አቡጊዳ – መድረክ በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ገና እውቅና አላገኘም

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በሀገሪቱ በሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ በመቃወም ለግንቦት 3 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንደለመደው ቀኑ እንዲራዘም በመጠየቅ እውቅና ሳይሰጥ ቀርቷል።

መድረኩ ለግንቦት 10 ቀን ሰልፉን ለማድረግ እውቅና ለማግኘት እየሞከረ ሲሆን፣ እስከአሁን ምን ደረጃ ላይ እንደተደረሰ ከመድረክ የተሰጠ መግለጫ የለም።

መድረክ የአንድነት ፓርቲን ጨምሮ ፣ በዶር መራራ የሚመራው ኦፌኮ፣ አረና ትግራይ፣ በዶር በየነ የሚመራዉ የደቡብ ሕዝቦች ድርጅትን አካቶ የነበረ ስብስብ እንደነበረ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት የአንድነት ፓርቲ በመድረክ ዉስጥ የሚሰበሰብ እና አብሮ የሚሰራ እንዳለሆነ በስፋት የተዘገበ ጉዳይ ነው።

መድረኩ እውቅና አግኝቶ ግንቦት 10 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ከተደረገ፣ በአዲስ አበባ ዉስጥ ባለፉት አራት ሳምንታት ሶስት ሰላማዊ ሰልፎች ተደረጉ እንደማለት ነው። ሚያዚያ 19 የሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ በመቶ የሚቆጠሩ፣ ሚያዚያ 26 ቀን አንድነት በጠራዉ ሰልፍ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ በመድረኩም ሰልፍ በርካቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። «በሰልፉም ላይ እስከ 50 ሺህ ሰው እንደሚሳተፍ እንጠብቃለን» አቶ ጥላሁን ስለሺ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ገልፀዋል።

መድረኩ በቅርቡ በአዋሳ ከተማ ታላቅ ሕዝባዊ ሰብሰባ በማድረግ ከሕዝብ ጋር መወያየቱም ይታውቃል።