ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለመመደብ ያቀረቡትን ጥያቄ ቅ/ሲኖዶሱ ውድቅ አደረገው – ‹‹ለምነው አብረውኝ ይሥሩ ያሏቸውን ሊቀ ጳጳስ በመገፍተር ኃይልዎን ማሳየትዎ እንዴት ነው የሚገፋው?››

  • በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመራው በቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ሊቀ ጳጳስ እንጂ በፓትርያርኩ የምደባ ምክረ ሐሳብ አለመኾኑን በመጥቀስ ነው ጥያቄአቸው ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረው፡፡
  • ከዚህም ባሻገር የብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከሓላፊነት መልቀቅ ምክንያታዊ ማብራሪያ እንደሚያስፈልገው ምልዓተ ጉባኤው ፓትርያርኩን በማሳሰቡ ለአ/አበባ ሀ/ስብከት የሊቀ ጳጳስ ምደባ አልተደረገም፡፡
  • ምልዓተ ጉባኤው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሓላፊነታቸው እንዲቆዩ ለማግባባት ጥረት ያደረገ ቢኾንም ከአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱና ከፓትርያርኩ አላስፈላጊ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ጋራ በተያያዘ በተደጋጋሚ እያገረሸ በሽምግልና ሲፈታ የቆየው አለመግባባት እልባት ሊያገኝ አለመቻሉ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

Holy Synod08

  • የፓትርያርኩ አቋም ካሳዘናቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው ሲናገሩ፡- ‹‹ገና አንድ ዓመት ሳይሞላዎት ለምነው አብረውኝ ይሥሩ ያሏቸውን ሊቀ ጳጳስ በመገፍተር ኃይልዎን ማሳየትዎ እንዴት ሥራ ኾኖ የሚቀጥለው? ከወዲሁ እንዴት ነው የሚገፋው?›› ብለዋል፤ ንግግራቸውም እንደተፈጸመ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት ባልተመለደ አኳኋን በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
  • ከአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት ዝግጅቱ ጋራ በተያያዘ በተፈጠሩ አለመግባባቶችና በተደረጉ ሽምግልናዎች መካከል ፓትርያርኩ ብፁዕነታቸውን ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባል ነዎት ወይ?›› ብለው እስከ መጠየቅ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡
  • የአ/አ ሀ/ስብከት እስከ ጥቅምት ፳፻፯ ዓ.ም. የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያለሊቀ ጳጳስ ሊቆይ ይችላል፤ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ ከትግበራ እንደታገተ ነው፤ ለውጡን በመደገፍ የተንቀሳቀሱ አገልጋዮችም ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡
  • የብፁዕነታቸውን ከሓላፊነት መልቀቅ፣ ከምልዓተ ጉባኤው ቁጥጥር ውጭ የኾኑት ፓትርያርኩ፣ በብፁዕነታቸው ላይ ‹‹ከቅ/ሲኖዶስ አባልነት እናወርዳቸዋለን፤ ወደ ጅማቸው እንመልሳቸዋለን›› እያሉ ሲዝቱ ከነበሩ የሀ/ስብከቱ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች የፈጠሩትን ቁርኝት ያረጋገጠ ኾኗል፡፡