ማን ይንገርልን – ማን ይመስክርልን
ጸጋዬገ ብረመድኅን አርአያ
እንደ ልጄ የምቆጥረውና ከበኩር ልጄ ከዩሐንስ ጋር ያደገው ሳምሶን በሕክምና ኮሌጅ ይማር በነበረበት ዘመን በምሽቱ ሰዓት ላይ የ‹‹ፈገግታ ጊዜ›› በምንለው ግማሽ ሰዓት ያጫውተን ነበር፡፡ አዎን ሕይወት ውጥርጥር ባለበትና ጭንቀት ከቀበሌ ከሚወረወር ቀስት፣ ጭንቀት ከየካድሬውና ከየፖለቲካው ኅቡዕ ድርጅት ከሚወረወር ሌላ ቀስት፣ ጭንቀት፣ ከመስሪያ ቤት ጭንቀት፣ ከበላይ አካል ጭንቀት፣ ከበታች አካል ጭንቀት፣ ጭንቀት —- አንድ የድሮ ማስታወቂያ ሚኒስትር እንዳሉት ከላይ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ በሚለቀቅብህ እሳት፣ ከታች ከሕዝቡና ከሠራተኛው ከሚነድድብህ እሳት የገና ዳቦ ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ‹‹በታይም አውት›› (ፋታ ልበለው) መልክ ከሳሚዬ ጋር የማደርገው የግማሽ ሰዓት ውይይት (ጨዋታ) ለእኔ “ማሳጅ” ነበር፡፡ መታሻ!