የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አባላት ውሳኔ

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር (ኢህአግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቻፕተሮች ጉባኤ ውሳኔ

ኢህአግ ከተቋቋመ 11 ዓመታት አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ አርበኞች መስዋዕትነት ቢከፍሉም በየወቅቱ በሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችና እንቅፋቶች ምክንያት ግንባሩ እድሜውንና የተከፈለውን መስዋዕትነት የሚመጥን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም። ይህ ለምን እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በዓለም ዙሪያ ያሉ የኢህአግ ቻፕተሮችና ነባር አባላት ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ያለፈው የካቲት ወር ግንባሩ ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦች አቅርበው ነበር።

ጠቅላላ ጉባኤው ካሳለፋቸው አበይት ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ቻፕተሮቹን ወክለው ወደግንባሩ የተጓዙ አባላት ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት 17 በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የግንባሩ የበላይ አመራር አካል የሆነው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዲገቡና የራሳቸውን የስራ ክፍፍል አድርገው በዳያስፖራ የሚካሄደውን የድርጅቱን እንቅስቃሴ እንዲያስተባብሩ ነበር። በዚህ መሰረትም ጠቅላላ ጉባኤው የኢህአግን የውጭ ኮሚቴ እንዲመሩ ዶ/ር መሃሪ በላይን መርጧል። ሌሎችን የስራ ሃላፊነቶች ግን የውጭ ኮሚቴው አባላት ተገናኝተው እንዲፈጽሙ ወስኗል።

ሆኖም ከጉባኤው መልስ ከጥቂት ቀናት በኋላ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ በመሻርና የውጭ ኮሚቴ አባላት ሳያውቁ ዶ/ር መሃሪ ወደጎን ተገፍተው ወደግንባሩ እንደገና ደርሰን መጣን ባሉ ሁለት ግለሰቦች አማካኝት አንደኛው በሊቀመንበርነት፥ ሌላኛው በጸሃፊነት ተሹመው፥ ሶስተኛ ሹመት ደግሞ ለሌላ ግለሰብ ይዘው መጡ።
የእነዚህ ሶስት ግለሰቦችን ስብስብም የውጭ ኮሚቴው ስራ አስፈጻሚ በማለት በራሳቸው ቡራኬ ሰጡት። ለተቀሩት አባላት ደግሞ ሹመት አርከፈከፉ። በዚህ ሁኔታ ተሾምን ብለው ራሳቸውን ያቀረቡት ግለሰቦች ኮ/ል ጌትነት ሊበን እና አቶ ጥላሁን ገላው ናቸው።

እንደነዚህ አይነት ግንባሩን የስልጣን መረማመጃ ለማድረግ የሚጥሩ ግለሰቦች ባለፉት አምስት አመታት ኢህአግ የሚያደረገውን እንቅስቃሴ ሲያሰናክሉና እንቅፋት ሲፈጥሩ፥ አባላትን ሲከፋፍሉና ሲያጣሉ፥ ብሎም ድርጅቱ ውስጥ ሙስና እና ንቅዘት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም ከግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ በድብቅ እየነጣጠሉ ከተለያዩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በግል በመገናኘትና ጉቦ በመስጠት የራሳቸውን ውሳኔ እያስወሰኑ ከጉባኤ ውሳኔ ውጭ መሪዎች እኛ ነን በማለት ላለፉት 6 ወራት የግንባሩ እንቅስቃሴ ተሽመድምዶ እንዲቆይ አድርገዋል። ይህን ህገወጥ ድርጊት የተቃወሙ 4 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሶስቱን ሹመኞች አመራረጥና አሿሿም አንቀበልም ብለው ከጅምሩ አቋም ወስደዋል። ሌሎች 10 አባላት ህግወጥ ድርጊቱን ቢቃወሙም መተዳደሪያ ደንብ ጸድቆ በዚያው መመራት እስኪቻል ድረስ ስራ እንዲካሄድ ወስነው መሰብሰብ ጀመሩ።

በዚህ መልክ ከላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ሰብሳቢነት ላለፉት 6 ወራት የውጭ ኮሚቴው ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም በኮ/ል ጌትነት ዳተኝነትና የስልጣን ስግብግብነት ብሎም በአቶ ጥላሁን ገላው ስርዓተ-አልበኝነት ምክንያት ምንም ስራ መስራት አልተቻለም።

