እንኩዋኔም መሃይም ሆንኩ ( ሄኖክ የሺጥላ )
የ ምርጫ ዘጠና ሰባት ሕልፈት ሕይወት የ አዲስ አበባን ወጣቶች ከምርጫ ወደ በርጫ በብርሃን ፍጥነት ሲመራቸው ቅንጅትም ከመንፈስነት ወደ ፈስነት የሄደበት መንገድ እንዲሁ ተመሳስይ ነብር። ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ነብር ሆነው የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች ከነብርነት ወደ ነበርንነት ፣ ቁልቁል ተንደርድረው ከዝግባነት ወደ ዘጋቢነት የተሸጋገሩበትን እጻዊ ( ምጸታዊ ጡዘት ) መንፈስ እና መንፈሰ ግስጋሴ ሳስበው ይገርመኛል። በምርጫው ዘመን የነበረው መንፈስ፣ ቀሳውሥቱና መነኮሳቱ፣ ዘማሪውና ደብተራው ፣ አዝማቹና ዘማቹ፣ ሰልፉ ፣ ጩኸቱ ፣ አሪታው ፣ ግድያው ፣ እስሩ፣ እንግልቱ፣ ሁሉም ጆሮዬ ላይ ያቃጭሉብኛል። እና የውስጥ ለውስጥ ህመም ያመኛል። አቦጊዳ ሄውዞ ፣ በጉዲሃ ወይጦ፣ የሚለው የልጅነት ሪትሚካል እውቀት ዛሬም አእምሮዬ ላይ የሚያቃጭለውን ያህል። የምርጫ ዘጠና ሰባት ለኔ የተለየ ትርጉም አለው። እኔ እና ጉውደኛዬ ( ስለሺ መከተ )፣ እነ ብርሃኑ ነጋ ፣ እነ ኃይሉ ሻወል ፣ እነ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ እነ ወዘተ ፣ ለምን ታሰሩ ፣ ነብዩ ለምን ተገደለ ብለን ነበር በግዜው በ ከተማው ውስጥ ለውስጥ ይወራለት የነበረውን የአርበኞች ግንባር ለመቀላቀል ወደ ጎንደር ያዘገምነው። ጎንደር ውስጥ በቆየንበቸው ጊዜያቶች የጎንደር ህዝብን ቅን አንጀት ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ሰው ወዳድነት ሳላመስገን አላልፍም። እና የ አርበኝነት ጀብዱዬን እዚህ ጋ ልግታው ( ምክንያቱም የሽንፈት ታሪክ ቢያወሩት ለዝና ቢወረወሩት ለጉራም አይሆንም እንዲሉ ) ነውና። እና ምርጫ ዘጠና ሰባትን ሳስብ የኢህአዲግ ልዩ ምልክት የነበረው ንብ ትዝ ይለኛል። አዋ ከደቡብ የቀሰመውን አበባ ትግራይ ላይ ነጭ ማር የሚሰራው ንብ። በነገራችን ላይ ፣ አሁን እሱም ” በክልልህ ቅሰም” ተብሎ ፣ የሚቀስመው ስላጣ ሀገር ባህል ላይ ያለውን አበባ ቀስሞ ኖሮ ገበሬው ማር ሊቆርጥ ቀፎውን ቢገፋው አሉ ” ቱባ ቱባ ክር !”።
እባካችሁ ልቀቁት እሱም የሚያምርበት እንደናነት ሲሰርቅ ነው ፣ ካልሰረቀ ጠብሽ ነው፣ ሊያውም የ ቱባ ክር ጠብሽ። እንዴት እንደዘነጉት እንጃ እንጂ ካልሰረቅ የነሱ ንብ ከዝንብ አይሻልም ። መቼም ይሄ አይጠፋችሁም። እንደምኞትና ፍላጎትማ ፣ ወልቂጤ የበቀለው ሙዝ አንገቱ ትግራይ ላይ ቢቆለመም ምኞታችሁ ነበር ግን አይሆንም ፣ አይቻልም ፣ እግዜር እምቢ አለ ። ያ ባርያ “አይዘራበት! አይጎለጎልበት ፣ አይወቃበት !” ነበር ያለው ። ግን እኛ ምን ነክቶን ነው። ግን እኮ ለጊዜውም ቢሆን የጎንደርን ደን ለትግራይ ፍጆታ ስትመነጥሩ እኔ ራሴ ቁዋሚ ምስክር ነበርኩ፣ እኔ ጫካ ልገባ ፣ እናንተ ደሞ አብረሃጅራ ላይ ወዝ አደር ፈልጋችሁ ተገናኝተን ነበር። እኔ ምስክር ነኝ ፣ የ አብደራፊን እጣን ፍቃችሁ ( አስፍቃችሁ ) ስትጭኑ፣ እኔ ምስክር ነኝ ዛሬ ለሱዳን የሰጣችሁትን መሬት የቅየሳ ሥራ ስትሰሩ ፣ አጠገባችሁ ነበርኩ ፣ አይ አልነበርክም ካላችሁ ከ ሳንጃ እርጎየዎች እየተመላለሰ ይቀይስላችሁ የነበርውን ሙስሊም የጎንደር ልጅ ጠይቁት !
