የርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎተ ተካሔደ

Holy Synod opening prayerዛሬ፣ ረቡዕ ግንቦት ፮ ቀን የሚጀመረው የ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት በትላትናው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተካሒዷል፡፡

ከቀኑ ፲ ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው በዚኹ የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት የተሰበሰቡ ከሠላሳ በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል፤ በሥርዓተ ጸሎቱ መክፈቻና መዝጊያ የቤተ ክርስቲያኑ የደወል ድምፅ ለደቂቃዎች ተሰምቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ‹‹ሁሩ ወመሐሩ›› በሚል ርእስ በጽሑፍ የተዘጋጀ ትምህርት የሰጡት የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት በላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡

‹‹ኹላችንንም ከየአህጉረ ስብከታችን ሰብስቦ ስሙን በመቀደስ፣ ቃሉን በመስማት ዓመታዊ ስብሰባችንን በጸሎት ለመጀመር ላበቃን አምላካችን እግዚአብሔር ‹ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐነ እስከ ዛቲ ሰዓት› በማለት እናመሰግነዋለን›› በማለት ትምህርታዊ ጽሑፋቸውን የጀመሩት ብፁዕነታቸው÷ በቅዱስ ሲኖዶሱ እየተጠናና እየተመከረበት የሚወጣው ሕግና ደንብ ለእምነታችን ህልውና፣ ለኅብረተሰባችን ማኅበራዊ አገልግሎት ዋስትና የሚሰጥ ስለኾነ ለሕጉ ተገዥዎች መኾን እንደሚጠበቅብን አሳስበዋል፡፡