎችን ሕልም ያመከነ፣ ብርቱ ክንዳቸውን የረታ፣ በምንምና በማንም ያልተበገረ፡፡ ሥጋንና አጥንትን አልፎ ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ክቡርና ሕያው የነፃነት ድ-ም-ፅ!!
የእናት አገር የኢትዮጵያን ምድር በነፃነት ውብ ሕብረ ቀለም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ያሸበረቀ ያስዋበ፡፡ ሺሕ ዓመታትን ያሳለፈ፣ በምንም በማንም ኃይል ያልተረታ፣ ከአድማስ አድማስ ያስተጋባ፣ አፍሪካን፣ መላው ጥቁር ሕዝቦችንና በአጠቃላይ ነፃነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት ያስተሳሰረ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ውብ የነፃነት ኩራት ልዩ ዜማ፣ ልዩ ቅኔ፣ በደም የተዋበ በደም ተቀደሰ፣ በደም ያሸበረቀ፣ በደም የተጌጠ!! ዕውቁ ሠዓሊ፣ ባለ ቅኔና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ እንዲህ እንደተቀኘው፣ እንዲህ እንዳሞካሸው፡-
… አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ፡፡
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ፣
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፡፡
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት፡፡
ለምለም ነው አገሬ፣
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ …፡፡
ሰላም! ሻሎም!
ይቀጥላል፡፡