እሰይ! ድል ለወጣቱ ትውልድ!!! ከሮበሌ አባቢያ፣ 5/5/2014
የአንድነት ፓርቲ ያቀረበውን እጅግ በጣም ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ፣ አይኖቼ እምባ እያቀረሩ፣ ልቤን ደስታ ፈንቅሏት ነው እኔም እንደ ሰልፈኞቹ መፈክር እያሰማሁ ከናት ሀገሬ ውጪ ከምኖርበት ከተማ በቴሌቪዥን ከመኖሪያ ቤቴ ተቀምጬ ነበር የተመለከትኩት።
እሰይ! ድል ለወጣቱ ትውልድ!!! በማለት ይህቺን መጣጥፍ ለመክተብ ተነሳሳሁ።
ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደጻፍኩት ግትር ኢትዮጵያዊ ነኝ። ያ እንዳለ ሆኖ፣ አንድነት ባዘጋጀው ሰልፍ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች በኦሮሞ ተማሪዎችና በደጋፊዎቻቸው ላይ የደረሰውን ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ አበክረው በማውገዘቸው በወገኖቼ ኢትዮጵያን ኮርቻለሁ፤ አድሮብኝ ከነበረው ጥልቅ ሀዘንም ተፅናንቻለሁ፤ ለሰብአዊ መብት ዓላማ ስኬት ለመታገል ቃልኪዳኔን አድሻለሁ።
ባለቤቴ በተወለደችበት፣ አድጋ ተምራ በተጋባንበት፣ አሁንም ዘመዶቿ በሚኖሩበት፣ እኔም አዳሪ ት/ቤት ሁለት ዓመት በተማርኩበት በአምቦ ብቻ ሳይሆን፣ የኦሮሞ ተማሪዎች በያለበት የመብት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማንሳታቸው የከፈሉት መስዋዕትነት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት እርሷም እኔም ዝግጁ ነን።
ተነሳ ተራመድ!
ተነሳ ተራመድ ለ”1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት” ወጣቶች ለሕዝብ ያበረከቱት፣ መዝሙር ነው። የመዝሙሩ ቃላትና እና ጣዕመ ዜማ ሕዝቡን ዳር ከዳር የማረከና ያስተባበረ ሆኖ እንደነበር አሌ የማይባል ሐቅ እና የቅርብ ትዝታ ነው።
የመዝሙሩ ወጣት አዘጋጆች የሙዚቃ መሣሪያዎች ከየቦታው በመለቃቀም፣ የተሰበረውን በመጠገን፣ ትርፍ ጊዜያቸውን ሰውተው በማዘጋጀት ነበር መዝሙሩን ለኢትዮጵያን ያበረከቱት። ለዚህም ትልቅ አስተዋጽኦ ወጣቶቹ የመዝሙሩ ደራሲያን እነ ጌቱ ማዴቦና ዘማርያን ጊዜ የማሽረው ምስጋና በታሪክ መዝገብ እንሚጻፍላቸው አምናለሁ። ምክንያቱም የመዝሙሩ ቃላት በሸጋ ሙዚቃ ታጅበው፦ የዘር የሃይማኖት ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ታጥቆ ለሥራ በመነሳት የበለጸገች፤ ለጠላት የማትበገር ዲሞክራሲያዊ ሀገር መገንባት፣ ለዘመናት በከንቱ የፈሰሱትን ወንዞች በመገደብ ለልማት ማዋል፣ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል መገንባት፣ እና የመሳሰሉትን ሀገራዊ እሴቶችን የሚያንጸባረቁ በመሆናቸው። ከመዝሙሩ ጽሁፍ ውስጥ አንድ ብቻ እርምት ተደርጓል። ይህም፣ “ይላል የአየር ኃይል” የሚለው ሐረግ፣ “ይላሉ ልጆችሽ” በሚል እንዲታካ፣ ኮሎኔል ምትኩ ሙለታ ያቀረቡት ሀሳብ ነበር። እርምቱም በጋለ ጭብጨባ ተቀባይነትን በማግኘቱ፣ የአብሮነትን ፖለቲካዊ መልእክትና ሁላችንም የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸንን ያንፀባረቀ ድንቅ ሀሳብ በመሆኑ ከፍተኛ መኮንኑ ጥልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።
“የተነሳ ተራመድ” ደራሲያንና ዘማሪዎች በሙሉ ባለሌ ማዕረጎች (non-commissioned
officers) ነበሩ። የስማቸውን ዝርዝር የያዝ ሊስት ከፈረምኩበት ደብዳቤ ጋር አያይዤ
ለደርጉ ጽ/ቤት ሰጥቻለሁ። እነዚህ ወጣቶች የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን፣ መሠረታዊ
የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ሲያነሱ እኛ ከፍተኛ መኮንኖች የት ነበርን እያልኩ በሐፍረት
እቆጫለሁ። ይበልጥ የማፍረውና የማዝነው መዝሙሩ የዓለም ወዛደሮችን ፍልስፍና
አያንጸባርቅም ተብሎ በአየር ላይ እንዳይውል መታገዱ ነው። የእገዳው ትዕዛዝ የተላለፈው
በደርጉ ሊቀመንበር በኩል ሰለመሆኑ በበኩሌ አልጠራጠርም። ደርግ መውደቂያው
ሲቃረብ፣ አየር ኃይሉ ሴሬሞኒ በሚያደርግበት ጊዜያት ተነሳ ተራመድ በግቢው ውስጥ
ለማስዘመር እንዲችል ተፈቀደለት። ግራ የገባው መንግሥት!!!
ማስተር ቴክኒሽን ግርማ ዘለቀ
ወጣቱ ጀግና ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ ዘለቀ፣ የአየር ኃይል መሣሪያ ግምጃ ቤት ሀላፊ
እንደመሆኑ የመጋዘኑን በር ከፍቶ በውስጡ የሚገኙትን የነብስ ወከፍ መሣሪየዎች ለባለሌላ
ማዕረጎች (ቴክኒሽያኖች) ካስታጠቀ በሗላ፣ በርሱ መሪነት በሕቡእ ይንቀሳቀስ የነበረው
ቡድን ይፋ ወጣና ደብረ ዘይት የምንገኝ የንጉሠ ነገሥቱ አየር ኃይል ከፍተኛ የአመራር
ባለሥልጣናት ተይዘን በተለያዩ ስፍራዎች በየካቲት ወር ሁለተኛ ሳምንት ሲጀመር በ1966
ዓ.ም ታሰርን፡፡ የጦር ሠፈሩም ባሳሪዎቻችን ቁጥጥር ስር ዋለ። ከሻለቃ ማዕረግ በታች
ያሉ መኮንንኖች ያልታገቱ ቢሆንም ምንም ዓይነት መሣሪያ ሳይታጠቁ በግቢው (ካምፕ)
ውስጥና ውጪ ይንቀሳቀሱ ነበር።
ከላይ ከተጠቀሰው እገታ በሗላ፣ አጋቾች ዐቢይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ በርካታ
ጥያቄዎችን ለመንግሥት አቀረቡ። በዚህ ሂደት ውስጥ ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ አልፎ
አልፎ ከግርማዊነታቸው ጋር በስልክ እየተገናኘ ለሚያቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ
በመስጠት ይደራደር ነበር። ለምሳሌ እናንተ ባድማ ላይ እያላችሁ ሱማሊያ የኢትዮጵያን
ድምበር አልፋ ብትወረን ምን ይደረጋል ብለው ጃንሆይ ሲጠይቁት፣ አድማችንን በቅጽበት
አቁመን ወራሪዉን በመግረፍ ይህንን የጋለ ቁጣችንን በጠላት ላይ እናበርዳለን ሲል
ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ ዘለቀ እንደመለሰላቸው ከእገታ በሰላም ከተለቀቅን በሗላ
ለማወቅ ችያለሁ። እውነትም ማ/ቴክኒሽያን ግርማ እንዳለው፤ አብራሪዎች እና
ቴክኒሲያኖች ስለአልታገቱ ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ላይ ስለነበሩ ተዋጊ አውሮፕላኖች
ከደብረ ዘይት፣ ከድሬዳዋና ከአስመራ አየር ጣቢያዎች በመነሳት፣ ከሶሰተኛው ክፍለ ጦር
ጋር በመተባበር ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጊያ ለመግጠምና ጠላትን ለማዳሸቅ ይቻል ነበር።
በቁጥጥር ስር የዋልነው ከፍተኛ መኮንኖች በታሰርን በሁለተኛው ቀን ከያለንበት ተወስደን
በባለ ሌላ ማእረጎች ክበብ ምግብ ቤት ምሳ ከበላን በሗላ በአቅራቢያው ከሚገኝ አንድ ሰፊ
አዳራሽ ውስጥ እንድንሰበሰብ ተደረገ። ሁለት ባለሌላ ማዕረግ ቴክኒሽያኖች፣ አንዱ ሽጉጥ
ሌላው ኦቶማቲክ (ኡዚ) የያዘ ከፊታችን ቆሙ። ዙሪያውን ስመለከት ጥቁር ቱታ የለበሱ
ፊታቸው ላይ ቁጣ የሚታይባቸው ኦቶማቲክ መሳሪያ የታጠቁ ቴክኒሲያኖች ቆመዋል።
ሽጉጥ የያዘው ቴክኒሽያን፣ እምባ እየተናነቀው አስተምራችሁ አሳደጋችሁናል፣ በማህበራዊ
ኑሮም ተሳስረናል፣ አበልጆችም የሆን አለን በማለት፣ እርምጃ ለመውሰድ የተገደዱበትን
በመግለፅ ላይ እያለ ንግግሩን ሳይጨርስ፣ ከአጠገቡ የቆመው ጓደኛው ከመቅጽበት ሽጉጡን
ከጁ ነጠቀውና ድራማው አበቃ። የገረመኝ ነገር ይህ ሁሉ ሲሆን ታጋች መኮንኖች
ሁኔታውን ከቁብ አልቆጠሩትም፡፡
ጃንሆይ ምህረት የማድረጋቸውን ዜና ለማሰማት፣ ምክትል የእልፍኝ አስከልካያቸው ሜጀር ጄኔራል አሰፋ ለማ፣ የመጡ መሆኑን አጋቾቻችን አበሰሩን። ከዚያም ከአየር ኃይል ካምፕ ውጪ ጋራ በሩ ተብሎ በሚጠራው ተራራ አቅጣጫ በሚገኝ ጥቅጥቅ ባለ ቁጥቋጦ በተከበበ ገላጣ ሜዳ ላይ ታጋቾች ከፍተኛ የአየር ኃይል መኮንንኖች ብቻ እንድንኮለኮል ተደረገ። ቀደም ሲል ከኛ ጋር ታግተው የነበሩት የአየር ወለድ ጥቂት መኮንንኖች አልነበሩም። ለምን እንደሆነ እስከ አሁን ይገርመኛል።
ምን ሊመጣ ነው ብለን ስንጠባበቅ፣ የአየር ወለድ አዛዥ ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ፣ በጥይት የተሞላውን ዝናር በወገቡ ዙሪያና ከጀርባው በትከሻው ላይ እስከ ጉልበቱ ድረስ አንዠርጎ መትረየሱን አንግቦ ከጥቂት አጃቢዎቹ ጋር ከቁጥቋጦ ውስጥ ወጥቶ ኩስትር ብሎ ከታጋቾች ፊት ለፊት ቆመ። ነገሩ ያልጠበቅነው እንደመሆኑ ይህ ወራሪ ከጎረቤታቸን በማን ታዞ ነው የመጣብን ሳንል አልቀረንም።
