የታጋዩ የልጅ ልጅ
<<ስኩል ኦፍ ኖርዘርን ስታር›› ከሚባለው ውድ ትምህርት ቤቱ የአያቱ ሾፌር ወደ ቤቱ ሲያመጣው ልቡ ከመኪናው ፍጥነት በላይ ነበር ወደ ቤቱ የሚሮጠው፡፡ ያየውንማ ለአያቱ መንገር አለበት፡፡ አያቱ እንዲህ ታዋቂ አክተር መሆናቸውን አያውቅም ነበር፡፡ ፊልሙን ሲመለከት አያቱን በመሪ ተዋናይነት በማግኘቱ ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር በኩራት ነበር ያወራው፡፡ እነርሱም የታዋቂ ሰው የልጅ ልጅ በመሆኑ ከፊልሙ በኋላ እንደ ንብ ነበር የከበቡት፡፡ ብዙዎቹ እንዲያውም በወረቀት ላይ አያቱን አስፈርሞ እንዲያመጣላቸው፣ ከተቻለም ፎቷቸውን እንዲሰጣቸው ለምነውታል፡፡
ቤቱ ሲገባ አያቱ የሉም፡፡ ደወለላቸው፡፡ እየመጡ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ መክሰስ ለመብላት እንኳን ሆድ አልቀረለትም፡፡ ይህን አስገራሚ ነገር ከአያቱ ጋር ማውራት እጅግ አጓጉቶታል፡፡ እየደጋገመ ‹ፐ› ይላል፡፡ አባቱና እናቱ ራሳቸው ይህንን የሚያውቁ አልመሰለውም፡፡ ይህንን ነገር ያወቀ የመጀመሪያ ሰው እርሱ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገምቷል፡፡ ‹ፐ›፡፡
አያቱ መጡ፡፡
‹‹አያቴ ቴክ ፋይቭ›› አለና በአምስት ጣቱ አምስት ጣታቸውን ገጨ፡፡
‹‹ምን ተገኘ ዛሬ›› አሉ አያትዬው ደንቋቸው፡፡
‹‹እኔኮ አክተር መሆንህን አላውቅም ነበር፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ አያቴ አክተር መሆኑን ሲያውቁ ሪስፔክት አደረጉኝ›› አላቸው በሳቅ እየተፍለቀለቀ፡፡ በጣቱ እንደ ሽጉጥ ያለ ነገር ሠርቶ፣ በእግሩ ተንበረከከና በግድግዳው ላይ ‹‹ቷ-ቷ-ቷ-ቷ›› አደረገ፡፡
‹‹የምን አክተር ነው››
‹‹እንዴ የሠራኸውን ፊልምኮ አየነው፡፡ ትምህርት ቤታችን ውስጥ አየነው፤ መሥራትህን ረሳኽው እንዴ››
‹‹የምን ፊልም ነው የሠራሁት››
‹‹አክሽን ፊልም ሠርተኻልኮ፤ ፓ ትልቅ ገን ይዘህ ተርርርርር ስታደርግ ጓደኞቼ አጨበጨቡልህ፤ ስታሩ አንተ ነበርክ እንዴ? ኢነሚዎችህ ሲተኩሱብህኮ ዘለህ ገደል ውስጥ ገባህ፤ ተንከረባበትክኮ፤ ከዚያ ደግሞ ቦንብ በጥርስህ ነቅለህ ወረወርክና ቦዋ ሰጠኸው፤ ከዚያ ታንኩ ሲተኩስብህ በገደሉ ውስጥ ገብተህ አመለጥካቸው፡፡ ልክ ስታመልጥ ጓደኞቼ እያፏጩ አጨበጨቡ፡፡››
አያት ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ለልጁ ምን አሳይተውት እንደሆነ ግራ ገባቸው፡፡
‹‹እስኪ ያየህውን ቀስ ብለህ ንገረኝ››
