የሀዲስ ግርማ የመታሰቢያ ድርጅት የ3ኛ ዓመት ጉባዔ ተካሄደ፤ የአማርኛ ቋንቋ የተከታተሉ ሕጻናት ተመረቁ!! – አቡጊዳ

በቦስተንና አካባቢዋ ከ3ዓመት በፊት በወጣት ሀዲስ ግርማ መታስቢያነት የተቋቋመው የሀዲስ ግርማ የመታስቢያ ድርጅት የ3ኛ ዓመት ጉባዔ እሁድ ጁን 1 ቀን 2014 ዓ. ም. በረስል ዩዝ ኮሚኒቲ ሴንተር፣ ካምብሪጅ (Russell Youth Community Center, Cambridge, MA) በተለያዩ ዝግጅቶች በተሳካ ሁኔታ ተካሄዷል። በእለቱ ከተካሄዱት ፕሮግራሞች የመጀመሪያው እና የብዙዎችን ትኩረት የሳበው በዚህ አመት በሀዲስ ግርማ መታስቢያ ድርጅት እና በወላጆች ጥረት በቅዳሜ የትምህርትና የቤተስብ ድጋፍ ፕሮግራም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ሕጻናትና ወጣቶች የምረቃ ስነ ስርዓት ነበር። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሕጻናት በጀማሪ፤ በመካከለኛ እና በመደበኛ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረውን የአማርኛ ትምህርት በጥሞና የተክታተሉ መሆናቸው በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገለጸ ሲሆን በእለቱም ሕጻናቱ በአማርኛ ሲናገሩ እና ሲያነቡ ከወላጆች ከፍተኛ አድናቆት በጭብጨባ ተቸሮዋቸዋል፤ እኛም ሌሎች የዚህ እድል ተጠቃሚ ያልሆኑ ህጻናት በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ዘመን ወላጆች ትኩረት በመስጠት ልጆቻቸውን በማስመዝገብ የአማርኛ ቋንቋ እንዲማሩ እንዲያደርጉ እናበረታታለን። በአማርኛ የትምህርት ዝግጅት ክፍል በኩልም የአማርኛ መጽሃፍና የፊደል መማሪያዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፤ እነዚህንም መጻህፍት ሕጻናት በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉበት መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ ለመግዛት የሚፈልጉ ወላጆች የሀዲስ ግርማን የመታሰቢያ ድርጅት የአማርኛ ትምህርት ክፍልን በማነጋገር ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል።

በቀጣይም የእለቱ ዋና ፕሮግራም በተመለከተ በአቶ ግርማ አስፋው አስተዋዋቂነት እና የመግቢያ ገለጻ መሰረት የአንድ ኢሚግራንት ቤተሰብ ምኞትን የማሳካት ሕልምና ጉዞ፤ በጉዞ ላይ ስለሚገጥሙ ሳንካዎች እና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ ገለጻ በእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ዶ/ር ኪም ፈቸል ፤ ዶ/ር ስቴፕልስ፤ ወ/ት ገነት በቀለ በተለያየ ርዕሶች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ ሰጥተዋል። በቀጣይም ተሳታፊዎቹ በግሩብ ውይይት ላይ በቤተስብና በወጣቶች ዙሪያ፤ ሥልጠና እና የሙያ ትኩረት፤ የትምህርት ዝግጅትና የገንዘብ ድጋፍ ምንጭ፤ ጭንቀትን ስለመቋቋም እና ስለአእምሮ ደህንነት ግንዛቤ ላይ ያተኮረ ውይይቶች ተካሂደዋል። በአጠቃላይ ይህ አይነቱ ትምህርታዊ ዝግጅቶች በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉ በአካባቢያችንን በተለያየ ጊዜ እየተክሰተ ባለው የአእምሮ ጭንቀት ላይ ግንዛቤ እንዲኖረን ከማድርጉም በላይ በዚህ ችግር የሚሰቃዩ ወገኖችንም ለመርዳት ትልቅ እግዛ ስላለው በርቱ ተበራቱ የሚያሰኝ ነው እንላለን። ሕብረተስቡም የዚህን አይነት ትምህርታዊ እና ጠቃሚ ፕሮግራሞችን መከታተሉ የጋራ ችግራችንን ለመቅረፍ ስልሚያስችለን አትኩሮት በመስጠት ቢሳተፉ ጥሩ ነው እንላለን።IMG_5111

IMG_5195

IMG_5230