ኢ- ፍትሃዊው እስሬ! እየፈሩ ጋዜጠኝነት የለም!
ኤልያስ ገብሩ ጎዳና (አዲስ አበባ)
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታችን ትልቅ አደጋ ላይ ነው
አርብ ግንቦት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከወዳጄ ጋዜጠኛ ዳዊት ሠለሞን ጋር ቀጠሮ ነበረኝ። ረፋድ 5፡25 ሰዓት ላይ የሞባይል ስልኬ ጠራች። ከአምባሳደር ወደአራት ኪሎ በሚጓዝ ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ ነበር። የመስመር (የቢሮ) ስልክ መሆኑን አየሁትና “ሃሎ” አልኩኝ። ‹‹አቶ ኤልያስ፣ የዕንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ?›› የሚል የሴት ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ‹‹አዎን›› ስል መለስኩላት። ብዙ ጊዜ አንባቢዎች ስለሚደውሉ፣ ምን ዓይነት ግብረ-መልስ (feed back) ይኖራት ይሆን ነበር ሀሳቤ፡፡