በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ማሻሻያ ላይ ሲካሔድ የቆየው የቅ/ሲኖዶሱ ውይይት ተጠናቀቀ፤ ስብሰባው በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ቀጥሏል
- በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሰብሳቢነት የተመራው ኮሚቴ በ80 አንቀጾችና በ99 ገጾች አዘጋጅቶ ያቀረበው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ የተጠናቀቀው፣ ምልዓተ ጉባኤው በሰጠው አስተያየትና ባደረገው ማስተካከያ መሠረት ከአርቃቂ ኮሚቴው ጋራ ሠርቶና አሟልቶ ለቀጣዩ ስብሰባ የሚያደርስ የሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ምሁራን ኮሚቴ በማቋቋም ነው፡፡
***
- የፓትርያርክ እንደራሴ ምደባ እንዳስፈላጊነቱ ሲሠራበት የቆየ መኾኑን በመጥቀስና ለወደፊቱም ሲያስፈልግ ሊመደብ እንደሚችል በመስማማት ከማሻሻያው እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
- የቅ/ሲኖዶሱን ዓላማ ለማስፈጸም እንደሚቋቋሙ በማሻሻያ ረቂቁ ከተገለጹት ተጨማሪ አካላት መካከል ‹‹ቋሚ ኮሚቴዎች›› እንደቀድሞው ጉዳይ ተኮር ኾነው ከሚደራጁ በቀር በቋሚነት መደራጀት የለባቸውም በሚል ማስተካከያ ተደርጓል፡፡
- ‹‹የሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን መማክርት ጉባኤ›› ለውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ በር ይከፍታል በሚል የምልዓተ ጉባኤውን ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሐሳቡ ከማሻሻያ ረቂቁ ወጥቷል፡፡፡፡
***
- ስለምንኵስና ደረጃዎች፣ መሥፈርትና አፈጻጸም፣ ለመነኰሳት ስለተከለከሉ ተግባራት(ያለፈቃድ ከገዳም ወጥቶ በከተማ መዋልና ማደርን፣ በመጠጥ ቤትና አልባሌ ቦታ መገኘትን፣ የግል ንብረት ማከማቸትንና ማቋቋምን፣ ለሴቶችና ባለትዳሮች በንስሐ አባትነት ማገልገልንና አለባበስን ጨምሮ) ሕግን ስለሚተላለፉ መነኰሳት ዝርዝር ደንብና መመሪያ እንደሚወጣ ተመልክቷል፡፡
- የማስመስከሪያ የአብነት ት/ቤቶች መምህራን እንደየሞያቸው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ወይም በየአህጉረ ስብከቱ አማካይነት ቋሚ ደመወዝ ይመደብላቸዋል፡፡ ከምስክር አብያተ ጉባኤያት የሚመረቁ ሊቃውንት በት/ቤቶቹ የምስክር መምህርና በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በጋራ የተፈረመ የጽሑፍ ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል፡፡ የአብነት ትምህርቶች ማረጋገጫ ከዶክትሬት እስከ ዲፕሎማ ድረስ ተመጣጣኝ ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡
- በቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ደረጃ ያሉ ካህናት የማንኛውም የፖሊቲካ እንቅስቃሴ አባል ወይም አራማጅ መኾን እንደማይችሉ የካህናትን መብትና ግዴታ በሚደነግገውና ለካህናት የተከለከሉ ተግባራትን በሚዘርዝረው የማሻሻያ ረቂቁ አንቀጽ በአከራካሪ ኹኔታ ውሳኔ አግኝቷል፡፡
***
- የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አስፈጻሚነትና የአስተዳደር ተግባራት የማከናወን ሥልጣን የተሰጠው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መምሪያዎችና አገልግሎቶች፡- (ሀ) መንፈሳዊ ዘርፍ፣ (ለ) የፋይናንስ የሰው ሀብትና ልማት ዘርፍ በሚል ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ በኾኑ ኹለት ምክትል ሥራ አስኪያጆች ለመከታተል የቀረበው ሐሳብ ‹‹አስፈላጊ አይደለም፤ ሥራ የለውም፤ ኹሉም ሥራ መንፈሳዊና መንፈሳዊውን ተግባር የሚደግፍ ነው›› በሚል ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቀረበውን ማብራሪያ መነሻ አድርጎ ጽ/ቤቱ በጠቅ/ሥ/አስኪያጁና በአንድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ ተወስኗል፡፡
- የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አንድ እንዲኾንና የዘርፍ ክፍፍሉ እንዲቀር በመወሰኑ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ውጭ በመዋቅር ሳይታወቅ ሲሠራበት የቆየው የንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ‹‹የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ›› ሥልጣን ተሽሯል!!!
- የጉባኤው ርእሰ መንበር ፓትርያርኩ፣ ከዘርፉ መዋቅራዊ አስፈላጊነት ይልቅ ‹የመቀመጫቸውን› ላጡት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ‹‹ታድያ ሰውዬውን የት እናድርገው?›› በሚል ያነሡት ጥያቄ የብፁዓን አባቶችን ፈገግታ ሳያጭር አልቀረም፡፡
- በርግጥም ለንቡረ እዱ ርእሰ መንበሩ ያሰቡላቸው ቦታ ባይገኝላቸውም የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁን በምልዓተ ጉባኤው አስተያየትና ማረሚያ መሠረት አሟልቶ ለቀጣዩ ስብሰባ እንዲያቀርብ በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ በፓትርያርኩ ውትወታ እንዲካተቱ መደረጉ እያነጋገረ ይገኛል፡፡
***
- በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲመክር የሰነበተው ምልዓተ ጉባኤው፣ በዛሬው፣ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ውሎው ስለቤተ ክርስቲያናችን ስትራተጅያዊ ዕቅድ የመሪ ዕቅድ ጥናት ዓቢይ ኮሚቴው በሚያቀርበው የትግበራ ስልቶችና ስለ ገዳማት አያያዝ በተቀረፁ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ላይ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡
- የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ እንዲቻል የቀረበው ጥናት፣ በጥቅምቱ መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ በሥራ ለመተርጎም በሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ ለግንቦቱ ስብሰባ እንዲቀርብ ምልዓተ ጉባኤው ትእዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
- ለምልዓተ ጉባኤው መነጋገርያ እንዲኾኑ ከጸደቁት ኻያ ያህል አጀንዳዎች መካከል፡- በተ.ቁ(4) የተያዘው ‹‹የአባቶች ምርጫ መመዘኛ ሕግ›› እና በተ.ቁ(5) የሰፈረው ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ›› እንደ ቅደም ተከተላቸው ቀጣይ ተራቸውን የሚጠብቁ ይኾናሉ፡፡




