ማሳጠር እንድንችል የወያኔን እድሜ

ወለላዬ

ማሳጠር እንድንችል የወያኔን እድሜ፣
ምን ማድረግ አለብን? ተናገር ወንድሜ?
እህቴም ድምጽን አሰሚ እንማከር፣
ምንድነው ሃሳብሽ ለገጠመን ችግር?
ይህንን የምለው የሃገሬ ጉዳይ፣
ስላሳሰበኝ ነው ከምንግዜም በላይ።
ቃላት በማሳመር በመደርደር ግጥም፣
ሰውን ማሰላቸት ማዳከም ባልወድም፣
ሀሳቤን ማስረዳት ይገባኛል የግድ፣
በትግሉ እንድንገፋ ባንድነት እንድንሄድ።
መጀመርያ በደንብ ሁሉን ነገር ሳናውቅ፣
ግለሰብ ድርጅት በደፈና አንናቅ።
እኔነኝ አዋቂው በዚህ ጉዳይ ዙርያ፣
ብዙ ቅርበት አለኝ ለናት ኢትዮጵያ፣
በማለት ሌላውን አሳንሰን አንይ፣
ጥፋቱን ልማቱን በግልጽ እንወያይ፣
በውይይት መድረክ በቡድን በግንባር፣
ያልጠራ ጥላቻ ጋርደን ትልቅ አጥር፣
በዘረኛ ቢታ በወያኔ ወጥመድ፣
ተወታትበን ታስረን ገብተን
አንሽመድመድ።
በአፋችን ትግል በልባችን ጥቅም፣
ይዘን አንነሳ የውሸት አናዝግም፣
መናገር ሳንችል መጠየቅ ፊት ለፊት፣
ጓሮ ተደብቀን አንደር በሃሚት።
ጥቅም አስተሳስሮን አነካክቶን ገንዘብ፣
ከልብ የሌለንን በአፍ በመሳደብ፣
እውነተኛ ታጋይ ለሚሰራው ስራ፣
ፊት ለፊቱ ቆመን አንሁን ደንቃራ።
እንዲሁም በመለስ የጎሳ ስንጠቃ፣
መከፋፈል ፈጥረን በከንቱ አንዋቃ።
ጠልተን እንዲጠላ ስም ሰጥተን በመንቀፍ፣
ለራሳችን ትግል አናሳጣ ድጋፍ።
የጠላታችን ጸር እንዲሆነን ወዳጅ፣
መንገዱን እንክፈት ብዙ ጊዜ ሳንፈጅ።
ወዳጅ እያራቅን ጠላት ማግበስበሱ፣
እኛን እየጎዳን ብዙ ጠቅሟል ለሱ።
የዘላለም ጠላት የዘላለም ወዳጅ፣
የለም ብሎ ካለን ብዙ ቆየ ፈረንጅ።
ደግሞም አንድ ጥፋት ግለሰብ ቢሰራ፣
ብዙ ነገር ቢጭር ለግዜው ቢአቅራራ፣
ትልቅ ጠላት አድርገን አብረን አንለፍልፍ፣
አውቀነዋል አንዴ በትዕግስት እንለፍ።
ሌላውን ደፍጥጠን ስልጣን ለመጨበጥ፣
አንችልም ጨርሶ ሌት ከቀን አንሩጥ።
ካልሄደ በስተቀር ማንም ሃቅን ይዞ፣
አይቀርም ማምጣቱ ሌላ ጥፋት መዞ።
ቃላት በመሰንጠቅ በከንቱ ልፈፋ፣
እንኳንስ ወር አመት ደቂቃም አናጥፋ።
ብዙ ከመደነቅ በጽሁፍ በግጥም፣
እውስጡ ያለውን ቁምነገር እንልቀም።
ከሁሉም ንግግር ጠቃሚ ሀሳብ ወስደን፣
ካለው ሁኔታ ጋር አንድ ላይ አስማምተን፣
ግማሹን በይፋ ከፊሉን በሚስጥር፣
በደንብ የተብልላ አርገንበት ምክር፣
ለመጓዝ ከቻልን በእንዲህ ያለ መንገድ፣
ሶስት ወራትም አንፈጅ ወያኔን ለማውርውድ።
እንኳንስ በሰው ደም የናወዘን መሪ፣
ታጥቆ የመጣውን የውጪ ወራሪ፣
በተደጋጋሚ ቋንጃውን በመስበር፣
ማስወጣት ችለናል አስቆጥረን አሳር።
ሆኖም ለዚህ ሁሉ ቋሚ መሰረቱ፣
እስትንፋሱ ጭምር ደምና አጥንቱ፣
ህብረት ስለሆነ እንቁም በጋራ፣
ንዝንዝ ጭቅጭቅ ይብቃን አተካራ።
በትንሽ ትልቁ ሳንሆን አኩራፊ፣
ችግር ቢገጥመንም ሆነን ሆደ ሰፊ፣
ከትግሉ ጎዳና ሳንሸሽ ሳንረቅ፣
አብረን መስራት እንቻል ህብረቱን
እናጥብቅ።