እና የምርጫ ዘጠና ሰባት መጀመሪያ ለአፍ እላፊ ከዚያ ደሞ ለሰዓት እላፊ እንደዳረገን መቼም ቢሆን አንረሳውም። እንደውም እንደ ቀልድ ተነግሮ በሁዋላ ግን በተግባር የተተገበርውን ቀልድ ሳስበው ይገርመኛል። የቅንጅት ምልክት የነበረው የድል ” ቪክትሪ ” ምልክት የሆነው የ አመልካች ጣትና የመሃል ጣት ሲሆን ፣ በጊዜው የነበሩ የወያኔ ደጋፊዎች ለቅንጅት ደጋፊዎች ይሉዋቸው ከነበረው ነገር ውስጥ አንዱ ” ይሄን ጣትህን የዛሬ ዓመት ለ ሲጋር ትጠቀምበታለህ ” ነብር ፣ ያሉት አልቀረም ፣ ወያኔ ጣቶቹን ገጥሞ ተኮሰ፣ ተቃዋሚውም እንዲሁ ጣቶቹን ገጥሞ እሳት ለሲጋራ ለኮሰ። እና ዛሬ ሁሉን በትዝታ እያወራን ቁጭ ብለናል ። እድሜ ለጊዜ ” ወይም ግዕዝ ደጉ ጊዜ ለኩሉ ” ይለዋል ፣ ትናንት የጮኸንላቸው ዛሬ ከሀርፋርድ ተመረቁ፣ ነብዩ ተጎዳ እንጂ፣ ትናንት ትምርታችንን ያቆምንላቸው ዛሬ ተምረው ፣ ለወግ ለማረግ በቅተው አሳዩን ፣ ወንድሜ ሥለሺ ተጎዳ እንጂ ፣ ዶክተሮቹም እያከሙ ፣ ኢንጂነሮቹም ከስህተታቸው ታርመው ፎቅ መስራት ጀመሩ ፣ ልማታዊ ሆኑ ፣ እኔ ጅብራሬም ከነ ሊቀመ ኩዋስ ጋ መሞዳሞድ ጀመሩ፣ የምርጫ ዘጠና ሰባት ሂደትና ድምዳሜ።
በመሰረቱ አጋጣሚን አላማው ያደረገ ታግይ ስትከተል ከዚህ የተሻለ ነገር ሊገጥምህ አይችልም። አንዳንዴ ሳስበው እንደውም እንኩዋንም መሃይም ሆንኩ እላላሁ፣ ምክንያቱም ብማር ኖር እኔም አጋድዬ እንጂ ተጋድዬ ለውጥ ማምጣት ባላሰብኩ ነበር። አሪፍ ሊቀመ ኩዋስ በሆንኩ ነበር። ግን ትግል የሚጀምረው ከራስ እንደሆነ ደሞ ትንሽም ቢሆን አውቃለሁ። ለብራ ያለን ፍቅራችን ሳይቀንስ እንዴት ጫከኛ መሆን ይቻላል። ሰው እንዴት ቁርጥ እያሰበ መታገል ይችላል፣ ነጻነት የህሊና እኮ ነው ፣ መጀመሪያ ራስን ከአካባቢያዊ ተገዥነቶች ነጻ ማውጣት ያስፈልጋል ። ክርስቶስ እንኩዋ በኔ ያመነ መስቀሉን ይዞ ይከተለኝ ነው ያለው።
እና ትናንት የተከተልናቸው ፣ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ብለውን ፣ ዛሬ ከላቀው የእውቀት አምባ ገብተው በ ዲግሪ ላይ ዲግሪ እየደራረቡ ፣ ያ የተሸነፉበት ጣታቸውን ቀስረው ፣ አሸወይና ወይናዬ ይሉናል፣ ወንድሜ ስለሺ ግን እነሱን ብሎ ፣ ከትምህርት ገበታው ተፈናቅሎ ፣ አስመራ የሽንኩርት ማሳ ሲጠብቅ እንደኖረ ሳስብ ይዘገንኑኛል፣ ያሙኛል። የ አስራት ወልደየስን መስዋትነት ሳስብ ፣ የ አሰፋ ማሩን አሙዋሙዋት ሳስታውስ፣ እነ መቶ አለቃ አብዮት ማንዳፍሮን ሳስታውስ ፣ ይሄ የ ሃርቫርድ ድግሪ ፣ ይሄ የእንግሊዝ ስኮላር ሺፕ ፣ እንደ ሺፕ ሥለማሰባችን የተሰጠን ሽልማትም ይመስለኛል። ወይዘሪት ብርቱካን ከሀርቫርድ ብትመረቅ ፣ ልደቱ እንግሊዝ ሀገር ሄዶ ገለመኔ ከሚባል ዩኒቨርስቲይ ቢመረቅ ፣ ከተነስሉለት አላም እና ከደረሱበት ደራጃ አንጻር እንደሰው ጥፍር ውስጥ የሚከት እንጂ ጸናጽል የምናንሸዋሽውለት፣ እጣን የምናጥንለት ፣ ከበሮ የምንደልቅለት ቅድስና አይደልም። ብርቱካንን ስናወድስ እያልን ያለነው እኮ እስክንድር ምን ትጠብቃለህ ነው። ነጮች ከኢትዮጵያውያኖች ልብ ውስጥ አጥበው / ጠርገው ማውጣት የሚፈልጉት ምንን ይመስልሃል። እንደሰው ሌላው የአፍሪካ ነገድ የሌለው አባቶች የነበራቸው ውድ ስብእና ” እምቢ!” የሚለው ማንነት ነው ። እሱን ሙሉ በሙሉ ስታጣ ሰውነትህን ታጣለህ። ያባቶችህ እምቢ ውስጥ አንተ አለህ ፣ የ ቴዎድሮስ እምቢ ውስጥ አስክንድር ነጋ አለ፣ የሚኒሊክ አሻፈረኝ ውስጥ አንዱዓለም አራጌ አለ ፣ የሃብተግዮርጊስ እልህ ውስጥ ርዮት አለሙ አለች ። እኔ እማውቀው ይሄንን ነው፣ እኔን የሚገባኝ ይሄ አይነቱ ኢትዮጵያዊነት እንጂ የሃርቫርድ ዔጵስ ቆፖስነት አይደልም። አይበቃም ?
እና ስለ ምርጫ ዘጠና ሰባት ሳስብ ፣ ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል፣ ዛሬን ሳስብ ሁሉም ነገር ድብልቅልቅ ይልብኛል። ስለ ምርጫ ዘጠና ሰባት ሳስብ ዶር በየነ ጴጥሮስና ዶ/ር መራራ ጉዲና ትዝ ይሉኛል ከዚያ ትዝታቸው አግራሞትን ይጭርብኛል ፣ እንደገና እንኩዋንም መሃይም ሆንኩ እላለሁ። እንደዚህ የከሸፈ ምሁር ከምሆን ፣ አለማወቄን አመሰገንኩ። ዛሬም ሽንፈታቸውን ሳይሆን በደላቸውን ሊነግሩን ሲያስቡ ” ቀሽም ” የሚለው ቃል ጭንቅላቴ ላይ አቃጨለብን። አዲስ አበባ ተወልደህ ካደቅ ደሞ እንዲህ
…