የቴክሳሱ ተንኮለኛ እባብ

ወርቁ ለገሠ ከዳላስ

እንደ እባብ ብልህ፣ እንደ ርግብ የዋህ ሁኑ ተብሎ መጻፉን ሁሉም ስለሚያውቀው ምዕራፍና ቁጥር በመጥቀስ አንባብያንን ማሰላቸት አልፈልግም። እዚህ በቴክሳስና በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኘው መካከለኛ ግዝፈት ያለው ሆግኖዝ ተብሎ የሚጠራው እባብ ብልሃት ከላይ የተጠቀሰውን ብሂል ፍንትው አድርጎ ለማሳዬት ይረዳል ብየ ስለገመትኩ ጠቅለል አድርጌ በአማርኛ ተረጎምኩት።

እንደሌሎች መርዛማ እባቦች በፍጥነት ለመወርወር ተፈጥሮ አላደለችውም። ከዚህም የተነሳ ሰውም ሆነ ሌላ ጠላት በገላጣ ቦታ ካገኘው ማምለጥ ከቶ አይቻለውም። እባቡ ዓይናፋርና መናደፍ የማይችል ሲሆን ጠላትነቱ ለ ዕንቁራሪት ብቻ ነው። እሱም መመገብ ስላለበት እንጅ ለተንኮል አይደለም። እንደ ኮብራ መርዛማነትን ያልታደለው ይህ እባብ በየጊዜው የጠላቶቹ ሰለባ ሆኖ ከምድረገጽ እንዳይጠፋ በደመ ነፍስ የራሱን የመከላከል ዓቅም በመገንባት የመከላከል ዕርምጃ ሳያሰልስ ይወስዳል።፡ እነዚህም ዕርምጃዎች በሶስት ደረጃ በቅደም ተከተል ይከናወናሉ፡

eastern hognose snake
1ኛ ደረጃ፡- ከላይ በሥ ዕሉ እንደተመለከተው የመከላከያ ዕርምጃ እንደሚከተለው ይከናወናል (1) ቀለሙ ከአካባቢው ጋር በመመሳሰሉ ከጠላቱ ዕይታ ሊሰወር እንደሚችል በመገመት ሰው ወይም ሌላ አውሬ መጀመሪያ ሲያገኘው ለጥ ብሎ ይተኛል። ይህ ሳይሠራ ሲቀር (2) በተቻለው ፍጥነትና በተገኘው ቀዳዳ ሾልኮ ማምለጥ ይሞክራል. ከላይ የተገለጹት ሁለት ዕርምጃዎች ስኬታማ ሆነው ካልተገኙ እባቡ ከዚህ በታች በሥ ዕሉ እንደተገለጸው ወደሁለተኛው ስትራቴጅ ይሸጋገራል:

