ቅ/ሲኖዶስ በመንግሥት ተወርሰው ስላልተመለሱ ቤቶችና ሕንፃዎች የተሟላ መረጃና ሪፖርት እንዲቀርብ አስመላሽ ኮሚቴውን አዘዘ፤ የአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ፹ ቀን የቅ/ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት ይዘከራል
- በአዲስ አበባ እና በሐረር ከተሞች ከ310 ያላነሱ የተወረሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቪላ ቤቶችና ሕንፃዎች አልተመለሱም፤ ለተመለሱት ቤቶችና ሕንፃዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማውጣት የተያዘው ዕቅድ በተሟላ ኹኔታ ተሳክቷል፡፡
- ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተመለሱት 16 ሕንፃዎች፣ 12 መጋዘኖች፣ 110 ቪላ ቤቶች ዓመታዊ የኪራይ ገቢ ከ23 ሚልዮን ብር በላይ ደርሷል፤ የኪራይ ተመን ማስተካከያ ለማድረግ ጥናት እየተካሔደ ነው፡፡
- የኢሕአዴግ ዋና ጽ/ቤትን ጨምሮ ለኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ፣ ለፊንፊኔ የምግብ አዳራሽ እና ለተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃዎች በካሳነት የታሰበው 70 ሚልዮን ብርና በምትክነት ይቀርባል የተባለው የግንባታ ቦታ እያነጋገረ ነው፡፡
- በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. የተቋቋመውና በአኹኑ ወቅት በመጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ሰብሳቢነት የሚመራው የቤቶችና ሕንፃዎች አስመላሽ ኮሚቴ ጨምሮ ስለ ካሳ ክፍያውና የአራት ኪሎ ‹መንትዮች ሕንፃ›ን ለማስመለስ ከመንግሥት አካል ጋራ ውይይት እያደረግኹ ነው በሚል ያቀረበው ሪፖርት ‹‹ያልተሟላ ነው›› ተብሏል፡፡
- የአስመላሽ ኮሚቴው፣ ሪፖርቱ፣ ቤቶቹና ሕንፃዎች ከከተማው የልማት ፕሮግራም አኳያ በወቅቱ የሚገኙበትን ኹኔታ አካቶና በመረጃ ተደግፎ እንዲቀርብ በቅዱስ ሲኖዶሱ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡
- የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የምሕንድስና ዘርፍ ዋና ሓላፊ የነበሩትና ከግንባታዎች ዲዛየንና ቁጥጥር ጋራ ተያይዞ ሲነሡ ለቆዩ የከፉ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ተጠያቂ የኾኑት አቶ ሰሎሞን ካሳዬ ከዋና ሓላፊነታቸው ተባረዋል!! ዘርፉ በባለሞያዎች የቴክኒክ ኮሚቴ በጊዜያዊነት እየተመራ ነው፡፡፡
***
- በመንግሥት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሠረት በማድረግ ተጠንተው የተጠናቀቁና ዋጋ የወጣባቸውን ሕንፃዎችና ቪላ ቤቶች ከከተማው ፕላንና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር የተጠናቀቁ የግንባታ ፕላኖችን በመውሰድ ቤተ ክርስቲያንን ከከፍተኛ ወጪ ለማዳን ጥረት ተደርጓል፡፡
- አህጉረ ስብከት እንዲሁም ታላላቅ አድባራትና ገዳማት በአክሲዮን እንዲሳተፉ በማድረግ ባሉን ክፍት ቦታዎችና ሰፋፊ መሬቶች ላይ ለእንግዶች ማረፊያ፣ ለመኖሪያ፣ ለሆስፒታል፣ ለቢሮ ወዘተ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ሕንፃዎችን በመገንባት ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያግዝ አቅም ለመፍጠር በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የረጅምና የአጭር ጊዜ የልማት ዕቅዶች ተይዘዋል፡፡
- የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በቴክኒክና በፋይናንስ ድጋፍ ረገድ የጂ.ቲ.ዝድ፣ የቻይናና የቱርክ ኩባንያዎችን ሰብስበው ያነጋገሩ ሲኾን በተለይም የቻይናና የቱርክ ኩባንያዎች የሚገነቧቸው ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ሕንፃዎች መገንባት የሚቻል መኾኑ ከኩባንያዎቹ ከተገኙት ዶኩመንቶች መረጃ አንጻር ታምኖበታል፡፡