የኮሎኔል የዓለም ዘውድ ወገናዊነት ከማን ጋር እንደሆነ ገና ንግግሩን ሲጀምር ግልፅ ሆነ። ግርማዊነታቸው ይቅርታ ያደረጉልን መሆኑን አበሰረን። ለሠራዊቱም በወር ሰባት (7) ብር ደሞዝ በዓፄው መልካም ፍቃድና ትእዛዝ ለመከላከያ ሠራዊት የተጨመረ መሆኑን አስታወቀን። ዝምታን ያዘለ ተቃውሞ ለጥቂት ጊዜ ሠፈነ። ከዚያ እጄን አወጣሁና ለመሆኑ ደሀው ገበሬ ከየት አምጥቶ ነው የተባለው የደሞዝ ጭማሪ የሚከፈለን ብዬ ላነሳሁት ጥያቄ መልሱ በደፈናው ገንዘቡ አለ ከየትም ይገኛል ሆነ። ያሳፍራል! ቀጥሎም ከታገትነው ውስጥ አንዱ ኮሎኔል (ጌታሁን እጀጉ) እኛ ታሳሪ፣ እናንተ አሳሪና መሐሪ የተሆነበት ምክንያት እንቆቅልሽ እንደሆነበት አምርሮ ተናገረ። ለዚህ ጠንካራ ተቃውሞ ኮሎኔል ዓለም ዘውድ ምላሽ አልሰጠም፤ ታጋቾች ኮሎኔሉን በትዝብትና በንቀት ዓይን ይመለከቱት ነበር። ስብሰባውም በዚህ አበቃና ወደ ሌላ ቦታ ተወሰድን። ምንስ አጥፍተን ነው በአየር ወለድ አዛዠ ትእዛዝ የታስረነው የሚለው ጥያቄ እስከዘሬ ድረስ በአዕመሮዬ ውስጥ ይመላለሳል።
ከኮሎኔል የዓለም ዘውድ አሳፋሪ ድራማ ተላቀን ወደ ካምፓችን እንድንመለስ ተደረገና በአየር ኃይል ሠልጣኞች ክበብ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰብን። መልከ መልካሙ አጅሬ ግርማ ዘለቀ ብቅ ብሎ እፊታችን ቆመ። ማራኪው ቁማናው እንዳለ ሆኖ የሚያማምሩት ትላልቅ ዓይኖቹ እንቅልፍ ከማጣት ምክንያት ይመስለኛል ቀልተዋል። ግርማ፣ ከፊትለፊቱ ለተቀመጥነው ከሻለቃ እስከ ብ/ጄኔራል ማዕረግ ላይ ለምንገኝ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ስለታሰርንበት ምክንያት እጅግ የሚመስጥ አጭር ንግግር አደረገ። ከአንድ መሪ የሚጠበቅ በሳልና ድንቅ ንግግሩንም፣ “እኛ በያዘችሁት ሥልጣን ስሩበት ብለን ተነሳን እንጂ ልንነጥቃችሁ አይደለም” በማለት ዘግቶ በሰላም አሰናበተን። ጥሪውና መልእክቱ ወቅታዊውን ሁኔታ ያካተቱ ጥርት ያሉ በመሆናቸው፣ ታጋቾች ትንፈሽ ሳንል አንዳች ጥያቄም ሆነ አስተያየት ሳንሰጥ ወደየቤታችን ሄድን። ተዳክሞ የነበረው የመንግሥት አስተዳደር ባስከተለው በደል ተነሳስተው፣ የምናዛቸው ባለሌላ ማዕረጎች የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ እስኪያነሱ ድረስ እኛስ ከፍተኛ መኮንኖች ምን እንጠብቅ ነበር? በበኩሌ መንፈሳዊ ቅናት ተሰምቶኝ እንደነበር አልክድም። ለውጡንም ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ ከልብ ለመደገፍ ወሰንኩ።
መሪ ይወለዳል ወይስ በሥልጠና ይታነፃል? በኔ እምነት ወጣቱ ግርማ ዘለቀ ከመሪነት ባሕርዩ ጋር የተወለደ ነው። በየካቲት 1966 አብዮት ያሳየው አመራረና ብስለት ካስገኘው ውጤት ጋር ሲገመገም፣ የመንግሥት ካቤኔ በሰላም ሥልጣኑን ሲለቅ በኢትዮያ ታሪክየመጀመሪያው ነው። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ዐቢይ ሰላማዊ ለውጥ ነው ለማለት እደፍራለሁ። ለዚህም ድንቅ ክንውን ማስተር ቴከኒሽን ግርማና አብዮታዊ ግብረ-አበሮቹ እነ ማስተር ቴክኒሽን አየለ ሐይሌ፣ ሲኒየር ቴክኒሽያን አበበ አረጋ፣ ወዘተ የሚመሰገኑ ናቸው። ለዚህ አንፀባራቂ ድል፣ ታሪክ ክሬዲቱን ለግርማና ለትግል ጓደኞቹ እንደሚሰጥ ጽኑ ተስፋ አለኝ።
የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ውለታ
የካቲት 15 ቀን 1966 ዓ.ም፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ለንጉሠ ነገሥቱ በይፋ ቀርቦ ጥያቄው ከፀደቀ በሗላ፣ የዘውድ ምክር ቤት ሌ/ጄኔራል ዐቢይ አበበ እንዲተኩ ቢያሳሰብም እርሳቸው ፈቃደኛ ሁነው ባለመገኘታቸው፣ የልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ በሰላም ሊተካ ቻለ። የቀድሞው ካቢኔ በሰላም ከሥልጣን መውረድ በምእራባውያን ዲፐሎማቶች ዘንድ እንደ ሰላማዊና ደም ያላፋሰሰ ለውጥ የተወደሰና የተደነቀ መሆኑን አንድ የፈረንሳይ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ደብረ ዘይት ለሥራ ጉዳይ መጥተው እግረ መንገዳቸውን ወደ ቢሮዬ ጎራ ብለው እንደነገሩኝ አስታውሳለሁ። ምን ጊዜም ምትክ የማይገኝላቸው፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ደም እንዳይፋሰስ በማሰብ ላሳዩት በሳል አመራርና ሥልጣን ለመልቀቅ ላደረጉት ውሳኔ የላቀ ምሥጋና ይገባቸዋል እላለሁ።
የክቡር ጠቅላይ ምኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ አስደናቂ አርቆ አስተዋይነትና እና በማ/ቴክኒሽያን ግርማ መሪነት ያጋቾቻችን በሳል ውሳኔ፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” ለተባለው መሪ መፈክርና በሗላም “ተነሳ ተራመድ” ለተሰኘው መዝሙር መከሰት፣ በኔ እምነት ፋና ወጊ ወይም አዋላጅ ሆኗል ብዬ እገምታለሁ።
ከእገታ ከወጣን በሗላ ከግርማ ዘለቀ እና ከሳተናው አብዮተኛ ጓዱ ከአበበ አረጋ ጋር ተቀራርበን ወዳጅነታችን እየበረታ ቀጠለ። የመሬት ላራሹ ጥያቄ እንዲተገበርና ሊበራል ዴሞክራሲ ለማምጣት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ተስማማን።
የግርማ ዘለቀ አሳዛኝ ፍፃሜ
የደርግ አመራር ብቃት ማነስና የሚከተለው የሶሽሊሰት ፍልስፍና ግርማን አላስደሰተውም፡፡ ፍልስፍናው፣ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የፊዉዳል ሥርዓት ፈፅሞ አይሠራም እያለ አጥብቆ ይከራር ስለነበር ከትግል ጓደኞቹም ከሶሽያሊስት ርዕዮት አቀንቃኞች ጋር ልዩነት ተፈጠረ።
ደርግ ግርማን የማረሚያ ቤት ሀላፊ አድርጎ በመሾም ከፖለቲካ አርቆት ነበር። አጅሬ ግን ስድቡን አልተቀበለውም፤ ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሄዶ ከፀረ-ደርግ ሐይሎች (ኢሕአፓና ኢዲዩ) ጋር ለመቀላቀል ሲጓዝ ጎጃም ውስጥ ዳንግላ ሲደርስ ላስቆሙት ወታደሮች እጁን ላለመስጠት በመታኮስ ገሎ በተኩሱ ልውውጥ እሱም ሞተ። በኔ እምነት፣ አትዮጵያም ጀግና ልጇን አጣች!!!