‹‹እይ፣ በትምህርት ቤታችን ‹ሂስትሪ ዊክ› አለ፡፡ ትናንት ፊልም ነበር፡፡ ‹ዘ ፋይተርስ› የሚል የኢትዮጵያ ፊልም አሳዩን፡፡ የድሮ ታሪክ ነው ብለዋል፡፡ እና – እና እዚያ ላይ አየሁህ፤ አሪፍ አክተር ነበርክ ለካ፡፡ ለምን ግን አክተርነት ተውክ? ነጋዴ ከመሆንኮ አክተር መሆን ይበልጣል፡፡ ዳድ ነጋዴ ነው፡፡ ጓደኞቼ ግን አድንቀውት አያውቁም፡፡ አንተ አክተር መሆንህን ሲያዩ ግን ከበቡኝኮ››
አሁን አያትዬው ገባቸው፡፡
‹‹ያየህውኮ እውነተኛ ታሪክ ነው›› አሉት፡፡
‹‹ቤዝድ ኦን ትሩ ስቶሪ – ነው››
‹‹ኖ ኖ ኖ ኖ፣ ያ የኛ የታጋዮች ታሪክ ነው፡፡ አክተር ሆኜ አይደለም፡፡ ከደርግ ጋር ያደረግነውን ውጊያ ፊልም ነው ያሳዩዋችሁ››
‹‹እንደ ደርግ ሆኖ የሠራው አክተር ማን ነበር? ታንክ ምናምን እየነዳ – ቡልቅ አድርጎ ሲተኩስ – ፓ››
‹‹ይህኮ ፊልም አይደለም፤ የተደረገ ታሪክ ነው፡፡
‹‹እንዴ አያቴ፣ አንተ ፋይተር ነበርክ እንዴ?››
‹‹አዎ››
‹‹ገን ምናምን ይዘህ›
‹‹አዎ››
‹‹ኦ- ማይ ጋድ -እና ሰው ገድለሃል?›› ስቅጥጥ አለው ልጁ
አሁን አያት እንዴት እንደሚያስረዱት ግራ ገባቸው፡፡ እርሱ ደግሞ አያቴ አክተር ነበሩ ብሎ ያገኘው ክብር ሲናድበት ታየው፡፡
‹‹አየህ ድሮ ደርግ የሚባል መንግሥት ነበረ›› ብለው ሲጀምሩለት
‹‹ደርግ ምን ማለት ነው? እዚያ ፊልሙ ውስጥም ደርግ ደርግ ይል ነበር፤ እኛኮ የአክተር ስም መስሎን ነበር››
አንገታቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እየነቀነቁ ለማስረዳት ቃላት ፍለጋ ገቡ፡፡
‹‹እርሱን ለማስወገድ ጫካ ገብተን ብዙ ዓመት ተዋግተናል››
‹ለምን ታወግዳላችሁ?ፊልሙ ራሱ ያልቅ ለም እንዴ››
‹‹ፊልም አይደለም ብዬህ››
‹‹ቆይ ግን ቢች አካባቢ ብቻ ነበር እንዴ ፋይት የምታደርጉት››
‹‹እንዴት›› አሉ ገርሟቸው
‹‹ቁምጣ ብቻ ነበራ ሁላችሁም ያረጋችሁት››
ሳቁ፣ እስኪበቃቸው ሳቁ፡፡
‹‹ግንኮ እይ›› አለና አንድ መጽሔት ይዞላቸው መጣ፡፡ የፋሽን መጽሔት ነው፡፡ እዚያ ቤት ደንበኛ የሆነ መጽሔት ነው፡፡ ‹‹እይ ፀጉራቸውን እንደ እናንተ አቁመው የሚበትኑትኮ ሴለብሪቲስ ናቸው፡፡ እይ›› ዘፋኞችና የፊልም ተዋንያን እዚያ መጽሔት የፊት ለፊት ሽፋን ላይ ፀጉራቸውን አንጨብረው ተነሥተዋል፡፡ ‹አክተር ካልሆናችሁ ፀጉራችሁን ለምን እንደዚህ አደረጋችሁት?››
‹‹እኛኮ ትግል ላይ ነበርን፤ እንደ እናንተ ንጽሕና ለመጠበቅ፣ ገላ ለመታጠብ፣ ፀጉር ለመቆረጥ ጊዜ አልነበረንም››
‹‹እና ሻወር አትወስዱም ማለት ነው? ሚስ ዝም ትላችኋለች?››
‹‹በኛ ጊዜ ሚስ የለም›› አሉ ለመገላገል፡፡
