እሁድ የሚካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ኗሪዎች በነቂስ ወጥተው የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ እናቀርባለን!! – አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ሰላማዊ ሰልፉን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ
የዕሪታ ቀን በሚል መሪ ቃል አንድነት ነገ ለሚያከናውነው ሰላማዊ ሰልፍ በጽህፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ በመውጣት በሰልፉ እሪታውን እንዲያሰማ ጠይቋል፡፡የመግለጫውን ሙሉ ቃል ያንብቡ፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
እሁድ የሚካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ኗሪዎች በነቂስ ወጥተው የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ እናቀርባለን!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት ከተመሰረተ እለት አንስቶ በኢትዮጵያችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የሁለንተናዊ እድገት ባለቤት እንድትሆን እየታገለ ይገኛል፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ስለ ሀገርና ስለ ሕዝብ ሲባል አመራሮቻችንና አባሎቻችን ያለምንም ስስት ዋጋ ከፋለዋል፡፡ አሁንም እየከፈሉ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶችን ወደ ጎን ብሎ ‹‹ልማት ብቻ›› በሚል ግንጥል አስተሳሰብ እየተጓዘ ቢገኝም የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት አልቻለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ የዜጎችን የመኖር ዋስትና አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡ ሕዝቡ መሠረታዊ የሆኑትን ቤት፣ ውሃ፣ መብራት፣ ስልክና ትራንስፖርት እንኳ በበቂ ሁኔታ ለማግኘት አልቻለም፡፡ የፍትህ ስርዓቱ አጣቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ስርዓቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክረው በሀይል ነው፡፡ ሰሞንኑ በኦሮሚያ ተማሪዎች ላይ የተወሰደው የግድያ ርምጃ እና የዞን 9 አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞች መታሰር ዋና ማሳያ ነው፡፡ የእምነት ነፃነት ፈተና ውስጥ ወድቋል፡፡ በአጠቃላይ በኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ከመድክም ውጭ ለህዝቡ የተረፈው ምንም ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ፓርቲያችን መንግሥት የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ የተቃውሞ ሠልፍ ለመጥራት ተገድዷል፡፡ ህዝቡ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ያለበትን ችግር እንዲገልጽና መንግሥትን እንዲያስጠነቅቅ ሠላማዊ ተቃውሞ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እሁድ የምናካሂደውን ሠልፍ ለማድረግ ወስነናል፡፡
አንድነት በህግና በሕግ የበላይነት አጥብቆ በማመኑ የተቃውሞ ሠልፉን ለማድረግ ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ ቢቻልም ህጋዊ መብቶቹን አንዳይጠቀም የተለያዩ ሰበቦች እየተደረደሩ ለማደናቀፍ ተሞክሯል፡፡ አንድነት በሰከነና በሳል በሆነ መንገድ መብቱን ሳያስነካ እስከመጨረሻው ለመዝለቅ ችሏል፡፡ በአጠቀላይም ከብዙ ውጣ ውረድና ምልልስ በኋላ የሚያዚያ 26 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም የእውቀና ደብዳቤ ለማግኘት ተችሏል፡፡ የእውቅና ደብዳቤው ከተገኘ በኋላ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በእስርና ወከባ መካከል ሆነው የተሳካ ቅስቀሳ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ለአባላቶቻችን ቁርጠኝነት የተሞላበት ቅስቀሳም ከፍ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
ፖሊስ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ የእውቅና ወረቀቱን እያየ አባሎቻችንና አመራሮችን ካላግባብ ማሰሩ ግን እጅግ በጣም አሳዝኖአል፡፡ ድርጊቱን ህገመንግስታዊ ኃላፊነቱን በመዘንጋት ለገዥው ፓርቲ በመወገን ሰልፋችንን ለማደናቀፍ እንደመሞከር እንቆጥረዋል፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ሊቀመንበር አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባልና በቀስቀቃሽነት የሚታወቀው አቶ ዘላለም ደበበ፤ የፍኖተ-ነፃነት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉና በሹፌርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ነፃነት ዘገየ ሆን ተብሎ በፖሊስ የ11 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆባቸው በእስር እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡ ፖሊስ ከድርጊቱ ተቆጥቦ የህጋዊ ሠልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ አመራሮችንና የፓርቲያችንን ጋዜጠኛ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡ በሕግም እንደምጠይቀ እናሳውቃለን፡፡ በኦሮሞ ተማሪዎችና በዞን 9 አባላት ላይ የተወሰደውን ርምጃም እናወግዛለን፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባና አካባቢው ኗሪዎች አንድነት ያዘጋጀውን የተቃውሞ ሰልፍ በነቂስ ወጥተው በመቀላቀለ ድምፃቸውን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሚያዚያ 25 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