- በመሀል ፒያሳ ዘውዲቱ ሕንፃ ጀርባ በሚገኘው 749 ካሬ ሜትር ክፍት ቦታ ላይ በማስተር ፕላኑ መሠረት ለቦታው ታሪካዊነት በሚስማማ አኳኋን ኹለት ባለአራት ደርብ ሕንፃዎችን በ48 ሚልዮን ብር ወጪ ለመገንባትና በማልሚያ ፕላን ስምምነት የግንባታ ፈቃድ ከተገኘባቸው አምስት ቦታዎች መካከል በአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አንድ ኹለገብ ሕንፃ ከቻይናው ሲ.ጂ.ሲ.ኦ.ሲ ጋራ በመተባበር በ3 ቢልዮን ብር ለማሠራት የቀረበው የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዕቅድ በቅ/ሲኖዶሱ ጸድቋል፡፡
- የኹለቱን የግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛየኖች ሥራ ከክፍያ ነጻ በበጎ ፈቃድ አግልግሎት የሠሩትና በምልዓተ ጉባኤው ፊት ቀርበው ከቦርዱ ሊቀ ጳጳስ ጋራ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ባለሞያዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ተመስግነዋል፤ ፓትርያርኩ በምልዓተ ጉባኤው ማብቂያ ዕብነ መሠረት በማስቀመጥ የግንባታ ሥራውን ያስጀምራሉ ተብሏል፡፡
***
- የቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ የ፹ ቀን መታሰቢያ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከናወናል፡፡
- በፀረ ሙስና አቋማቸው የሚታወቁት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ፣ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎች እንደተናፈሰው ፈጽሞ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ተከታይ አይደሉም፡፡
- በኦሮሚያ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕግ ባለሞያና በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ግምቢ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ፍሬ የኾኑት ባለቤታቸው ወ/ሮ ፀሐይ አመንቲ እንዲሁም መላው ቤተሰዎቻቸው በቅዱሳን ወዳጅነታቸውና በጽኑ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባራቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
- የዐደባባይ ሰዎችንና የፖሊቲካ ባለሥልጣናትን ፕሮቴስታንታዊ በማድረግና ፕሮቴስታንታዊ ናቸው በሚል ፕሮቴስታንታዊነት ማስፋፋት፣ በኵላዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጠራ ታሪክ የሚገፋ ጎሳዊ ጥላቻን ለማጠናከር አድርባይ ፖሊቲከኞችና ጎጠኞች በስፋት የተያያዙት የብተና ፕሮጀክት ነው፡፡
- ከነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ የፖሊቲካ አቋም ጋራ ፍቅር ባይኖረንም በዚህ መንፈስ በሐዋርያዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሰነዘረውን የአድርባዮችና ጎጠኞች ሤራና ስልት ማጋለጥ ግን ኦርቶዶክሳዊነታችን ግድ ይለናል፡፡
- በሐራዊ ምንጮች እንደተረጋገጠው፣ ነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ በሓላፊነት በሠሩባቸው አካባቢዎች ኹሉ በአጥቢያቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት በአባልነት ተመዝግበው አስተዋፅኦ በማድረግ የምእመንነት ግዴታቸውን የተወጡ ኦርቶዶክሳዊ ነበሩ፡፡
- በአዲስ አበባ የመካኒሳ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባል የነበሩት ነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ፣ በስፋት ከሚነገረው መመረዝ ጋራ በተያያዘ በታመሙበት ወቅት በጥያቄአቸው መሠረት የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበው መነኰሳት በመኖርያ በቤታቸው እየተገኙ ጸሎት ያደርጉላቸው፣ ጠበልም ያጠምቋቸው ነበር፡፡
- ሥርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የኾነው መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ለማሳመር ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ስለኾኑ ነው!!