ስለዚህም በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ የኢህአግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፥ እንዲሁም የአፍሪካ፥ አውሮፓ፥ አሜሪካና ካናዳ የቻፕተሮች ተጠሪዎችና አባሎቻቸው ዛሬ እሁድ ነሀሴ 1 ቀን 2010 ጉባኤ ጠርተው ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፈዋል፤

1. የኢህአግ ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በዳያስፖራ የሚገኙ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የውጭ ኮሚቴውን አደራጅተው ጉባኤው በመረጣቸው በዶ/ር መሃሪ በላይ ሰብሳቢነት ስራቸውን ዛሬ ነገ ሳይሉ እንዲጀምሩ።

2. ከአንዳንድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የድብቅ ግንኙነት በማድረግና እጅ መንሻ በመስጠት ህገወጥ በሆነ ሁኔታ መሪዎች ሆነን ተሹመናል እያሉ ውዥንብር የሚፈጥሩት ጠቅላላ ጉባኤ ያልመረጣቸው ኮ/ል ጌትነት፥ አቶ ዘውዳለምና አቶ ጥላሁን ይቅርታ ጠይቀው ወደኮሚቴው እንዲመለሱና ለጉባኤው ውሳኔ ተገዢ እንዲሆኑ።

3. የሁለተኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ይከበሩ የሚል ጥያቄ ባነሱ አባላት ላይ እነዚሁ ሶስት ግለሰቦች የሚያካሂዱትን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያቆሙ።

4. የኢህአግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከኢትዮጵያ ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ግንኙነት ማድረግ የሚገባቸው በሁሉም ቻፕተሮች ድጋፍ ባለውና በህጋዊነት ከተደራጀው የውጭ ኮሚቴ ጋር ብቻ እንዲሆን።

5. በቅርቡ ለንደን ከተማ ውስጥ በድርጅቱ ስም የተጠራው ስብሰባ የውጭ ኮሚቴውና የዩ.ኬ. የኢህአግ ቻፕተር ያልወሰኑበት፥ ኢህአግን የማይወክል፥ የተዘጋጀውም ግንባሩን መነገጃ ለማድረግ በተነሳሳ አንድ ግለሰብ መሆኑ እንዲታወቅ። ከዚህ በፊት በዚሁ ግለሰብ አማካኝነት በለንደን ተመሳሳይ ስብሰባ በመጥራት ውዥንብር ለመፍጠር ሙከራ ተደርጎ ለንደን በሚገኙ የዩ.ኬ. ቻፕተር አባላት ጠንካራ ጥረት መክሸፉ ይታወሳል።

6. ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢህአግ ስም ከተሰበሰበው ገንዘብ አብዛኛው ለሰራዊቱ ጥቅም አለመዋሉ በበቂ ማስረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል። ከዳያስፖራ የተሰበሰበ ገንዘብ የዋለው ለጥቂት የአመራር አባላት የግል ጥቅም ሲሆን ይህም የገንዘብ ምንጭ እንዳይደርቅ ሲባል በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ የድርጅቱ ደጋፊዎች በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው እየተበጣበጡ እንዲቀጥሉ ዘዴ ተቀይሶ ቆይቷል። ይህም ዳያስፖራው የሚያዋጣው ገንዘብ ባክኖ እንዲቀር አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህን ወንጀል እያወቁ ርካሽ የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ እነኮ/ል ጌትነት ራሳቸውን መጠቀሚያ በማድረግና የዚህ ሙስና ተባባሪ በመሆን በሰራዊቱ ላይ ሲቀልዱ ቆይተዋል። ስለዚህም የውጭ ኮሚቴው ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ከግንባሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጋር ስራውን በማቀናጀት አስተማማኝነት ያለው የሂሳብ አያያዝ እስኪያበጅ ድረስ በኢህአግ ስም በየትኛውም ሀገርም ሆነ ከተማ ገንዘብ እንዳይሰበሰብ። እስከዛው ድረስ በኢህአግ ስም ገንዘብ የሰበሰቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁሉ የሰበሰቡትን ገንዘብ በአግባቡ ለኢህአግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ እንዲያስረክቡና የገንዘብ ርክክቡ በኦዲተር ተመርምሮ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ብሎም ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት እንዲቀርብ።

7. የኢህአግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ዳያስፖራ ከሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ገንዘብ እየተቀበሉ ኪሳቸው የሚያስገቡ አንዳንድ አባላት እንዳሉ ማስረጃዎች ተገኝተዋል። ይህም በግንባሩ ውስጥ ንቅዘት የሚያስፋፋ በመሆኑ እንደዚህ አይነት ሙስና የሚፈጽሙ በግንባሩ ያሉ የአመራር አባላት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ። ከዚህ በተጨማሪ አብዛኛው የኢህአግ መሪዎችና አርበኞች በየዱር ገደሉ ከወያኔ ጋር ሲፋለሙ እነዚህ ጥቂት ድርጅቱን የግላቸው አክሲዮን ማህበር ያደረጉት የአመራር አባላት ለፍርድ እንዲቀርቡ። (ስማቸው ካስፈለገ በቅርቡ ይፋ ይሆናል)

8. የኢህአግን ሚስጥራዊ ሰነዶች ከዋና ጽህፈት ቤት አውጥተው በዳያስፖራ ላሉ ግለሰቦች ለጥቅማጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ፥ እንዲሁም የግንባሩን ማህተም በመጠቀም አደናጋሪ ደብዳቤ ከግንባሩ የስራ አሰፈፃሚና የውጭ ኮሚቴ እውቅና ውጭ እንዲወጣ የሚያደርጉ የአመራር አባላት እንዳሉ ተደርሶበታል። ይህ ጉዳይ በልዩ አጣሪ ኮሚቴ ታይቶ እርማት እንዲደረግበት።

9. የኢህአግ ጠቅላላ ጉባኤና ሌሎችም ግንባሩ ያካሄዳቸው ስብሰባዎች ላይ ትኩረት የተጣለበትና በዳያስፖራ በሚገኙ የኢህአግ ቻፕተሮች ቀደም ሲል የተጀመረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን የሚያቀራርቡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በስፋት እንዲቀጥሉ።

10. በሁለተኛው የኢህአግ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጉባኤው ያልመረጣቸው ግለሰቦች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሆነው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህን የሚያደርጉ የአመራር አባላት ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ።

11. ኢህአግ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ከጣለባቸው ድርጅቶች አንዱና አንጋፋው ሲሆን ይህን ድርጅት መነገጃና የስልጣን መረማመጃ ለማድረግ አሰፍስፈው ከሚጠብቁ ሰረጎ ገቦች፥ እንዲሁም ከወያኔ ቅጥረኞች ለመከላከል ሁሉም አባላት በያሉበት ነቅተው እንዲጠብቁ።

12. ኢህአግ ተጠናክሮ የቆመለትን ዓላማ እንዲመታ የሚያስችለው ብቃት ያለው አመራር ያስፈለገዋል። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የበላይ አመራር አካሉ የሆነው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የተለያዩ ችሎታዎች ያሉአቸውን አባላት ከዳያስፖራ ማስገባቱ እንደአንድ ትልቅ እርምጃ ተቆጥሮ ተመሳሳይ ማሻሻያዎችና ለውጦች በግንባሩ ውስጥ እንዲካሄዱ።

13. ኢህአግ ከሌሎች ጸረ-ወያኔ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ህብረት የሚፈጥርበት ሁኔታ ላይ ከመቼውም ይበልጥ ጠንክሮ እንዲሰራ።

14. ጀግናው የኢህአግ ሰራዊት የደምና የአጥንት እንዲሁም የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ባለበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቹን በቂ የሞራልና የማቴሪያል እርዳታ ሊያገኝ አልቻለም። ይህ የሆነበት ምክንያት የተለያየ የግል ፍላጎትና ተልዕኮ ይዘው ወደድርጅቱ ጠጋ የሚሉ ሰርጎ ገቦችና ያደፈጡ ሴረኞች በሚፈጽሙት እኩይ ተግባርና አንዳንድ የአመራር አባላት በሚያሳዩት የስነምግባር ጉድለት መሆኑ ግልፅ ነው። ለኢህአግ ሰራዊት በዚህ አጋጣሚ የምንገባው ቃል ቢኖር አርበኛው ከእንግዲህ ወዲያ የጥቂት ግለሰቦች መነገጃና የስልጣን ጥም ማርኪያ እንዳይሆን በጽናት እንደምንታገል ነው።

አንድነት ሃይል ነው
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

የኢህአግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የውጭ አመራር አባላት
የኢህአግ ቻፕተሮች በዳያስፖራ