‹‹እንዴት፣ ሚስ የሌለው ትምህርት ቤት አለ እንዴ? እንደዚያ ዓይነት ትምህርት ቤት በ‹አይስ ኤጅ› ጊዜ ብቻ ነው የሚኖረው››
‹‹እኛ እንደናንተ የመማር ዕድል አላገኘንም፣ትግል ላይ ነበርን››
‹‹ፋይት ብቻ ነበር ሥራችሁ ማለት ነው፤ እኛን ግን ዳድ ፋይት አታድርጉ ይለናል፡፡ እኔና ሳሚኮ ዋተር ገን ይዘን ፋይት ስናደርግ፣ ፋይት ጥሩ አይደለም ይላል፡፡ እናንተን ግን አባታችሁ ዝም ይላችኋል አይደል? ታድላችሁ፤ እስኪ ዳድን አስፈቅድልን››
‹‹ፋይት ማድረግማ ጥሩ አይደለምኮ››
‹‹ታድያ እናንተ ለምን ፋይት አደረጋችሁ››
‹‹እኛኮ ከደርግ ጋር ነው ፋይት ያደረግነው››
‹‹በቃ ወይ እኔ ወይ ሳሚ ደርግ እንሆናለና››
‹‹እይውልህ ጃክየ ወደፊት በደንብ አስረዳሃለሁ፤ አሁን ገና ልጅ ነህ››
‹‹ቆይ ቆይ አያቴ፣ እነዚያኞቹ፣ ኢነሚዎቹ ደርግ ናቸው ብለሃል፣ እናንተ ማንን ሆናችሁ ነው ፊልሙን የሠራችሁት›› ፊልም የሚለው ነገር ከልቡ ሊወጣ ባለመቻሉ እያዘኑ
‹‹የኛ ስም ኢሕአዴግ ይባላል››
‹‹እኛ ግን ሁለቱንም ስሞች አማርኛ ስንማር አልተማርናቸውም፤ ሚስም አታውቃቸውም ማለት ነው›› አለና በሳሎኑ መስኮት ውጭ ውጪውን ማየት ጀመረ፡፡
‹‹ጃክ ምነው አያትህ ፋይተር በመሆኔ ከፋህ እንዴ›› አሉት አያቱ፡፡
‹‹እኔ ግን ፋይተር ከምትሆን አክተር ብትሆን ነበር ደስ የሚለኝ፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ አያቴ አክተር ነው ስላቸው ጎል እንዳገባ ተጫዋች ነበር ያቀፉኝ››
‹‹ፋይተር ነበር፣ ፈሪደም ፋይተር ነበር በላቸዋ››
‹‹እና ከዚያ ሰው ገድሏል ወይ? ለምን ገደለ? ማንን ነው የገደለው? ቢሉኝስ፤ እኔንስ ቢፈሩኝስ፣ አያቱ ቁምጣ ለብሶ አየነው ብለው ቢስቁብኝስ፤ የአያቱ ፀጉር ተንጨብሯል ቢሉኝስ፤ በ‹አይስ ኤጅ› ጊዜ የነበረ ነው ቢሉኝስ፣ አልነግራቸውም››
አያቱም በተራቸው በመስኮቱ በኩል ወደ ውጭ ማየት ጀመሩ፡፡ ‹‹ተተኪው ትውልድ ግን እንዲህ ነው የሚረዳን ማለት ነው? የእርሱ ዘመን ጀግኖች ሌሎች ናቸው ማለት ነው? ወታደራዊ ታሪክን ማድነቅ ትቶ መዝናኛዊ ሰብእናን የሚያደንቅ ትውልድ ነው ያፈራነው ማለት ነው? ምናልባት ከኛ በፊት ለነበሩት ሌሎች ታጋዮችና አርበኞች ቦታ ባለመስጠታችን አዙሪቱ እኛም ላይ እየደረሰ ይሆን? ውጊያችንን እንደ ፊልም ነው የሚቆጥሩት ማለት ነው? ›› ማለቂያ የሌላቸውን ጥያቄዎች በመስኮቱ በኩል ይወረውራሉ፤ ጥያቄዎቹ ግን በመስኮት እንደወጡ ነው የቀሩት፤ አልተመለሱም፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው