በጥቁር ፕሮፓጋንዳ የማይጨፈለቀው ብርቱካናዊው መንፈስ!

ከስለሺ ሃጎስ (መርሕ ይከበር)

ሰሞኑን ከተከናወኑ ትልልቅ መንግስታዊ ክንዋኔዎች ይልቅ የሀገሪቱ ዋነኛ አጀንዳ ለመሆን የቻለው ወሬ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከእስር መፈታትና የተፈታችበት ሁኔታ ነው፡፡ (አንቺ ብዬ የምጠራት ስለ ፍቅሬ እንጂ ስለ ክብሯማ አንቱታም ቀላል ነው)

ወ/ት ብርቱካን በሲውዲን ለሚገኙ ደጋፊዎቿ ባደረገችው ንግግር ሰበብ ታህሳስ 20፣ 2000 ዓ.ም ለዳግም እስራት ከበቃች በኋላ ስለ እስሯ ህገ ወጥነትና ስለ ጠንካራው ስብዕናዋ በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ ባሉ ትልልቅ መድረኮች ላይ ብዙ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ከራሱ ደጋፊዎችና አባላት ሳይቀር በርካታ ወቀሳና ትችቶች ተሰንዝረውበታል፡፡ አሰርኩበት ካለው ምክንያት በብዙ ዕጥፍ የሚበልጥ ዋጋ ሊከፍልበትም ግድ ያለው ክስተት ነበር፡፡ የወ/ት ብርቱካን እስር፡፡ ከ21 ወራት የእስር ቆይታ በኋላ ግን ረቡዕ መስከረም 26/2002 ዓ.ም “ታላቁ” ና ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደረቱን ነፍቶ ወ/ት “ብርቱካን ¢ተሳስቼ ነበር¢ ብላ መንግስትን ይቅርታ ስለጠየቀች ከእስር ተፈታለች” ሲል ተሳልቆብናል፡፡ ከዚህ ዜና በኋላ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በእንዲህ አይነት ይቅርታ ከእስር ለመውጣት ለምን ፈለገች? የይቅርታው ይዘትስ አላማ ምንድ ነው? በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ የረበበው የነፃነት መንፈስ በጠየቀችው ይቅርታ ሳቢያ ይደበዝዝ ይሆን? ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ጥያቄዎች በአንዳንድ ጓደኞቼ ሲነሳ በመስማቴ በዚህ ጽሁፍ ላይ የበኩሌን ላካፍላችሁ ወድጃለሁ፡፡

ጠ/ሚር ሊገኑ የሞከሩበትን የብርቱካን ይቅርታ

ኢቲቪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽፋዋለች ብሎ ባነበበልን የይቅርታ ደብዳቤ ላይ የሚከተሉት ሀረጋትና ዓ.ነገሮች ይገኙበታል፡፡ “ከቀድሞው የቅንጅት አመራሮች ጋር በመሆን በፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር . . . ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሀገር በሄዱበት ወቅት በበኩላቸው ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ እንደሌለ በማስመሰል መንግስት ይቅርታ ሳልጠይቅ ነው. . . የተሳሳተና በክህደት ላይ የተመሰረተ መረጃ መስጠታቸውን አምነው . . . የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ጠርቶ በድጋሚ የፈጸሙትን ስህተት እንዲያርሙ ተደጋጋሚ ምክር ቢለግሳቸውም . . . ወደዚህ ስህተት ሊገቡ የቻሉት መንግስት የውጭ ሃይሎችን ተፅእኖ በመፍራት ሊያስረኝ አይችልም፣ ካሰረኝም ተገዶ በአጭር ጊዜ ይፈታኛል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን ገልጸዋል. . . የተሰጠኝን ይቅርታ በመካድ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት በማታለሌ…” እነዚህን ሀረጎችና ዓ.ነገሮች የዚህ ጽሁፍ አንባቢዎች እንደምታስተውሉት ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች የወ/ሪት ብርቱካን እስርን አስመልክቶ ለሚሰነዝሯቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ቃል በቃል የተናገሯቸው ናቸው፡፡ ይህን ሁኔታ እንደ ተራ የአጋጣሚ ክስተት ከማየት ይልቅ የይቅርታ ደብዳቤውን ፀሀፊ ማንነት እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳና ጠ/ሚር መለስ በጉዳዩ ላይ ተመሣሣይና ቃል በቃል አንድ የሆነ ሀሳብ ይናገራሉ ብሎ ለማመን የሚያስችል ተመሣሣይ ስብዕናና የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸው በመሆኑ ከዚያ ይልቅ ሚዛን የሚደፋው ጥርጣሬ ደብዳቤው በቀጥታ ከዚያ ከምናውቀው ቢሮ ተጽፎ እንድትፈርምበትና ሸምድዳ በማነብነብ በካሜራ እንድትቀረጽ መደረጉ ነው፡፡ ይህ ጥርጣሬ እውነትነቱ የሚያመዝንበት በርካታ ምክንያቶች በመኖራቸው ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሚለው ነው፡፡

ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ እስሯን አስመልክቶ የተናገሯትን እያንዳንዷን ዓ.ነገር እውነትነት ቃል በቃል እንድታረጋግጥ የተደረገው የህግ የበላይነትን ሣይሆን የእሳቸውን ቃል በማስክበር በኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛና ጽኑ ሰው (አንድ ለእናቱ) እሳቸው ብቻ መሆናቸውን በግድ እንድናምን ለማድረግ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አያስቸግርም፡፡ በተለይ ደግሞ በየመንገዱ በትልልቅ ቢል ቦርዶች ፎቷቸው እየተሰቀለና የተለያዩ ከናቴራዎችና የቁልፍ መያዣዎችን ከእሳቸው ፎቶ ጋር በማተም በነፃ እየታደለ ሊገነባ ከሚሞክረው የራስ ማንነት ግንባታ (personality cult) ጋር አያይዘን የወ/ት ብርቱካንን የይቅርታ ደብዳቤ ይዘት ስንመረምር ነገሩ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፡፡

የዚህ ሙከራ ድምር ውጤት ደግሞ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካዊ አመለካከት ወዘተ ሳይገድበው አዲሱ ትውልድ ወ/ት ብርቱካንን እንደ ራሱ ወኪል አድርጎ መቁጠር በመጀመሩና አዲስ የነፃነትና የጽናት መንፈስ በወ/ት ብርቱካን በኩል በሰፋት እየተቀጣጠለ በመምጣተቱ ይህን ጥልቅና ሰፊ ብርቱካናዊ መንፈስ በመጨፍለቅ በምትኩ መለሳዊነትን ለመተካት የተደረገ ከንቱ ሙከራ መሆኑን የማያውቁ ማወቅ ያልፈለጉት ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ግን እንዲህ እንላለን “በምኞትና በተስፋ አምጠን የወለድነውን መንፈስ ከኢቲቪ ጋር ተባብረን የምንገድል እፉኝት አይደለንም፡፡

ይሁን እንጂ የትኞቹም አምባገነን መንግስታት በሚተገብሩት አኳኋን ኢህአዴግም በዚህ መንገድ መጓዙ የሚገርም ባይሆንም በአጽንኦት ሊታዩ የሚገባቸው ነጥቦች ወ/ት ብርቱካን በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከእስር ለመውጣት ለምን ፈለገች? ለዚህ ለዚህማ ቀድሞውንም አስተባብላ ከእስራቱ ለምን አላመለጠችም? የሚሉት ናቸው፡፡ የነገሩ ስረ ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ የወ/ት ብርቱካን ህይወት መደምደሚያና የአላማዋ ፍጻሜ እንቢ ማለት ወይም አይበገሬነቷን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትን በማጎናጸፍ የሀገሩና የስልጣን ባለቤት ማድረግ ጭምርም እንደሆነ ከተግባሮቿ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አይበገሬነቷንማ በቃሏ ብቻ ሳይሆን በጨለጠቻቸው መራራ ጽዋዎች ማስመስከሯን ደጋፊዎቿ ብቻ ሳይሆኑ ተቃዋሚዎቿም ጭምር እየተናነቃቸው የዋጡት ደረቅ ሀቅ ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው ወ/ሪት ብርቱካን እስር ቤት ሆና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል በጽናት መርቶ ለድል የሚያበቃ መሪ በመጥፋቱ ኢህአዴግ የ99.6% የፓርላማ ወንበር አሸናፊ መሆኑ ታውጇል፡፡ በተለይም የአዲሱ ትውልድ አባል የሆነው ወጣቱ ያለ እረኛ እንደተተወ መንጋ በቁጭትና በተስፋ መዋተት እጣፈንታው መሆኑ አሳዛኝ አጋጣሚ ነበር፡፡ በእኔ እምነት ይህ ወጣት የሚሰበስበው፣ አደራጅቶ የሚያታግለው በመጨረሻም ለድል አብቅቶ የሀገሩ ባለቤት የሚያደርገው መሪ በናፈቀበት በዚህ ጊዜ ወ/ሪት ብርቱካን ቀደም ሲል ለእስር ስትዳረግ ከነበረው መከራ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ አንገፍጋፊ መስዋዕትነት ከፍላ (የተጠቀሰው ድርሰት ላይ ፈርማም ቢሆን) ከእስር መውጣት ግዴታዋ ነበር፡፡ ይህንንም አድርጋዋለች፡፡ ይቅርታዋ የሚነግረን ኢህአዴግ ሊያስተላልፍ ከሞከረው መልዕክት ይልቅ የወ/ሪት ብርቱካንን ታላቅነት ነው፡፡ ከዚህም በላይ የታጠቀችው የሞራል ሰይፍ ባለ ሁለት ስለት ሆኖ እምቢም እሺም ብላ የምታሸንፍ ዘመናዊ ጀግና መሆኗን ይቅርታዋ ጮክ ብሎ ይናገራል፡፡ ይህ እንዳለ ሆነ የይቅርታ ሂደቱ የኢህአዴግ ሰዎች ለዝንት አለም በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ከህሊናና ከሞራል በታች በሆነ ቅርቃር ውስጥ ገብተው የተከበረውን የሀገራችንን የይቅርታ ባህል ወደ ተራ የፖለቲካ ጥቅም ማግኛነት እየለወጡት መሆኑን ማሳበቁ አልቀረም፡፡

የይቅርታ ክብር የት ገባ?

ይቅርታ በሀገራችን የተከበረ ባህል መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቋንቋን፣ ጎሳንና ሃይማኖትን ዘሎ በአራቱም መዕዘናት በድፍን ኢትዮጵያ የሚተገበርና ከምንም በላይ የሚከበር ባህል ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያዊነትን አንድ አድርገው ከሚያስተሳስሩ እሴቶች መሀከል የሚመደብ በመሆኑ በመንግስታዊ መዋቅርም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነበር፡፡ አሁን ድረስ የፍትህ አካላት በተፃፈ ዘመናዊ ህግ በዘላቂነት ሊፈቷቸው የማይችሏቸውን ውስብስብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግጭቶችን በመፍታት የማይናቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ያለ ባህላችን ነው፡፡ ወፍራም አለንጋ ያለው ባለጡንቻ ይቅርታ የሚጠየቅበት አቅመቢሱ ብቻ የሚጠይቅበት የጉልበት ህግ ሳይሆን ያጠፋ ክሶ የተበደለ ተክሶ ከዚያ በኋላ በዳይና ተበዳይ በፍቅር የሚኖሩበት ፍትሐዊ ተግባር ነው፤ ይቅርታ፡፡

