ሰበር ዜና – ማኅበረ ቅዱሳን በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አያያዝና አጠባበቅ ላይ ለዛሬ የጠራውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተፈቀደው ጥናታዊ ጉባኤ በፓትርያርኩ ውሳኔ ተከለከለ

mahibere kidusan

  • የክልከላው መንሥኤ ‹‹የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለትን ባልተከተለ መልኩ በቀጥታ የአድባራትንና የገዳማትን አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ስብሰባ መጥራት›› የሚል ነው፡፡
  • ለጥናታዊ ጉባኤው የተጠሩት የገዳማትና አድባራት አለቆች ቤተ መዘክር ያላቸው ሦስት አብያተ ክርስቲያን ብቻ መኾናቸውን የገለጹት የጉባኤው አስተባባሪዎች በበኩላቸው÷ ለቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች፣ ምሁራንና እንግዶች ጥሪ የተደረገው ዕቅዱና አስፈላጊነቱ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቀርቦ ከተፈቀደ በኋላ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
  • ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ የኾነበትን አሠራር በመሻር ማንኛውንም ስብሰባዎቹንና ጉባኤዎቹን ኹሉ ያለልዩ ጽ/ቤታቸው ፈቃድ እንዳያካሒድ ከሕጉ ውጭ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
  • የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የጥናታዊ ጉባኤውን መከልከል በተመለከተ በቀጥታ ለማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደደው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ስለጉባኤው እንደሚያውቁና ዝግጅቱም የአሠራር ክፍተት እንደሌለበት ለልዩ ጽ/ቤቱ የበላይ ሓላፊ በማሳወቅ ሊታገድ እንደማይገባው በመከራከራቸው ነው፡፡
  • የማኅበሩ የጥናትና ምርምር ማዕከል በየኹለት ወሩ የሚያካሒደው መደበኛ ጥናታዊ ውይይት አካል የኾነውና የሚመለከተው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ዝርዝር ይዘቱን ከአንድ ወር በፊት በውይይት ጭምር እንዲያውቀው ተደርጎ የተጠራው ጥናታዊ ጉባኤ የተከለከለበት ዋነኛ ምክንያት በልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ እንደተመለከተው ዝግጅቱን ካለማወቅ ጋራ የተያያዘ አይደለም፡፡
  • የልዩ ጽ/ቤቱ የክልከላ ውሳኔ ከታወቀበት ከትላንት ቀትር ጀምሮ ደብዳቤውን ለአፅራረ ቤተ ክርስቲያን አካላት ጭምር እያሰራጩ የሚገኙት በፓትርያርኩ ዙሪያ በአማካሪነትና ረዳትነት ስም ከተጠጉት እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ የዓላማና የጥቅም ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት አማሳኞቹ እነኃይሌ ኣብርሃ መኾናቸው ሲታይ፣ ርምጃውና የክልከላ ምንጩ÷ የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤ ከታገደበት የካቲት ወር ጀምሮ የተጠናከረውና ማኅበሩን ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ልዩ ተልእኮ ባላቸው ባለሥልጣናት ጭምር ተደግፎ የቀጠለ ጫና ስለመኾኑ ግልጽ ያደርገዋል፡፡
  • የማኅበሩ አመራር ስለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የክልከላ ደብዳቤ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ መምከሩ የተገለጸ ሲኾን በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት የጽሑፍ ምላሽ እንደሚሰጥ ተመልክቷል፤ ታይቶ በማይታወቅ የአመራር አቅም ደካማነት፣ የጎሰኝነት ሰለባ በመኾንና ለአማሳኞች ሽፋን በመስጠት በበታች ሠራተኞች ዘንድ ሳይቀር ክፉኛ እየተናቁና እየተጠሉ በመጡት ፓትርያርክ ዙሪያ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን መሣርያ ኾነው የተኮለኮሉትን ጥቅመኞች የማጋለጥ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው እየተገለጸ ይገኛል፡፡