አስተዳደሩ ለናዝሬት ሰኔ 1 ሰልፍ እውቅና ሰጠ – የአዳማ/ናዝሬት አንድነት
አንድነት በአዳማ ስለመሬት ስሪትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ጠራው ሰልፍ ከ20 ቀናት በኋላ ዕውቅና አገኘ፡፡ ግንቦት 5 ነበር ደብዳቤያችንን ለከንቲባው ጽ/ቤት ያስገባነው፡፡ ጥያቄያችንም ግንቦት 10 ሰልፍ ለማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም በከንቲባው ጽ/ቤት ቢሮክራሲ ለሰኔ 10 ሊፈቀድ ቀርቶ ሊያነጋግሩን እንኳን ባለመቻላቸው ወደ ከንቲባው የተላከው ደብዳቤያችን በከንቲባው አማካኝነት ከግንቦት 20 በኋላ ሊስተናገድ ከባንኮኒ ገብቶ ተቆለፈበት፡፡
ክትትላቸውን ያላቋረጡት የአዳማ አንድነት ቢሮ ስራ አስፈጻሚ አባላት ዕልህ አስጨራሽ የሆነውን ትንኮሳና ውጣውረድ ተቋቁመው፤ በዛሬው ዕለት ጠዋት ከንቲባው ጽ/ቤት ገብተው ለምሳ እንኳን ሳይወጡ ጉዳያቸውን በሰላማዊ የትግል ስልት መንገድ ቢሮ ገብተው በመቀመጥ (sit-inn) እና “ጉዳያችን እስኪፈጸም አንወጣም” በማለት ለማስፈጸም ችለዋል፡፡ ደብዳቤው እጃችን ሲገባ ሰዓቱ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን ይህንን መልዕክት ስንጽፍ ምሳችንን ኀ/ስላሴ ምግብ ቤት በልተን ገና ማረፋችን ነው፡፡ (ስለ ኀ/ስላሴ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ወደ ፊት ይኖረናል-የድሆች መመገቢያ ነውና፡፡)
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በፍትሃዊ የመሬት ስሪት ጥያቄ እና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ለሰኔ አንድ የጠራው ሰልፍ በዛሬው ዕለት እውቅና በማግኘቱ ለመላው የአንድነት አፍቃሪ ሕዝባችን ደስታችንን ስንገልጽ በታላቅ ኩራት ነው፡፡ ሰኔ አንድ በአዳማ ፖስታ ቤት ጠዋት ከ3፡30 ጀምሮ በመገኘት ድምጻችንን እንድናሰማ በአክብሮት ጋብዘንዎታል፡፡
ኢህአዴጋዊነት ከሕግ በላይ መሆኑ ይቁም!
ድል የሕዝብ ነው!
25/09/2006 ዓ/ም አዳማ
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)