አሁን አሁን እያየን ያለነው ግን በዳዩ አካል ወፍራም አለንጋ ስላለው ብቻ እራሱ ገርፎ እራሱ ይቅርታ አስጠይቆ እራሱ ይቅር ብሎ ሰጥ ለጥ ለማድረግ የሚሞክርበት ርካሽ ክንዋኔ እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ ለዚህ አስረጅ ለመፈለግ ሌላ ጉዳይ ላይ መኳተን ሳያስፈልግ የወ/ት ብርቱካንን የይቅርታ ሂደት ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ዓለም እንደመሰከረው ያለ ሕግ ከመንገድ ላይ ታፍሳ ለእስር የተዳረገችው፣ ለአምስት ወራት በጨለማ ቤት የተጣለችው፣ በፍ/ቤት የተወሰነላትን የመጎብኘት መብት የተነፈገችው፣ የሦስት ዓመት ሕፃን ልጇንና አዛውንት እናቷን ባዶ ቤት ጥላ ለ19 ወራት እስር ቤት የከረመችው እራሷ ወ/ሪት ብርቱካን ሆና ሳለ ይቅርታ እንድትጠይቅ መገደዷ የተከበረው የሀገራችን የይቅርታ ባህል ከላይ በተጠቀሰው መልኩ እየተገለበጠ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ይህን ጽሁፍ ለማሰናዳት የወ/ት ብርቱካንን ይቅርታ ሳሰላስል በተደጋጋሚ በአእምሮዬ ይመላለስ የነበረው የእማማ አስካለ ሁኔታ ነው፡፡ እማማ አስካለ ጎረቤታችን ነበሩ ውሃ ቀጠነ ብለው ከሰፈሩ ሰው ጋር ሁሉ የሚጣሉ ሰው በመሆናቸው ስድባቸውን ያልቀመሰና አሽሙራቸው ያልደረሰው ጎረቤት የለም፡፡ ታዲያ እማማ አስካለ ከሰው ጋር ተጣልተው በበሸቁ ቁጥር ንዴታቸውን የሚያበርዱት አሸናፊ የተባለ የልጅ ልጃቸውን ያለ ጥፋቱ በመቆንጠጥ ነው፡፡ እሳቸው ከሰው ጋር በተጣሉ ቁጥር አሸናፊን ሲቆነጥጡ እኔነኝ ያለ ገላጋይ እንኳን አያስጥላቸውም፡፡ ጣቶቻቸውን ከጭኑ ስር የሚያነሱት “እማይዬ አይለመደኝም . . . ሁለተኛ አይለመደኝም” እያለ ሲጮህ ብቻ ነው፡፡ አሸናፊ አይለመደኝም ያለው ምን እንደሆነ ቢጠየቅ ግን መልስ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ብቻ ግን አይለመደኝም ብሎ ከሚያደብነው ቁንጥጫ ይገላገላል፡፡

ይህን የልጅነት ትውስታዬን ገጽ አጣብቤ ያስነበብኳችሁ እኛ የእማማ አስካለ ጎረቤቶች አሸናፊ ያለ ጥፋቱ ተቆንጥጦ ያለ ጥፋቱ አይለመደኝም በማለቱ እሱን እንደ ጥፋተኛ ከመቁጠር ይልቅ የእማማ አስካለ ያልተገባ ድርጊት እንደሚቀፈን ሁሉ በወ/ት ብርቱካን ላይ እየሆነ ያለው ነገር ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ሆኖ እያለ መንግስታችን የእማማ አስካለን አይነት ትዝብት ውስጥ ለመውደቅ ለምን እንደመረጠ ሊገባኝ ስላልቻለ ነው፡፡ እንጂማ ወ/ሪት ብርቱካን በቁንጥጫ ብዛት የማትንበረከክ መሆኗን ማንም ሊመሰክረው እንደሚችል ጠፍቶኝ አይደለም፡፡

በመጨረሻም

በመላው ሀገራችን በወ/ሪት ብርቱካን በኩል የተንሰራፋው የነፃነትና የጽናት መንፈስ የአንድ ሰው ጉዳይ አይደለም የወደፊቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትገነባበት ሀገራዊ መንፈስ እንጂ፡፡ ይህ መንፈስ በሁላችንም ያደረ፣ ባላደረባቸውም ሊያድር የሚገባ የተስፋ መንፈስ ነው፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን በአንደበቷ “አንዳንዴ የምታሰርለት አንዳንዴም የምፈታለት” ብላ ለገለጸችው ሀገራዊ አላማዋ በዘመናችን ያልታየ መስዋዕትነት ከፍላ ለእስር እንደተዳረገች ሁሉ አሁን ደግሞ በእኔ እምነት ለቀደመ አላማዋ በነፃ ሳይሆን የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍላ ከእስር ተፈታለች፡፡ ቀሪው የቤት ስራ ደግሞ የተከታዮቿ ነው፡፡ አንድ ትውልድ እውነተኛ መሪውን ለመፍጠር ለመሪው የሚመጣውን ሁሉ መስዋዕትነት መክፈል የሚጠበቅበት በመሆኑ ይህን ተግባር ለመፈጸም መዘጋጀት ለድል ያበቃል፡፡ ያኔ ይህ ሰፊና ጥልቅ ሀገራዊ መንፈስ እልፍ አእላፍ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ቢከፈትበትም እየፈካ ቢሄድ እንጂ ፈጽሞ ሊደበዝዝ አይችልም፡፡ ብራቮ ብርቱካን!!