ለክቡር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር – ግርማ ሠይፉ ማሩ

ሐምሌ 11 ቀን 2006
ለክቡር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በጥርጣሬ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት አያያዝ ይመለከታል

ክቡር ኮሚሽነር ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ በ “ወንጀል” ተጠርጥረዋል በሚል የፓርቲያችን አንድነት ለፍትህና ዲሞክራሲ (አንድነት) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው እና የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም አቶ አብርሃ ደሰታ ከአረና ፓርቲ እና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ በፖሊስ ቁጥጥር ስር አንደሚገኙ ሰምተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሁን አንጂ ይህን ማመልከቻ እሰከምፅፍበት ሰዓት ድረስ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ታሳሪዎች ከህግ አማካሪ እና ቤተሰብ ጋር በህግ በተፈቀደው ስርዓት መሰረት ሊገናኙ አልቻሉም፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ማንም በሌለበት እና ከህግ አማካሪዎች ጋር ሳይገናኙ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ወደ ማእከላዊ ሄደዋል የሚል ዜና ቢወጣም አሁንም በትክክለኛ ሁኔታ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው መረጃ የሚሰጥ አካል አላገኘንም፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ከምሸቱ በአንድ ሰዓት ፍርድ ቤት ቀርበዋል የሚሉም አሉ፡፡

በዚህ የተነሳም ተሳሪዎች በድብቅ ፍርድ ቤት ቀርበዋል የሚባልበት ሁኔታ እና ይልቁንም ከህግ አማካሪያቸው እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ የተደረገበት ሁኔታ ከፍተኛ ጥርጣሬ የሚያሳድር ነው፡፡ የእነዚህ ታሳሪዎች በጥርጣሬ የታያዙበትን ወንጀል እንዲያምኑ በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ሆነ በህገ መንግስት ተቀባይነት ባገኙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ምንም ዓይነት የሀይል እርምጃ እና ህገወጥ የሆነ ምርመራ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ሰለሆነም ክቡር ኮሚሽነር በህገ መንግስት የተፈቀደ ሰብዓዊ መብታቸውን የተነፈጉ እነዚህ ታሳሪዎች ያሉበትን ሁኔታ መስሪያ ቤቶ ክትትል እንዲያደርግ እና ለቤተሰቦች እንዲያሳውቅ አደራ ጭምር እየጠየቅሁ፡፡ የፖሊስ አካላትም ይህን ህገ ወጥ ክልከላቸውን እንዲያቆሙና ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ እንዲያሳሰቡልን እንጠይቃለን፡፡ በአፋጣኝ የታሳሪዎችን ሁኔታ ማወቅ በታሳሪዎች ላይ ሊደርስ ከሚችል አካላዊም ሆነ ሌላ ማንኛውም ጉዳት ለመታደግ ስለሚረዳ፣ ሀገርም ከዚህ የምትጠቀመው አንድም ነገር ስለማይኖር ክቡርነትዎ አሰፈላጊውን ትኩረት ስጥተው ኃላፊነቶን እንደሚወጡ ተሰፋ አለኝ፡፡

ከማክበር ከሠላምታ ጋር

ግርማ ሠይፉ ማሩ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል