ድብደባ እና ህግ አስከባሪው ፖሊስ ሚና – አድማ መበተን ወይስ ድብደባ – ሰሚር አሊ

ድብደባ እና ህግ አስከባሪው ፖሊስ ሚና

ድብደባ ከድሮም ባህላችን የነበረ ባል ሚስቱን መደብደብ፣ አባት ልጁን መግረፍ፣አስተማሪ ተማሪውን መጠፍጠፍ፣ለኛ ኢትዮጵያውያን የታዘዘልን ባህላዊ ህክምናዎች ኣንዱ ይማስለኛል፣ በሀሳብ እና ንግግር ችግርን ክመፍታት ይልቅ ጉልበት አለኝ የሚለው አካል በሀይል አስገድዶ የራስን ፍላጎት መጫን በመሀበረሰባችን ውስጥ ያለ እውነታ ነው። እናስ መንግስት የማህበረሰቡ ውጤት ነውና ክድሮም ጀምሮ በተለያዩ ገዢዎቻችን ስንጠፈጠፍ ኖረናል አሁንም አለም ስለ ሰብአዊ መብቶች የተሻለ ግንዛቤ አለባት በምንልበት ወቅትም እኛና ድብደባ ላንፋታ የተጋባን ይመስል የድብደባ ሌጋሲያችንን እያስቀጠልን ነው። በቅርቡም ባሎች ሚስቶቻቸውን በመደብደብ የሶስተኛ ማእረግነት አግኝተናል እንዲሁም፣ በቅርቡ በመንግስት በኩልም በሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን እና ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በጅምላ በፌድራል ፖሊስ ለመደብደብ ታቅዶ ታልሞ የሰለጠኑ በሚመስል ሁኔታ ብዙ ሺህ ሰዎች ፅሎት ሊያደርጉ በሄዱበት እንዲሁም ነጋዴዎች እና ገበያተኞች እንደ አንበጣ ወረሽኝ በድንገት ተወረው ተደብድበዋል።
Image

አድማ መበተን ወይስ ድብደባ

እንደ ፈረደብን ሌላ ሀገር ምሳሌ ላርግና ህዝብ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲኖሩት ሰልፍ መውጣት የተለመደ ነው። ነገሩ ከፍቶም ችግር ከተፈጠረ አድማ በታኝ ፖሊሶች መተው ሰልፉን መበተን እንዲሁም ከተቃውሞ አድራጊዎቹ ወገን እንደ ድንጋይ እና ሀይል መጠቀም ከተጀመረም በተለያዩ መንገዶች መበተን አዲስ አይደለም። ነገር ግን ባለፈው አርብ በአንዋር መስጊድ እና መርካቶ አካባቢ የታየው ሁኔታ ግርም የሚል ነው።

ምክንያት፡~
1 ድብደባው የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፉ ሳይደረግ በፊት እየተሰገደ ነበር።
2 የተቃውሞ ስልፈኞቹ መሀል በገቡ ደህነነቶች እና ምልምል ካድሬዎች ሰልፉ ሰላማዊ እንዳይሆን አስቀድመው ህዝቡ መሀል ድንጋይ በመወርወር እንዲረበሽ አስደርገዋል።
3 በሌላ ሀገር እንደምናየው ህዝቡ እንኩዋን ከፖሊስ ሀይል ጋር ሊጋጭ ይቅርና አንድ ፖሊስ በያዘው ዱላ ብቻ እስክ ሀምሳ ሰዎችን የሚሆኑ እያሩዋሩዋጠ ሲዥልጥ ነበር።ህዝቡም እራሱን ለመከላከል ያደረገው በአለም የምንተወቅበትን እሩጫ ብቻ ነበር።
4 እናም የፖሊስ ተልእኮ አድማ መበተን ሳይሆን መግረፍ ይመስል ነበር።
5 መርካቶ አካባቢ ደጅ ላይ በልብስ ስፌት የሚተዳደሩ ወጣቶች ስራቸውን እየሰሩ ባሉበት ሰአት ከየት እንደመጣ እንኩዋን ያላዩት የፖሊስ መንጋ መቶ አናት አናታቸውን ሲፈልጣቸው ማሽናቸውን ጥለው እግሬ አውጪኝ ሲሉ ባለሱቆች ሱቃችሁን አልዘጋችሁም ተብለው እንግልት እና ድብደባ ተደርጎባቸዋል።

