ቅዱስ ሲኖዶሱ በቋሚ ኮሚቴዎች እና በመማክርት ጉባኤ ሊደራጅ ነው

  • የቅዱስ ሲኖዶሱን የአመራር፣ የአስተዳደር፣ የቁጥጥርና የመወሰን ብቃት ያግዛሉ
  • የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላት ለማቀናጀትና አሠራራቸው ጥንካሬ እንዲኖረው ያስችላሉ
  • ምልዓተ ጉባኤው በአጭር ጊዜ የሚይዛቸው በርካታ አጀንዳዎች የተጠና ውሳኔ ያገኛሉ
  • የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶሱ ይኾናል
Holy Synod00

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ

(አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ ፰ ቁጥር ፪፻፲፮፤ ግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻውና ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት ለኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ፣ የመምራትና የማስተዳደር ዓላማዎቹን የሚያስፈጽምባቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለማደራጀትና በተለያዩ የሞያ ዘርፎች በማማከር የሚያገለግል የመማክርት ጉባኤ ለማቋቋም በሚያስችል የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ላይ በምልዓተ ጉባኤው ውይይት እየተካሔደ መኾኑን የአዲስ ጉዳይ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ከሚነጋገርባቸው ኻያ ሦስት አጀንዳዎች መካከል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ማሻሻያ ረቂቁ በ99 ገጾች ካካተታቸው 80 አንቀጾች መካከል፣ ቅ/ሲኖዶሱ ዓላማዎቹን ስለሚያስፈጽምባቸው አካላት በሚዘረዝረው አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2(4) እና (5) ተጠሪነታቸው ለቅ/ሲኖዶስ የኾኑ መምሪያዎች(የሥራ ክፍሎች)፣ ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን የሚገኙበት የመማክርት ጉባኤ እንደሚኖሩት ተመልክቷል፡፡

በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ አንቀጽ 12(3) መሠረት፣ ከላይ ወደ ታች እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተዘረጋው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ኹሉ ላይ የበላይ አካል ኾኖ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣት የዳኝነት ሥልጣን ላለው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠሪ ኾነው ይደራጃሉ የተባሉት ቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ሰባት ሲኾን ዝርዝርቸውም፡-

  1. የእምነትና የትምህርት ጉዳዮች፣
  2. የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ጥናትና ዝግጅት፣
  3. የአህጉረ ስብከትና የገዳማት ጉዳዮች፣
  4. የውጭ ግንኙነት፣
  5. የልማትና ፕሮጀክት ጉዳዮች፣
  6. ኦዲትና ኢንስፔክሽን፣
  7. የሥነ ምግባርና የሥነ ሥርዓት ኮሚቴዎች

እንደኾኑ ተገልጧል፡፡

ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን እየተመለከቱ፣ እያጠኑና እየመረመሩ፣ የየመምሪያዎቹንና የአህጉረ ስብከትን የሥራ አፈጻጸም እየገመገሙ የውሳኔ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ተጨማሪ ኮሚቴዎች በቅ/ሲኖዶሱ ሊቋቋሙ እንደሚችሉ ያመለከተው ረቂቁ፣ የኮሚቴዎቹ አባላት ከቅ/ሲኖዶስ አባላት መካከል የሚመረጡና አስፈላጊ ኾኖ በተገኘ ጊዜ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናንም ባለሞያዎች የኾኑ ምሁራን ተመርጠው በአማካሪነት አብረው እንደሚሠሩ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለማማከርና በየሞያ ዘርፉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾነ አንድ የመማክርት ጉባኤ እንደሚቋቋም በማሻሻያ ረቂቁ ተጠቅሷል፡፡ የመማክርት ጉባኤው ተሳታፊዎች ከየሀገረ ስብከቱ የተመረጡ ‹‹ኦርቶዶክሳውያን ምሁራን›› እንደሚኾኑ በረቂቁ አንቀጽ 12(4) ሰፍሯል፤ ተሳታፊ ምሁራኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሕዝበ ክርስቲያኑ ዕውቅና ያላቸው እንደሚኾኑ አመልክቷል፤ የመማክርት ጉባኤው ስብሰባዎች በዓመት ኹለት ጊዜ የሚደረጉና በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት እንደሚካሔዱም ገልጧል፡፡

Holy Synod02

የቅ/ሲኖዶስ አባላት ከቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋራ በስብሰባ ላይ

ቋሚ ኮሚቴዎቹና የመማክርት ጉባኤው በራሳቸው የሚዘጋጅ የውስጥ ደንብ ይኖራቸዋል፤ የሥራ አፈጻጸማቸውንም በየሩብ ዓመቱ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የሊቃውንት ጉባኤ፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት፣ የሥነ ሥርዓትና የሥነ ምግባር ዘርፍ የመሳሰሉት አካላት÷ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዓቢይ ጉባኤ ቅ/ሲኖዶስ ተጠሪ የሚኾኑበትን አሠራር ለመዘርጋት መታሰቡን የሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ጠቁሟል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ በአዲስ መልክ የተካተቱት አካላት፣ ቋሚ ኮሚቴዎችና የመማክርት ጉባኤ የማቋቋም ሐሳብ የምልዓተ ጉባኤውን ስምምነት አግኝቶ ከጸደቀ፥ ፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ በአባልነት የሚገኙበትን የቅ/ሲኖዶሱን የአመራር፣ የአስተዳደር፣ የቁጥጥርና የመወሰን ብቃት በማገዝ፣ አሠራሩን በማቀናጀትና በማጠናከር የጥንታዊቷን ቤተ ክርስቲያን ሥር የሰደደና የቆየ አስተዳደራዊ ችግር ሩቅ በማይባል ጊዜ ለመፍታትና ለውጦችን ለማየት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

ፓትርያርኩ በምልዓተ ጉባኤው ስብሰባ መክፈቻ ላይ በሰጡት መግለጫ የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔዎች በጥናት ላይ ተመሥርተው ደረጃ በደረጃ በተግባር ለመተርጎምና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልናና ክብር፣ አንድነትና ሥርዓት እንደነበረው አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች በቅ/ሲኖዶሱ እንደተወሰኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