eastern hognose snake
2ኛ ደረጃ፡- በዚህ ደረጃ እባቡ የሚወስደው የመከላከል ዕርምጃ ማስመሰልን የተላበሰ ሲሆን መርዛማ እባቦች የሚያሳይዋቸውን ጠባዮች ሁሉ በመሞከር ጠላቱን አስፈራርቶ ማባረር ይሞክራል: (1) እባቡ ራሱን ከፍ አድሮ በመያዝ፣ አፉን ከፍቶ ወይም ዘግቶ ወይም በተጠቀለለው ሰውነቱ ውስጥ በመቅበር ቆልማማ ጅራቱን በአየር ላይ ቀጥ አርጎ ያቆመዋል። ከዚያ በመቀጠል በረጅሙ አየር ስቦ ስያስወጣ ልክ አደገኛ የሆኑ የእባብ ዝርያዎች የሚያወጡትን ሲር ሲር የሚል ድምጽ ይፈጥራል። ይህም ጠላቱን “ወዮልህ! መርዛማ ነኝ፤ ተበላሸህ!” እያለ በፍርሃት እንድዋጥና ነፍሱን ለማትረፍ እንዲፈተለክ ሊያስገድደው ይሞክራል። (2) እባቡ ራሱንና አንገቱን ጨምሮ የላይኛው የአካል ክፍሉን ጠፍጠፋ ቅርጽ እንድይዝ በማድረግ በአደገኛነቱ የታወቀውን የኮብራ እባብ ቅርጽ እንድይዝ ያደርጋል። በአፉ ውስጥ የሚገኙት ከረጢቶች በአየር ተሞልተው ስለሚወጠሩ የእባቡን ራስ አስፈሪና አስደንጋጭ ያደርጉታል። ይህም ጠላቱን ወደመጣበት ባፋጣኝ እንድመለስ ማድረግ ካላስቻለ (3) እጅግ መርዛማ የሆኑ እባብ ዝርያዎችን ባህርይ ተላብሶ ጠላቱን ለማጥቃት የተዘጋጀ መሆኑን ለጠላቱ ይፋ ያደርጋል። መጥፎነቱ ይህን ዕርምጃ ሊወስድ ዝግጅት ሲያደርግ አፉን እንደከደነ ስለሆነ ስለተናዳፊ እባብ ዕውቀት ያላቸው ሰዎችም ሆኑ እንስሳት እባቡ አምቧታሪ መሆኑን በቀላሉ ይለዩትና ስትራቴጅው ሊከሽፍ ይችላል።

eastern hognose snake

3ኛ ደረጃ፡- በተራ ቁጥር 2 የተመለከተው ስትራቴጅ ሳይሰምር ቀርቶ ጠላቱ ሙዝዝ ብሎ ሰውነቱን ካልነካው በስተቀር በተራ ቁጥር 3 የተመለከተው የመከላከያ ዕርምጃ ፈጽሞ አይታሰብም። ያ ሁሉ ዘዴ ከተደቀነበት የሞት አደጋ ካላስጣለው ግን 3ኛው ደረጃ ላይ የተመለከተው ስትራቴጅ በሚከተሉት ቅደም ተከተል ይከናወናል። መጀመሪያ ያስታውካል፣ ቀጥሎ ዘግናኝ የሆነ ሽታ ያለው ኬሚካል ይረጫል፣ ቀጥሎ የማያቋርጥ ደም ከአፉ ይጎርፋል፣ ምላሱን ጎልጉሎ ያወጣና ሆዱን ለጸሃይ አጋልጦ በመጠቅለል ሞቻለሁ፣ የኔ ነገር አበቃለት ዓለም ደህና ሰንብች፣ ጠላቶቼ ደስ ይበላችሁ፣ ዕረፉት የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። ቢገለብጡት እንኳ መልሶ ሆዱን በማጋለጥ ህይዎት እንደሌለው ለማረጋገጥ ይጥራል። ጠላቱ ጥሎት እስከሚሄድ ድረስ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ድፈጥ የሞተ ምሰል ዘዴውን ይገፋበታል። ጠላቱ ከአካባቢው መሄዱን ካረጋገጠ በኋላ ግን ራሱን ቀና አርጎ የቅኝት ሥራውን ይፈፈጽምና ሸውጀሃልሁ ብሎ ፈትለክ ብሎ በማምለጥ ከአካባቢው ይሰወራል።

hognose snake

በደመ ነፍስ እንዲህ ዓይነት ከሞት የማምለጫ ጥበብ ሲከናወን ማዬት አጃኢብ የሚያሰኝ ነው። እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ ሁን ተብሎ የተጻፈው ሁሉንም የእባብ ዝርያ ሳይሆን ይህን የቴክሳሱን ተንኮለኛ እባብ መሠረት በማድረግ ሳይሆን ይቀራል?

በሚቀጥለው ጽሁፌ አንዲት እንደ መለስ ዜናዊ ሸረኛ የሆነች የወፍ ዝርያ በሌሎች ወፎት ላይ የምትፈጽመውን ደባ አስመልክቶ በማቀርበው ትርጉም እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን።

(ምንጭ፡ bugsinthenews.com)