ፖሊስ መታሁ ስትል የሰማሁዋት አንዲት ልጅ ብቻ ነች ምክንያትዋን ስታስረዳም" መስጊድ ውስጥ ታግተን እንዳለ አንዱ ፖሊስ መጣና ከአጠገቤ የቆሙትን አሮጊት በያዘው ዱላ ወገባቸውን ሲላቸው አላስቻለኝም ለምን እኔን አይመታም እንዴት እኝህን ሴትዮ አልኩና ጫማዮን አውልቄ አናቱን ብየው ወደ ህዝቡ ውስጥ ስገባ ቆይ በሁዋላ ላግኝሽ እያለኝ ተሰወርኩበት። " በተረፈ አንድ ተጎድቶ የተኛ የፖሊስ ምስል እዚሁ ፌስቡክ ላይ የተለቀቀ አይቻለሁ እሱንም በግርግሩ መሀል መኪና የገጨው መሆኑን ተረድቻለሁ።

ከአንዋሩ ድብደባ በሁዋላ መስጊድ ውስጥ የታገቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እስከ ምሽቱ አራት ሰአት ድረስ ታግተው ወደ ተለያዩ ቦታዎች በትልልቅ መኪኖች እንደ ሰርዲን ታጭቀው ተወስደዋል።

በየማቆያ ጣቢያዎቹ የነበረው ሁኔታም የተለያየ ነበር በጉለሌ አካባቢ የታሰሩት ሰዎች በተለያዩ ኮማንደሮች ልማታዊ የምክር አገልግሎት ተሰጥቶዋቸው የተወሰደባቸው ሞባየሎቻቸው ተመልሶላቸው ከለሊቱ ዘጠኝ ሰአት አካባቢ ተለቀዋል።

ወደ ኮልፌ ያለው የፌድራል ፖሊስ ማሰልጠኛ የተወሰዱት ግን ያዩት አበሳ አሳዛኝና ዘግናኝም ነበር የሴቶችን መከናነቢያ ማቃጠል ለሊቱን ሙሉ የሰልጣኝ ፌድራል ፖሊሶች ድብደባ እንዲሁም ሞባየሎቻቸውን ቅሚያም ነውር አልነበረም። ሞባየል ሲነ’ጥቁ ቆምንለት ከሚሉት የህግ ማስከበር አላማ በተፃራሪ እንደቆሙ የሚያገናዝብ ህሊናም አልነበራቸውም። እንዲሁም ድብደባው ይደረግ የነበረው ቀጥታ አናት አናት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ደግሞ ሰዎቹ ጭንቅላት እና ከበሮን መለየት ይችላሉ ወይ ያስብላል።

አንዱ ሽማግሌ ሲያጫውቱኝ እኔ ስብሰባ ይሁን ምን የማውቀው ታሪክም አልነበረም በቃ ከባንክ የሰው አርባ ሺ ብር ቼክ አውጥቼ በዛው ልሰግድ አንዋር ሄድኩ የገጠመኝ ግን ድብደባና ዝርፊያ ነበር። በግርግሩ መሀል ስሮጥ ብሩ ተበተነ ካጠገቤ የደረሱትም ፖሊሶች "የአሸባሪ ብር ፥የአሸባሪ ብር "እያሉ ብሩን ወደ ኪሳቸው መዶል ጀመሩ እኔንም አንዴ አናቴን ሲሉኝ ነብሴን ለማዳን ፈረጠጥኩ።እንዲሁም ልጆቻቸው የታሰረባቸው ቤተሰቦችን አንዳንድ ፖሊሶች ልጆቻችሁን እንድናስለቅቅላችሁ እያሉ እስከ ሁለት ሺ ብር መጠየቅም ተጀምሮ ነበር።

እናም ህግ አስከብራለሁ የሚለው ፖሊስ እና መንግስት አሸባሪ ሆነው ህዝቡ ደግሞ ሲሸበር ዋሉ ለማጠቃለያም የዛሬ አመት እንዲሁ በኢድ ሰላት ላይ ድብደባ ተደርጎ ነበር፣ እናም አንድ ገጠመኝ አጫውቼያችሁ ልሰናበት ልጁ ፖሊሶች እንደ ለመዱት አናት አናቱን በዛ ዱላቸው ሲያራውጡት የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው ሆኖበት "ወላሂ እኔ ክርስትያን ነኝ" አላቸው።