ፋሺስትን-አርዕድ ሸጋው አርበኛ የብቸናው ተወላጅ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አራዳ ጨርቅ ተራ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ሲሰቀል፣ አንቺ ኢትዮጵያ ወንድ አይብቀልብሽ ብሎ መራገሙ ይታወቃል። የጎጃሙን ተወላጅ ጀግናውን ግርማ ዘለቀን ያ እርግማን ደርሶበት ይሆን?። ግርማ ዘለቀ ሲሞት እጅግ በጣም አዘንኩ። የተወለድኩበትን ቦታና ወላጆቼን አልመረጥኩም፤ ግን የወላጆቼ የትውልድ ስፍራ ሰሜን ሸዋ ነው፤ የጠቀስኳቸው ሁለቱም ጎጃም የተወለዱትን ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እጋራለሁ። ምን ጊዜም ኢትዮጵያዊነቴን አስቀድማለሁ!!!
ለወጣቱ ትውልድ
የ1966ቱ አብዮት በኢትዮጵያችን ውስጥ የፈነጠቀው ተስፋ በዘመነ ደርግ ከጨለመ በሗላ በምርጫ 1997 ብልጭ ድርግም ብሎ ሞተ። አብዮቱ ሲፈነዳ የ“ተነሳ ተራመድ” ደራሲዎችና ዘማሪ ወጣቶች የቋጠሩት ራእይ ገና ግቡን አልመታም። የዛሬው ወጣት ብዙ ሥራ የሚጠብቀው ቢሆንም፣ አሁን እንደሚታየው ከተባበረ ድል አድራጊነቱ አይቀሬ ነው።
እስከዚያም ድል ድረስ፣ ይህቺን “ከተነሳ ተራመድ” የቀነጨብኳትን ግጥም ሰንቆ መጓዝ ብልህነት ነው፦
ተብላ እንዳልነበር የዳቦ ቅርጫት
እንዴት ትባላለች ኢትዮጵያን ራባት
ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት
በከንቱ ፈሰዋል ለብዙ ሺህ ዓመታት
የዘር የሃይማኖት ልዩነት አንሻም
ይላሉ ልጆችሽ ኢትዮጵያ ትቅደም
ማጠቃለያ
1. የአንደነት ፓርቲ መሪዎች ያዘጋጁት እጅግ ደማቅ ሰላማዊ ሰለፍ በሰላም በመጠናቀቁ እነኳን ደስ ያላችሁ እያልኩ፣ “የሚሊዎን ሕዝብ ንቅናቄ ራዕያቸው እንዲሳካ እጸልያለሁ፣እሳተፋለሁ
2. ሰሞኑን በኦሮሞ ልጆች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ በደል ለታለቁ የኦሮሞ ሕዝብ ውርደት ነው። ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ መሆን፣ ፎቅ ቤቶችን ከማሳነፅና ሰፋፊ መንገዶችን ከመሥራት መቅደም አለበት። ወያኔ እነዚህን በደሎች ሲፈፅም ለ23 ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን ላይ ኖሯልና በቃህ መባል አለበት።
3. ስለዚህ፣ አቶ ገብረመድህን አርአያ ሚያዚያ 2006 ዓ.ም “ብአዴን ማን ነው?” በሚል ርዕስ ኢትዮሚዲያ ድረገፅ ላይ ባወጡት ጽሑፍ እንዳሉት፣ “በደል በከፋ መንገድ ከመቀጠሉ በፊት በህዝባዊ አመጽ ህወሓትን ማንበርከኪያ ጊዜው አሁን ነው።”
4. በኦሮሞ ልጆች ላይ የተፈፀመው ግድያና ሰቆቃ፣ በኢትዮጰያ ሐዝብ ላይ እንደተፈፀመ መቆጠር አለበት። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነግ በኔ ብሎ በአንድነት በመነሳት፦ ሀ) የወያኔን እኩይ ተግባር ማስቆም፤ ለ) ወንጀል የፈፀሙ ባለሥልጣናትና ጀሌዎቻቸው በፍጥነት ለፍርድ እንዲቀርቡ ማስገደድ አለበት።
የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች አለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ!
